Site icon Dinknesh Ethiopia

የሊቅ ዐቢይ የሰላም ኖቤል ሽልማቱ ሲፈተሽ – ከኀይሌ ላሬቦ

Haile Larebo

ከኀይሌ ላሬቦ – ሊቅ ዐቢይ የሰላም ኖቤል ሽልማት በመቀበሉ የብዙዎቻችን ደስታ የሰማይ ጣራ እስከመንካት ደርሷል። አገሪቷ ያሳለፈችውንና እየተፋጠጠች ያለውን ስፍር ቊጥር የሌለውን ለሚሰማ ሁሉ ዘግናኝና አሰቃቂ ግፍና ሥቃይ ወደመርሳት ያለች ይመስላል። ሆሆታውንና እልልታውን እንደከንቱ ውዳሴ የሚያዩትም አልጠፉም። እንደነዚህ ዐይነቶቹ ሀገራዊ ክብርና ኩራት፣የሌላቸው ተብለው እየተወቀሱ ናቸው። የተሸለመችው፣ኢትዮጵያ፣ነች። ይኸንን የማይረዳ ጤንነቱ መመርመር አለበት እስከማለትም ተደርሷል።

ይቅርታ ይደረግልኝና ስለዚህ ዐጠር ባለ መልክ ጥቂት እርማትም ውዳሴም ላክልበት። በምንም መልኩ ካለመሸለም መሸለም እጅግ ደስ ይላል። እውድድር የገባ ካሸነፈ፣ ሁሌም ይደነቃል። ሊቅ ዐቢይም ተወዳድሮ አሸንፏል። ስለዚህ ቢወደስና ቢደነቅ የሚጠበቅ ነው። ከንጉሣዊ አገዛዝ መጨረሻ በኋላ፣ ኢትዮጵያን ዓለም ያወቃት በድሮ ግርማዋና ክብሯ ሳይሆን በዘቀጠ ሰብእናዋ ነው።

ድርቅ፣ ራብ ሲባል እንደምሳሌ የምትጠራ ኢትዮጵያ ናት። ከዚያ ባሻገር፣ በግራ ፖለቲካ፣ ጦርነት፣ የርስበርስ ዕልቂትና ወደኋላ ቀርነትም አንደኛው እሷ ናት ቢባል ከእውነት የራቀ አይደለም። የዐቢይ ሽልማት የኢትዮጵያ ስም ከተለመደው ከሩጫ ጐን በሰላም ወዳድነትም በዓለም መድረክ እንዲነሣ አድርጓል። ከቀረው አብዛኛው የዓለም ክፍል በተለይም አፍሪቃ፣ ከአስደናቂ ጥንታዊ ሥልጣኔዋ በተጨማሪ፣ የራሷም ብሔራዊ ቋንቋና የባህል ልብስ፣ እንዳላት ለማስታወቅ ከፍተኛ ዕድል ነበረው።

ግን በሚያሳዝን ሁናቴ ሊቅ ዐቢይ ዕድሉን አልተጠቀመውም። በአማርኛ ፈንታ የተጠቀመው ባዕድና ቄሣራዊ ቋንቋ ነው። እንደ ገናናው የህንዱ መሪ ማኅተማ ጋንዲ በገዛ አገሩ ልብስ በመላው ዓለም ፊት ከማብረቅረቅ ይልቅ ከባሕርማዶ የተዋሰውን ለመልበስ መረጠ። እንደኔ ከሆነ፣ ይኸ ትልቅ ስሕተት ነው። ይኸንን ግድፈት ወደጐን እንበለውና፣ ሽልማቱ በጥሩ እንጂ በመጥፎ መታየት ያለበት አይመስለኝም።

ለመሆኑ አማራ ማነው – ከኀይሌ ላሬቦ

ጥያቄ የሚነሣው የተሸለመበት ዋናው ምክንያት ምንድርነው ተብሎ ሲጠየቅ ነው። የኖቤሉ ሸላሚዎች ደጋግመው እንደነገሩን፣ የተሸለመበት ዋነኛው ምክንያት ከኤርትራ ጋር ዕርቅ በመፍጠሩ ነው። ይኸ ደግሞ ጥቅሙ ለምዕራባዉያን እንጂ ለኢትዮጵያ እንዳልሆነ፣ ታሪክን በአጭሩ ዳሰስ ብናደርግ የሚረዳ መሰለኝ።

ከኢጣልያን፣ ከዚያ ኋላም ለዐሥር ዓመታት ካስተዳደረው ከእንግሊዝ መንግሥት፣ ጀምሮ የምዕራባውያን ፍራቻ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ታታሪና ነፃነት ወዳድ ስለሆነ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣኔ መጐናፀፍ ይችላል፤ ኢትዮጵያ ከዘመነች ደግሞ የማትደፈር ብርቱ አገር በመሆን ከምዕራባውያን ተፅዒኖና ቊጥጥር ውጭ ለመሆን ትበቃለች የሚል ነው።”
ስለዚህ ከዚህ ሥጋት ለመከላከል ምዕራባውያን እንደዋና ግባቸው አድርገው የያዙት ኢትዮጵያን ማዳከም ይገባል የሚል ነው። ይኸንን ለመረዳት “ከታሪክ መድረክ፤ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ትላንትናና ዛሬ” በሚለው ድርሰቴ አሰፍሬአለሁና፣ የፈለገ እዚያ ማንበብ ይችላል። እንግሊዝ ኤርትራን ባስተዳደረችበት ወቅት፣ ይኸንን ዓላማ ለማሳካት ተግታ ሠርታለች።

ግቡን ባትመታም፣ የዘራችው ዘር ቈይቶም ቢሆን መክኖ አልቀረም። እሷን የተካችው አሜሪቃ ይኸን ዓላማ አሜን ብላ ተቀብላ፣ ከብዙ ልፋት በኋላ፣ በሺዘጠኝ መቶ ሰማንያ ዓ.ም. ላይ ላገላግላችሁ ስትል በሽምግልና በለንደን ከተማ ባቀነባበረችው ስብሰባ አማካይነት በግብር ላይ ለማዋል በቅታለች።

Address to the Oromo Intellectuals’ – ከኀይሌ ላሬቦ

በምዕራባውያን ዕይታ፣ ኢትዮጵያ የምትዳከመው አገሪቷን በመከፋፈል ነው። ቀላል ሆኖ የታያቸው ሰሜኑን ከተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ነጥሎ ነፃ አገር ማድረግ ሲሆን፣ ቀጥሎ ደግሞ በተለያዩ ጎሳዎች ከፋፍሎ ርስበርስ ማጋጨትና ወደጦር ዐውድማ መለወጥ ከዚያም ከተቻለ መገነጣጠል ነው። ከላይ እንዳልሁት፣ የሰሜኑን ክፍል አሜሪቃ በትግል አጋሩ የትግራይ ሕዝብ የነፃነት ግንባር [ትሕነግ] አሳክቶታል።

ይሁንና በትሕነግና በሻዕቢያ መካከል የተፈጠረው ጠብና ውዝግብ፣ የኤርትራን ነፃነት አጥያቄ ውስጥ አስገባ። የዐቢይ ሥራ ለገዛ አገሩ ጥቅም ምንም ሳይደራደር፣ ኤርትራን ከዚህ ውጥንቅጥና ማጥ አወጥቷል ማለት ይቻላል። በኢትዮጵያ ስም ነፃነቷን አረጋግጦላታል። ስለዚህ ዐቢይ የምዕራባውያንን ምኞት በማይቀለበስ መልክ ሙሉ በመሉ አሳክቷል የማይባልበት ምክንያት የለም።

ኢትዮጵያውያን በጥቅምት ዐሥራሰባት ቀን ሺስምንት መቶ ሰማንያ ዘጠኝ ዓ.ም. ላይ በአዲስ አበባ ከኢጣሊያን ጋር በመፈራረም ኢጣሊያኖች የያዙት አገር የኢትዮጵያ አካል መሆኑን፣ የኢጣሊያ መንግሥት “መልቀቅ ያማረው እንደሆነ ለኢትዮጵያ ይመልሳል” የሚለው ውልና፣ በኋላም አፄ ኀይለሥላሴ በጥበብ ከኢትዮጵያ ጋር ያዋሃዱት አገር የኛ ነው እንዳይሉ አድርጓል። ዐቢይ የአውሮጳውያንን ሤራ በመቀበል፣ ለሥልጣኑ ሲል ሰለባቸው ሁኗል። ይኸ ለኢትዮጵያ ትልቅ ኪሣራና ውርደት እንጂ ክብር አይመስለኝም።

ዐቢይ በአሜሪቃ ምክርና ርዳታ ትሕነግ-ኢሕአዴግ፣ ኢትዮጵያውያንን ከፋፍሎ ለዘለዓለም ሊገዛ ሲል የፈጠረውን የክልል ሥርዐት በሕጋዊነት እንዲቀጥልና ዕውቅናውን ሊያረጋግጥለት እየሠራ እንዳለ እናያለን። ስለዚህ ዐውቆም ይሁን ሳያውቅ፣ ወዶም ይሁን ሳይወድ፣ ሁለተኛውን የምዕራባውያን ግብ ሊያሳካ በትጋት እየሠራ እንደሆነ አያጠራጥርም። ይኸም ለኢትዮጵያ ውርደት እንጂ ክብር ነው ማለት አይቻልም።

ዐቢይ በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ [ሕወሓት] ማሕፀን ተፈልፍሎ ካደገ በኋላ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር [ኢሕአዴግ] በዘረጋው የስለላ መረብ በታማኝነት በማገልገል በሥርዐቱ ዕርከን አድጎ ከፍተኛ ሥልጣን ለመጨበጥ በቅቷል። ለሠላሳ ዓመታት ያህል የኢትዮጵያን ስምና ታሪክ በማጠልሸት፣ ሀብቷን በመበዝበዝ፣ ሕዝቧን በመከፋፈል፣ አንድነቷን በመሸርሸር፣ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ ሲያበቃ፣ በቅርቡ በሞት አፋፍ እየጣረ ያለውን ኢሕአዴግን፣ ሕይወቱን ሊያራዝም ሲል በለውጥ ስም ብልፅግና በማለት ሊያጠምቀው ችሏል።

ይሁንና ድርጅቱ ከርስበርስ የሥልጣን ሽኩቻና ሽግሽግ ውጭ፣ ያደረገ የሥርዐትም ሆነ፣ የአቋም ለውጥ በፍጹም የለም ማለት ይቻላል። አባቶቻችን የጉልቻው መለወጥ ወጡን አያጣፍጥ እንደሚሉ፣ የድርጅቱ ስም መለወጥ የተሻለ ሁናቴ ያመጣል የሚል ስሜት በአብዛኛው ሕዝብ ልቦና በማስነገብ፣ አፍኖት የያዘውን ችግሩን ለጊዜው ሊያስረሳውና ሊያደነዝዘው ይችል ይሆናል። የኢትዮጵያን ትንሣኤ ያመጣል ብሎ ማሰብ ግን ራስን ማታለል ብቻ ሳይሆን ጅልነትም ነው።

ሊቅ ዐቢይ የአገሩን ችግር እንዲቀርፉ ሲል የሚያቋቋማቸው ኮሚቴዎች፣ በሥራው እንዲያግዙት ሲል የሚሾማቸው አጋሮቹ ሚኒስትሮች፣ በየመስኩና በየአስተዳደሩ ዘርፍ የሚመርጣቸው አብዛኞቹ ሰዎች፣ በብቃታቸውና በሙያቸው ዕውቅና ሳይሆን፣ ልክ እንደራሱ በኢሕአዴግ የተፈለፈሉና የተመለመሉ፣ የሥርዐቱ ጠንሳሾች፣ ፈጣሪዎችና አራማጆች ናቸው ማለት ይቻላል። ይኸም የሚያመለክተው ሊቅ ዐቢይ እየሠራ ያለው በሕዝቡ የተጠላውን ሥርዐት ለመቀጠልና ለማጠናከር እንጂ፣ አገሪቷ እየተጋፈጠች ካለች አንገብጋቢና ከባድ ፈተና ለመታደግ አይደለም ቢባል ስሕተት አይመስለኝም።

ሊቅ ዐቢይ የኢትዮጵያ ሕዝብ በንግግሩ ተመሥጦ ባጨበጨበለት መሠረት፣ ሕወሓት በአፈቀላጤው ኢሕአዴግ ያቋቋመውን ሥርዐት አገርስሶ መጣል ሲችል፥ እስካሁን የወሰደው ርምጃ አሳዛኝ እንጂ የሚደነቅ አይደለም። ምዕራባውያንን ግን እንዳስደሰተ፣ ሽልማቱ ይናገራል። ሽልማቱ ኢትዮጵያን ጠቀማት፣ ከዚያም ዐልፎ ደግሞ የተሸለመችው ኢትዮጵያ ነች ማለት ግን በኔ እምነት በጣም አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን፣ እጅግ በጣም የሚፈታትንም ነው።

Exit mobile version