በአለማየሁ አንበሴ
መንግስት ወንጀለኞች ብሎ ለበየነው የህወኃት ቡድን ውግንና በማሳየት የሃገር ክህደት ፈፅመዋል የሚል ውንጀላ የቀረበባቸው የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ዘ ሄግ በሚገኘው ዓለማቀፍ የወንጀለኞች ፍ/ቤት ማክሰኞ ዕለት ክስ እንደሚቀርብባቸው ምንጮች ጠቆሙ፡፡
በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የህግ ባለሙያዎች በዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ላይ ያደራጁት ክስ፤ በዓለማቀፍ ተቋም ከተሰጣቸው ሃላፊነት ውጭ በመንቀሳቀስ አሸባሪ ቡድንን የመደገፍ ወንጀል የሚል ነው ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ዶ/ር ቴዎድሮስ ላይ የዘር ማጥፋትና በሰው ልጅ ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ክስ እንደሚቀርብባቸውም ታውቋል፡፡ የህወኃት አባል በነበሩበት ዘመን በፈጸሟቸው የዜጎች ሰብአዊ መብት መጣስ ወንጀልም እንደሚከሰሱ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የአለማቀፍ የወንጀለኞች ፍ/ቤት (ICC) አቃቤ ህጎችም፣ የቀረቡላቸውን ማስረጃዎች በመመርመር ክሳቸውን አደራጅተው በማጠናቀቅ ላይ መሆናቸው ተነግሯል፡፡
የፊታችን ማክሰኞ ህዳር 22 ቀን 2013 ዓ.ም ዘ ሄግ በሚገኘው ፍ/ቤት፣ ጉዳዩን የያዙት አቃቤ ህግ ዴቪድ ስቴይማን፣ ክሳቸውን እንደሚያቀርቡና ለጋዜጠኞችም ማብራሪያ እንደሚሰጡ ይጠበቃል ተብሏል።
Source: Addis Admas