dark cloud
News

ደመና በትግራይ ሰማይ

ትግራይ ፡ ምርጫውን ለማስቆም የሚተላለፍ ውሳኔ የጦርነት አዋጅ ነው፡ የትግራይ ክልል

በትግራይ ክልል ሊካሄድ የታሰበውን ምርጫ ለማስቆም በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚተላለፍ ማንኛውም ውሳኔ እንደ ጦርነት አዋጅ እንደሚቆጥረው የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ::

tplf

መግለጫው የወጣው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከቀናት በፊት ነገ ቅዳሜ የሚካሄድ አስቸኳይ ስብሰባን መጥራቱን አስመለክቶ ነው።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለአባላቱ ባስተላለፈው ጥሪ ላይ 5ኛ የፓርላማ ዘመን 5ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ አስቻኳይ ስብሰባ ነሐሴ 30/2ዐ12 ዓ.ም እንደሚካሄድ ከማሳወቅ ውጪ በምን አጀንዳ ላይ ውይይት እንደሚካሄድ የገለጸው ነገር ባይኖርም፤ የትግራይ ክልል ሥራ አስፈጻሚ በክልሉ በሚካሄድ ምርጫ ላይ የሚሰጥን ውሳኔ እንደማይቀበለው ከወዲሁ አሳውቋል።

የክልሉ ሥራ አስፈጻሚ መግለጫ የፌደሬሽን ምክር ቤት የጠራውን አስቸኳይ ስብሰባ “ያልተለመደና አጀንዳው የማይታወቅ” ሲል ቢጠቅሰውም በትግራይ የሚካሄደው ምርጫን የሚመለከቱ ውሳኔዎች ሊተላለፉ እንደሚችሉ ባስቀመጣቸው ሃሳቦች አመልክቷል።

የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት በ27/12/2012 ዓ.ም ለፌዴሬሽን ምክር ቤቱ በጻፈው ደብዳቤ ምክር ቤቱ አስቸኳይ ጉባዔ ለማካሄድ በሚያስብበት ወቅት አጀንዳውን ለአባላቱ መግለጽ እንደሚጠበቅበት አስረድቶ፣ በተደጋጋሚ ስለአጀንዳው መጠየቁን ገልጿል።

ሆኖም ግን አጀንዳውን ሳያውቁ እንዲሳተፉ መጋበዛቸውን በመጥቀስ አስቀድሞ አጀንዳው የማይገለፅላቸው ከሆነ ” ለመሳተፍ እንደማይችሉ” አስፍሯል።

የሥራ አስፈጻሚው መግለጫ እንዳለው “ምርጫውን ለማስቆም ወይም ለማደናቀፍ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚወስደው ማናቸውም ውሳኔ እንደጦርነት አዋጅ ይቆጠራል” ከማለቱ በተጨማሪ “በዚህ ምክንያት ለሚፈጠር ችግር ተጠያቂው የፌዴሬሽን ምክር ቤትና ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል” ሲል ብሏል።

በዚህም ምርጫውን ለማስቆም የሚተላለፍ ውሳኔ ተቀባይነት እንደሌለው በመግለጽ “ሕዝቡ በምርጫ የሚያስተዳድረውን አካል እንዲመርጥ ሊበረታታ የገባዋል እንጂ ይህን ሂደት ለማስቆም የሚደረግ ጥረት ፀረ ዲሞክራሲያዊ” መሆኑን አመልክቷል።

መግለጫው በትግራይ ክልል ስድስተኛው ዙር ምርጫ ጊዜውን ጠብቆ እንዲካሄድ ከወራት በፊት ውሳኔ መተላለፉን አስታውሶ፤ ይህንንም ለማሳካት በክልሉ ያሉት የሚመለከታቸው አካላት የሚጠበቅባቸውን እያከናወኑ በመሆናቸው ክልሉ በምርጫው “ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ በሕዝብ ውሳኔ መሰረት ቀጣዩ የክልሉ መንግሥት የሚቋቋም ይሆናል” ብሏል።

ቀደም ሲል የትግራይ ክልል ከሌሎቹ የአገሪቱ ክልሎች በተለየ ምርጫውን በተናጠል ለመካሄድ መወሰኑን ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይህ ውሳኔ ሕገወጥ መሆኑን በመግለጽ ክልሉ ምርጫ ለማካሄድ ከሚያደረገው እንቅስቃሴ እንደቆጠብ አሳስቦ ነበር። ክልሉም ይህንን በመቃወም ምላሽ ሰጥቶ ምርጫውን በማካሄድ ገፍቶ ለምርጫው ከአንድ ሳምንት ያነሰ ጊዜ ቀርቷል።

ሐሙስ ምሽት የወጣው መግለጫ ሕዝቡን በማሳተፍ ለሁሉም ግልጽ በሆነ ሁኔታ ምርጫውን ለማካሄድ ወደ ፍጻሜው መደረሱን ጠቅሶ በዚህ ጊዜ የሚደረግ ማንኛውንም ጣልቃ ገብነት “በአገሪቱ ህልውና ላይ አደጋን የሚጥል መሆኑ ሊታወቅ ይገባል” ሲል አስጠንቅቋል።

በዚህም መሰረት ምርጫው በአገሪቱና በክልሉ ሕግ መሰረት የሚካሄድ በመሆኑ በማንኛውም ጣልቃ ገብነትና ጫና ሂደቱ እንደማይቆም አመልክቶ “ሕዝቡም ይህንን ለመመከት እንዲዘጋጅ” ጥሪ ከማቅረቡ በተጨማሪ የአገሪቱ “ብሔር ብሔረሰቦችና ፌደራሊስት ኃይሎች” ከጎኑ እንዲቆሙ ጠይቋል።

በመላው አገሪቱ በነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ ሊካሄድ ታቅዶ የበረው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ በሕዝብ ተወካዮች እና በፌዴሬሽን ምክር ቤት ቢወሰንም የትግራይ ክልል ምርጫውን በተናጠል ለማካሄድ ወስኖ ጳጉሜ 04/2012 ዓ.ም ለማካሄድ ተዘጋጅቷል።

ይህንን በተመለከተም የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ የትግራይ ክልል መንግሥት ምርጫ ለማካሄድ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንዲያቆም የሚያሳስብ ደብዳቤ ለክልሉ መጻፉ ይታወሳል።

ምክር ቤቱ በዚህ ደብዳቤው ላይ እንዳመለከተው የትግራይ ክልል የተሰጠውን ማሳሰቢያ ሳይቀበል ቀርቶ “ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ በሚጥል” ድርጊቱ የሚገፋ ከሆነ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት “በሕገ መንግሥቱና በሌሎች ሕጎች የተሰጠውን ስልጣን ለመተግበር እንደሚገደድ” አስጠንቅቆ ነበር።

ለዚህም የትግራይ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ በሰጡት ምላሽ የደረሳቸው ማስጠንቀቂያ ሕገ መንግሥታዊ መሰረት የሌለው መሆኑን በመግለጽ “የሕገ መንግሥት መርሆዎችን የሚጥስ፣ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ሉአላዊ የስልጣን ባለቤትነትን የሚጻረር” በመሆኑ የትግራይ ክልል መንግሥትና ሕዝብ እንደሚቃወሙት ገልፀው እንደማይቀበሉት አሳውቀዋል።

በክልሉ የታቀደው ምርጫ ሊካሄድ ቀናት የቀሩት ሲሆን አጀንዳው ምን እንደሆነ እስካሁን ያልታወቀ አስቸኳይ ስብሰባ የፌዴሬሽን ምክርቤት ለማካሄድ ጥሪ ማቅረቡን ተከትሎ ነው የትግራይ ክልል ይህንን መግለጫ ያወጣው።

ትግራይ ፡ ምርጫው “እንዳልተደረገ የሚቆጠር፣ የማይጸናና ተፈጻሚነት የሌለው ነው” የፌዴሬሽን ምክር ቤት

በትግራይ ክልል በመጪው ረቡዕ ሊካሄድ የታቀደው ምርጫ ከአገሪቱ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን በመሆኑ “እንዳልተደረገ የሚቆጠር፣ የማይጸናና ተፈጻሚነት የሌለው ነው” ሲል የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ መወሰኑ ተገለጸ።

ethiopian parliament

ምክር ቤቱ ዛሬ [ቅዳሜ] ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባው ላይ በትግራይ ክልል የሚካሄደውን የምርጫ እንቅስቃሴን በተመለከተ የሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበለት የውሳኔ ሐሳብ ላይ መወያየቱ ተገልጿል።

በዚህም መሠረት የትግራይ ክልል ምርጫን በሚመለከት ያሳለፈው ውሳኔ፣ እንዲሁም እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ከአገሪቱ የበላይ ሕግ ጋር የሚቃረን በመሆኑ ተፈጻሚነት እንደሌለው ገልጿል።

በዚህም ምክር ቤቱ በቀረበለት የውሳኔ ሐሳብ መሰረት በትግራይ ክልል ምርጫ ለማካሄድ የሚደረገው እንቅስቃሴ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(1) መሰረት እንዳልተደረገ የሚቆጠር፣ የማይጸናና ተፈፃሚነት የሌለው ነው በማለት፣ ተቀባይነት የለውም ብሏል።

በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ “ሕገ ወጥ አካላት በሚፈፅሙት ድርጊት ምክንያት በሕዝቡ ላይ ጉዳት ሊደርስበት አይገባም ብሎ የሚያምን መሆኑና በቀጣይም ምክር ቤቱ ለትግራይ ሕዝብ ካለው ውግንና አንጻር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳት እንዳይደረስ ችግሮችን በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መግባባት ላይ ተደርሷል” ብሏል።

በኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ሊካሄድ ዕቅድ ተይዞለት የነበረው ምርጫ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችል አመቺ ሁኔታ የለም በማለት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምርጫው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ መወሰናቸው ይታወሳል።

በዚህም የፌደራልና የክልል ምክር ቤቶች ቀጣዩ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ በሥራቸው ላይ እንዲቆዩ ተወስኖ የነበረ ቢሆንም የትግራይ ክልል በተናጠል ምርጫውን እንደሚያካሂድ አሳውቆ የተለያዩ ተግባራት ሲያከናውን ቆይቷል።

ክልሉ ምርጫውን እንዲያስፈጽምለት ብሔራዊውን የምርጫ ቦርድ ጠይቆ የነበረ ቢሆንም፣ ቦርዱ በተናጠል ምርጫውን ለማካሄድ የቀረበውን ጥያቄ ባለመቀበሉ፤ የትግራይ ክልል የራሱን የምርጫ ኮሚሽን አቋቁሞ የምርጫ ዝግጅት በማድረግ ድምጽ ለመስጠት ቀናት ብቻ ቀርተውታል።

ምርጫን በሚመለከት በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተላለፈው ውሳኔ በመላው አገሪቱ የሚገኙ ክልሎች ተግባራዊ የማደረግ ግዴታ ቢኖርባቸውም፣ የትግራይ ክልል ከዚህ ውሳኔ ውጪ በሚቃረን ሁኔታ ምርጫ ለማካሄድ እንቅስቀሴ እያደረገ መሆኑን ለምክር ቤቱ በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ተጠቅሷል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባካሄደው በዚህ አስቸኳይ ስብሰባው ላይ የትግራይ ክልል መንግሥት ያወጣው የምርጫ አዋጅ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረን መሆኑን፣ በዚህም ክልሉ የምርጫ ኮሚሽን ማቋቋሙ ሕገ መንግሥቱ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሰጠውን ስልጣን እንደሚቃረን ገልጿል።

በዚህም የትግራይ ክልል ምክር ቤት፣ አስፈፃሚ አካላት እና የምርጫ ኮሚሽን ምርጫን በሚመለከት ያወጣው የምርጫ አዋጅ የተላለፉ ውሳኔዎችና የፈፀሟቸው ተግባራት ከሕገ መንግስቱ ጋር የሚቃረኑ በመሆናቸው፣ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 9(1) መሰረት “እንዳልተደረጉ የሚቆጠሩ፣ የማይፀኑ እና ተፈፃሚነት የሌላቸው ናቸው” በማለት የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ ውሳኔ አስተላልፏል።

ከዚህ በተጨማሪ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የራያ ራዩማ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ እና የወልቃይት ጠገዴ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ለምክር ቤቱ ያቀረቧቸውን ቅሬታዎች በመጥቀስ “የትግራይ ክልል እያካሄደ ካለው ሕገ ወጥ ምርጫ ጋር ተያይዞ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች መብት አለማክበር ተቀባይነት የሌለውና ሊታረም የሚገባው” መሆኑን ምክር ቤቱ አመልክቷል።

በትግራይ ክልል ምርጫ ለማካሄድ 2̌.7 ሚሊዮን ሰዎች መመዝገባቸውና ለምርጫው የሚያስፈልጉ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን የክልሉ ምርጫ ኮሚሽን መግለጹ ይታወቃል።

በዚህም መሰረት የድምጽ መስጫው ቀን ረቡዕ ጳጉሜን 04/2012 ዓ.ም እንደሚሆን መገለጹ ይታወሳል።

 

ምንጭ፡ bbc.com/amharic

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *