
መስከረም 10፣ 2018
(September 20, 2025 )
አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ
ከኢትዮጵያውያን ትብብር ንቅናቄ፣
ጉዳዩ፦ በኢትዮጵያ የፖለቲካ/የሕሊና እሥረኞች የሚያካሄዱት/ያካሄዱት የረሃብ አድማ፣
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ተቃዋሚ ድርጅቶች፣ መሪዎችና አባሎቻቸው፣ የፖለቲካና የሰብዓዊ መብት ተሟዋጓቾች፣ ጋዜጠኞችና ሌሎችም የተለያዩ ሃሳብ አስተናጋጆች፣ በጠ/ሚኒስትር ዓቢይ መንግሥት እየታደኑ፣ በየእሥር ቤቶች መታጏራቸው፣ የተለመደ የዘወትር ሕይወት ለመሆኑ በሀገር ውስጥም፣ በዓለም አቀፉ ደረጃም የታወቀ ሀቅ ነው። ምንም ዓይነት የፍርድ ሂደት ሳይቃኛቸው፣ መረጃ በሌለው የፈጠራ ክስ በየእሥር ቤቱ ተወርውረው የስቃይ ሕይወት ከሚገፉት መካከል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፦
1ኛ/ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል፣
2ኛ/ የተከበሩ አቶ ዮሐንስ ቧያሌው፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል፣
3ኛ/ የተከበሩ አቶ ታዬ ደንድአ፣ የቀድሞ ምክትል ሚኒስትር፣
4ኛ/ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሲሳይ አውጋቸው፣
5ኛ/ ዳዊት በጋሻው፣ ሲሳይ ጎበዜ፣ መስከረም አበራ፣ ገነት አስማማው (ጋዜጠኞች)፣
6ኛ/ ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ፣ ዶ/ር ቴዎድሮስ ኃ/ማርያም፣ ዶ/ር ጫኔ ከበደ፣ ዶ/ር ካሣ ተሻገር (ሃኪሞች)፣
7ኛ/ አቶ ታዴዎስ ታንቱ፣ የታሪክ ሊቅና ጋዜጠኛ፣
እነዚህና ሊሎችም በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች፣ መረጃ አልባ በሆነ የፈጠራ ክስ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ስቃይና መከራ እያዩ ነው። በእስረኞች ላይ በየጊዜው ከሚለበዱ የፈጠራ ክሶች ጥቂቶቹን ለመጥቀስ፣ ሽብርተኝነት፣ የጥላቻ ንግግርና ብጥብጥ አጫሪነት የሚሉትን ያካትታል።
እውነታው ግን፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ሽብር የሚያካሄደው፣ ሕገ መንግስቱን በመጣስ ሰብዓዊና ፖለቲካ መብትን የሚረግጠው፣ ለ7 አመታት የዘለቀው፣ የአቢይ አህመድ አስተዳደር ነው። አገሪቱን የጦርነት አውድማ አድርግዋታል። የሰሜኑ የትግራይ ጦርነት፣ በአማራና በአፋር ጭምር ከ 1 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ከጨረሰና አይሌዎችን አቁስሎ፣ በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ንብረት ካወደመ በኃላ፣ ሕዝብ ከዚያ ጦርነት ሳያገግም፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች፣ ሌሎች አውዳሚ ጦርነቶች እየተካሄዱ ነው። በመላ ሀገሪቱ የሰላምና የፀጥታ እጦት፣ ሕዝቡን ከሚያባንን ስጋት ላይ ጥሏል። ዘር ተኮር ግድያና ማፈናቀል፣ የሕዝቡ ዕጣ ፈንታ ሁኗል። በዚያ ላይ የኢኮኖሚ ድቀት፣ የገንዘብ ዋጋ ግሽበት፣ የፍጆታ ዕቃ ዋጋ መናር፣ በጠቅላላው የኑሮ ውድነት ህዝቡ ከሚችለው አቅም በላይ ሆኖበታል።
በአንፃሩ ግን፣ የሙስና ብዛትና የባለሥልጣናት በዚህ ዓይን ባወጣ ዝርፊያ መሰማራት፣ የአደባባይ ምስጤር ሁኗል። በዚያው መጠን፣ የሰብአዊ መብት ረገጣ፣ የተቃውሞ ሃሳብ አለመቀበል፣ የአቢይ መንግሥት የዕለት በዕለት ፖሊሲው ሲሆን፣ የጠቀስናቸው የሕሊና እስረኞችና ሌሎችም በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ፣ ለእስራትና ስቃይ የሚዳረጉት፣ በዲሞክራሲያዊ መብታቸው ስለተጠቀሙና፣ ጦርነት ይቁም፣ሰላም ይምጣ፣ የሕዝብ ሰብዓዊና ዲሞክራሲ መብት ይከበር ብለው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው፣ በሰላማዊ መንገድ ስለታገሉ ብቻ ነው።
በዚህም ምክንያት፣ከ 300 በላይ የሚሆኑ የሕሊና እስረኞች፣ በቂሊንጦ እስር ቤት የረሃብ አድማ እያካሄዱ ነው/አካሄደዋል።ተቃውሟቸውም የሚከተሉት ናቸው፦
- ያለምንም ፍትሓዊ የፍርድ ሂደት ለረጅም ጊዜ መታሰራቸው፣
- የሕክምና አገልግሎት መነፈጋቸው፣
- በየዕለቱ ሰብዓዊ መብታቸው መረገጡ፣
- የአካል ጉዳት ለሚያስከትል ድብደባና እንግልት መዳረጋቸው፣
- ዘር ተኮር ጥቃት ስለሚደርስባቸው ነው።
ጥያቄዎቻቸው ይህ ሁሉ በአስቸኳይ እንዲቆምና፦
1) የሕሊና እስረኞች በሙሉ፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቁ፣
2) እስከዚያው አጣዳፊ የሕክምና ዕርዳታ እንዲያገኙ፣
3) በአማራ ብሔረሰብ አባላት ላይ የሚካሄደው የዘር ተኮር ጥላቻና ጉዳት በአስቸኳይ እንዲገታ፣
4) ክስ የተመሰረተባቸው፣ጉዳያቸው ፍትሓዊነትን በተከተለ የፍርድ ሂደት፣ እንዲታይ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም፣ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብና ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እስር ቤት ለመጎብኘት የኢትዮጵያን መንግሥት በመጠየቅና በመጎትጎት፣
- የእሥር ቤቱን ፅዳትም ሆነ በሌላ መልክ እጅግ ያዘቀጠ ሁኔታ እንዲመረምሩልን፣
- መንግሥት የእስር ቤቱን እጅግ ያዘቀጠ ሁኔታ እንዲያሻሽል እንዲጠይቅልንና፣
- በነፃ የምንለቀቅበትን መንገድ እንዲያፋጥኑልን እንማፀናለን ብለዋል:
በመጨረሻም እነዚህ የፖለቲካ እስረኞች፣ በከባድ እስራትና ቁጥጥር ሥር እያሉ፣ ያለምንም ፍርሃትና ሙሉ ድፍረት የተጋረጠባቸውን የግፍ አገዛዝ ጥሰው፣ የረሃብ አድማ በመጥራት የራሳችውን እጅግ የከፋ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን፣ የመላው ኢትዮጵያን ሕዝብ ሰቆቃና ብሶት እንዲሁም እሮሮ በማሰማት፣ ለፍትሕ፣ ለሰብዓዊ መብት መከበር፣ ለዲሞክራሲ ልዕልና ላደረጉት ትግል፣ መወደስ፣ መከበርና መደገፍ አለባቸው።
የፖለቲካና የሕሊና እሥረኞች በአስቸኳይ ይፈቱ
የተባበረ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ያሸንፋል
የኢትዮጵያውያን ትብብር ንቅናቄ






