ኢሕአፓ ጽናት እስከ ድል በሚል መሪ ሃሳብ ከሃምሌ 14 እስከ ሃምሌ 15 ቀን 2017 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባዔውን በሲዳማ ክልል ሃዋሳ ከተማ ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ በዚህ ጉባዔ ላይም ከመላው ኢትዮጵያ የተወጣጡ የኢሕአፓ አባላት ተሳትፈዋል፡፡
በጉባዔው ላይ የኢሕአፓ መስራቾችና የቀድሞ አባላት እና አማካሪዎች የሆኑት መርሻ ዮሴፍ፣ ክፍሉ ታደሠ እና መንግስቱ ሙሴ (ዶ/ር) ከባህር ማዶ ኢሕአፓን እና ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ የሲዳማ ክልል የሃገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ በእንግድነት የተጋበዙ አካላትም ንግግር አድርገዋል፡፡
ወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ እና የኢሕአፓን ቀጣይ ፖለቲካዊ አቅጣጫ የተመለከተ መነሻ ጥናት ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ቀጣይ የኢሕአፓ ፖለቲካዊ አቅጣጫ ሆኖ እንዲቀጥል በጠቅላላ ጉባዔው ጸድቋል፡፡ ሌሎችም የጠቅላላ ጉባኤውን ውሳኔ የሚጠይቁ ዋና ዋና ጉዳዮች ቀርበውም ጸድቀዋል፡፡
ኢሕአፓ ለሚወቀስባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች የኢሕአፓውያን የጋራ መልሶች በዝርዝር ቀርቧል፡፡
ላለፉት ሶስት አመታት ፓርቲውን በጽናት እና በታማኝነት ሲመሩ የነበሩት ረዳት ፕሮፌሰር ዝናቡ አበራ ኢትዮጵያን እና ትግሉን ለወጣቱ ማስረከብ ይገባናል በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል። ድምጻቸውንም ለሌላኛው ተወዳዳሪ መጋቤ ብሉይ አብርሀም ሀይማኖት ሰጥተዋል። ይህ የቀድሞ ሊቀመንበሩ ተግባር ስልጣንን አንዴ ካገኙ በኋላ ‹ከስልጣኔ የሚለየኝ ሞት ነው› የሚል አስተሳሰብን ለሚከተሉ ባለስልጣናት በምሳሌነት የሚጠቀስ ተግባር እንደሆነ ፓርቲያችን በጽኑ ያምናል፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር ዝናቡ አበራ ላለፉት አመታት የአገዛዙ እና የአሽከሮቹ እስር፣ ድብደባ፣ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ሳይበግራቸው ህዝብን፣ ሃገርን እና ፓርቲያቸውን በታማኝነት እና በጽናት በማገልገላቸው ኢሕአፓ በአባላትና አመራሩ ስም በእጅጉ ያመሰግናቸዋል፡፡
ላለፉት ሶስት አመታት ፓርቲውን ሲመሩ የቆዩ አመራሮችን ለመተካትም የአዲስ አመራር ምርጫ ተካሂዷል፡፡ በዚህ መሰረትም ኢሕአፓ፡-
መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት – የኢሕአፓ ፕሬዘዳንት
መላከ ካሳ – የኢሕአፓ ምክትል ፕሬዘዳንት
ሚስጥረሥላሴ ታምራት – የኢሕአፓ ዋና ጸሓፊ
ሙሉጌታ ሓድጉ – የኢሕአፓ የፋይናንስ ንብረት አስተዳደር አድርጎ መርጧል፡፡
ኢሕአፓ አዲስ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን የመረጠ ሲሆን ማዕከላዊ ኮሚቴውም ቀሪ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን መርጦ አጽድቋል፡:
አሕአፓ ባለፉት አመታት የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ተገማች አለመሆናቸውን በተደጋጋሚ በሰራቸው ጥናቶች አረጋግጧል፡፡ ለሁሉም በሚታይ መልኩ ዓላማቸው የገዢውን ስልጣን መጠበቅ ብቻ የሆኑ ጦርነቶች እና አለመረጋጋቶች በሁሉም ክልሎች ላለፉት ሰባት አመታት ቀጥለዋል፡፡
በትግራይ ክልል ብልጽግና የትም ሃገር ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የውጭ ሰራዊትን ጭምር በመጋበዝ በራሱ ሃገር ዜጎች ላይ ሞትን እና የተራዘመ ስቃይን አውጇል፡፡
ቀጥሎም በአማራ ክልል መሰረታዊ የህልውና ጥያቄ በመያዝ ጥያቄያቸው እንዲመለስ በሰለማዊ እና ፖለቲካዊ መንገድ በተራመዱ ዜጎች ላይ የለመደውን የፍረጃ ቅጽል ከመስጠት ማለትም ‹ጽንፈኛ፣ ጃዊሳ› ከማለት አልፎ ኢትዮጵያን እና ህዝቧን አደኽይቶ በገዛቸው ከባድ መሳሪያዎች ዒላማውን ንጹሃንን በማድረግ በጅምላ እየገደለ ይገኛል፡፡
ይህ አገዛዝ ላለፉት ሰባት አመታት ለኦሮሚያ ህዝብም አንድም ቀን ሰላም ሰጥቶት አያውቅም፡፡ የሚፈጸሙ ግድያዎችን በኦሮሞ ወጣቶች እና አገዛዙን ሚቃወሙ የኦሮሞ ልሂቃን እና ፖለቲከኞች ላይ ያለምንም ተጨባጭ ማስረጃ በማላከክ የኦሮሞ ህዝብ ወደ እርስ በእርስ ግጭት እንዲገባ እና በሌላ ብሄር ተወላጆች ዘንድ እንዲጠላ የተቀናጀ ተግባር በመንግስት ሃይሎች ሲፈጸም ቆይቷል፤ እየተፈጸመም ነው፡፡
ብልጽግና ትናንት በራሱ ዜጎች ላይ ላቀደው እኩይ አላማው አጋዥ ይሆን ዘንድ ውል አልባ ግለሰባዊ ግንኙነት መስርቶ ከነበረው የኤርትራ መንግስት ጋር ምክንያቱ በማይታወቅ መልኩ ግንኙነቱ በመሻከሩ የግል ጸብን ወደ ሃገር በማምጣት በተለይ ለሰሜኑ ህዝብ ዳግም የእልቂት እና የጥፋት ድግስ ደግሶለታል፡፡
ለአብነት እነዚህን ጦርነቶች ብቻ አነሳን እንጂ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት እና ግጭት የሌለበት ቦታ አለ ለማለት አይቻልም፡፡
ብልጽግና ከህወሓት መሩ ኢህአዴግ በብዙ እጥፍ ድርብ ያስከነዳ ዘረኝነትን፣ ሙስናን እና የእኔ ብቻ ባይነት ባለቤት ነው፡፡ በሃገራችን ረጅም የስርአተ-መንግስት ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የእርስ በእርስ ግጭት በሀገሪቱ ውስጥ እያካሄደ ነው፡፡ የዜጎችን ህይወት ማክበርም ማስከበርም አልቻለምም አልፈለገምም፡፡ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ የሰውነትም ሆነ የዜግነትም መብት ቅንጦት ወደመሆን ወርዷል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ እና በተለያዩ የክልል ከተሞች መንገድ ለማስፋት (የኮሪደር ልማት) በሚል እድሜ ልኩን ለፍቶ ከገነባው ቤቱ እና ማህበራዊ ህይወቱ ባልተገባ መልኩ እንዲፈናቀል ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በተደራጀ እና በተቀናጀ ሁኔታ የአዲስ አበባ ተወላጆች ከመዋቅር እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑ የአደባባይ ሃቅ ነው፡፡ ከአማራ ክልል የሚመጡ ዜጎችም ሃገራቸው እና መብታቸው ሆኖ ሳለ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ ስለመከልከሉ የታየና የተሰማ እውነት ነው፡፡
አገዛዙ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚገፉ የውጭ ፖሊሲዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በመቀበሉም የአገሪቱ ኢኮኖሚ በእጅጉ እንዲያሽቆለቁል ከመሆኑም በላይ ከዚህ ቀደም መካከለኛ ገቢ የነበራቸው ዜጎች አሁን በልተው ማደር የማይችሉበት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ አድርጓል።
ዲፕሎማሲን በተመለከተ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነበራትን ከፍተኛ ተሰሚነት በዘመኗ ሙሉ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እዲላሽቅ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ቀደም አፍሪካን እንዲሁም ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን በተመለከተ መንግስታትን ታማክር ጭምር የነበረች ኢትዮጵያ ዛሬ ተሰሚነቷ ምን ላይ ነው የሚለውን ጥያቄ መልስ ለህዝቡ እንተወዋለን፡፡
የኢትዮጵያውያን ብሄራዊ ምልክት የሆነውንና በድንቅ የዲፕሎማሲ ጥበብ ግንባታው 67 በመቶ ደርሶ የነበረውን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ‹የተገነባው ለፖለቲካ ትርፍ ነው› በማለት በማንኳሰስ የመላው ኢትዮጵያውያንን ልብ ሰብሯል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ደምና ላባቸውን ሳይሰስቱ መስጠታቸውን በንግግራቸው ክደዋል፡፡ ይህንንም ከሰሞኑ የአሜሪካው ፕሬዘዳንነት አሜሪካ ለግድቡ ከፍተኛ እርዳታ አድርጋለች በማለት ለሰጧቸው ተከታታይ መግለጫዎች ምላሽ ባለመስጠት ገፍተውበታል፡፡
ኢሕአፓም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምልክት የሆነው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን ደምና ላብ ብቻ የተገነባ መሆኑን ያምናል፡፡ አሁን በስልጣን ላይ ያለው ብልጽግና በድርጊቶቹ በግድቡ ህልውና የተደራደረ በመሆኑ ያለውን አጠቃላይ ሂደት ለኢትዮጵያ ህዝብ የመሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡ የግድቡ አርማ የሆኑት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ገዳይም በገለልተኛ አካላት ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ እንዲደረግ በጽኑ እናሳስባለን፡፡
ወደብን በተመለከተ ብልጽግና እየሄደበት ያለው ያልተገባ እና ህገወጥ አካሄድ ኢትዮጵያ ያላትን ህጋዊ እና ተገቢ የወደብ ጥያቄ ተገቢነቱን በዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ጥያቄ ውስጥ ከትቶታል፡፡
በአጠቃላይ ብልጽግና ላይ የሚስተዋለው የጦረኝነት እና የማን አለብኝነት መንፈስ ለዘመናት ታፍራ እና ተከብራ የኖረችው ኢትዮጵያ የመፍረስ አደጋ እንዲጋረጥባትና ኢትዮጵያውያንም የዜግነት እና የሰውነት ክብራቸው እንዲገፈፍ ምክንያት ሆኗል፡፡
ሕዝብም ካልተደራጀ እና ለመብቱ መታገል ካልጀመረ እንደእስካሁኑ ሁሉ የሉዓላዊ የስልጣን ባሌትነቱን እና የዜግነት እና የሰውነት ክብሩን መጠበቅ እንደማይችል ተደጋግሞ የተረጋገጠ በመሆኑ ሕዝቡ ለመብቱ በአንድነት መቆም እንዲጀምር ኢሕአፓ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
የብልጽግና መንግስት ለፖለቲካዊ ጥያቄዎች ወታደራዊ ምለሽ መስጠትን፣ ጦርነትን እዚህም እዚያም መጣድን፣ ንጹሃንን የጦርነት ዒላማ ማድረግን እንዲያቆም ኢሕአፓ በጽኑ ያሳስባል፡፡ ያለምንም ቅድመ ሁኔታም ጦርነቶችን እንዲያቆም እናሳስባለን፡፡
ኢሕአፓ ተቃዋሚ በመሆናቸው፣ በፖለቲካ አመለካከታቸው እና በማንነታቸው ምክንያት ለአመታት በግፍ እስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና ዜጎች በአስቸኳይ እንዲፈቱም ያሳስባል፡፡
የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ግድ ይለናል የሚሉ ዓለም ዓቀፍ ተቋማትና ወዳጅ አገራትም በዚህ ወሳኝ የሰላማዊ ትግል ምዕራፍ ወቅት ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያውያን ጎን በመቆም አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
በኢትዮጵያ እና በህዝቧ ተደራድሮ የማያውቀው ኢሕአፓ ከዛሬ ጀምሮ ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ለኢትዮጵያውያን ነጻነት፣ እኩልነት እና ስለፍትህ የሚያደርገውን ሰላማዊ ትግል አጠናክሮ እንደሚቀጥል ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ቃል ይገባል፡፡
ድል ለኢትዮጵያውያን!!!
ሃምሌ 16 ቀን 2017 ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ





