raya
News

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ, ሰሚ ላጣው የራያ ጩኸት የፍትሕ ያለህ!! – ደጄኔ አሰፋ

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የአክሱም ያልተጠበቀ ጉብኝት የተሰጠው ሽፋን የከተማዋ ነዋሪዎች የአክሱም ሐውልት ተጎዳብን የሚል አቤቱታ ነበር።የለገጣፎ ተፈናቃዮች፣የራያ እና የወልቃይት ሕዝብ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጩኸቶችን ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አልሰሙም።ጉዳዩን ያስተባብራሉ የተባሉ፣ጥያቄውን ያነሱ ብቻ ሳይሆን የአማርኛ ሙዚቃ ሰማችሁ፣ትግርኛ ቲቪ አላይም ብላችሁዋል የሚል ክስ እና ማንገላታት፣ድብደባና እንግልት ዛሬም አልቆመም።

ከአክሱሙ ጉዞ በሁዋላ ሕወሓት ተሳዳጅ ሳይሆን ከኦዴፓ ጋር በፈጠረው እንደ ግን ፍቅር እንደገናን የፓለቲካ ጨዋታ በዘረፈው፣በገደለው አስሮ ባሰቃየው ሊጠየቅ ቀርቶ በዚያ ድምጻቸውን ሲያሰሙ የነበሩ እየተሳደዱ ነው። ከሰኔ 15 በፊት የነበረውን የፓለቲካ እሳቤ ግንዛቤ ውስጥ በመክተት ይመስላል ዛሬም የራያ የሕዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሰሚብያለህ ሲሉ ይጣራሉ።

የራያን ሰሚ ያላገኘ ጩኸት እነሆ ምን አልባት ሕዝብ ሰሚ ማጣቱን እንዲገነዘብ ይሆናል።ያንብቡት ሼር ያድርጉት

የዶ/ር ዓብይ መንግስት….
.
መቼም በራያ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን አሰቃቂ ግፍ ለመግለፅ ትልቅ አቅም ይፈልጋል። “ኧረ የፍትህ ያለህ?” ብንልም ሰሚ የለም። ሰሚ አለማግኘት ደግሞ ሌላ ህመም ነው! የማይነጋ ጨለማ!
.
ትህነግ በራያ ንፁሃን ዜጎች ላይ ያለከልካይ የሚፈፅመው ኢሰብአዊ ድርጊት ዛሬም አላባራም። ትህነግ ከማዕከላዊው መንግስት በራቀ ልክ እልሁን የሚወጣው በራያ ህዝብ ላይ ነው። ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከትህነግ ጭቆና ተላቆ አንፃራዊ እረፍት ያገኘ ሲሆን የራያ ህዝብ ግን አሁንም የትህነግ የግፍ ማራገፊያ ወደብ ሆኖ ብቻውን የመከራ ፍዳውን እየበላ ይገኛል።
.
ከአምስት ወር በፊት የትህነግ ልዩ ሃይሎች #ሰላም_ደሳለኝ የተባለች የራያ ወፍላ ታዳጊን ለሰባት ሆነው በመድፈር ልጅቱ ከአካላዊ ጉዳት በተጨማሪ ለአእምሮ ህመም (ለእብደት) ተዳርጋ እንደቀረች የሚታወቅ ነው። የእህታችን ጠባሳ ሳይሽርልንና በመንግስት ዝምታም እጅግ አዝነን ባለንበት በዚህ የመከራ ወቅት ይሄው በሃምሌ 20/2011 ቅዳሜ ምሽት በራያ አላማጣ ጅሃን አካባቢ (ስሟን መጥቀስ ለህልውናዋ ስል አልጠቅሰውም) የ16 አመት ታዳጊ ልጅ በ4 የትህነግ ልዩ ሃይሎች ተደፍራለች። ከደፈሯት በኋላም ሰውነቷን በምላጭ በመተልተል ጭካኔ የተሞላበት ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ፈፅመውባታል። ለሶስት ቀናት ደብቀዋት ከከረሙ በኋላ በቤተሰብ እና በህዝቡ ፍለጋ ተገኝታ ወደ ቤተሰቧ ተመልሳለች። በዚህ ወንጀል አንዲት #ሴት የልዩ ሃይል አባል በትልተላው ተባባሪ የነበረች ሲሆን ለጓዶቿ ስትል በድርጊቱ መተባበሯም ታውቋል። የልጅቱን ሰውነት የተለተሉበት ምክንያት፥ መደፈሯ ሳይታወቅ በደም መፍሰስ እንድትሞት ነበር። ሆኖም ግን ትረፊ ያላት ነፍስ በህይወት ተርፋ የደረሰባትን አሰቃቂ ለቤተሰቡ እያለቀሰች መተንፈስ ችላለች።
.
በ1997 ዓ.ም ተሻሽሎ በወጣው የኢፌዲሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 520 እና ተከታይ አንቀጾቹ መሰረት የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እስከ ሞት ቅጣት ድረስ ያስቀጣል። የአስገድዶ መድፈር የተፈጸመባት/በት ግለሰብ የእድሜ ትንሽነት/ህጻንነት፣ የአካል እና የእዕምሮ ጉዳት ታይቶ ቅጣቱ እየከበደ በመሄድ እስከ ሞት ፍርድ ይደርሳል ይላል የወንጀል ህጉ። በአንድ የክልል ልዩ ሃይል እንዲህ ዓይነት አሰቃቂ ድርጊት ሲፈፀም ደግሞ ቅጣቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ይቻላል። ታዲያ ምን ያደርጋል የፌደራል መንግስት በራያ ወረዳዎች የህግ የበላይነትን ማስከበር ቀርቶ የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ተቀዳሚ ህገ መንግስታዊ ግዴታውንስ መች ተወጥቶ ያውቃል?!? የራያ ህዝብ ቢገደል፣ ቢታፈን ፣ ቢፈናቀል አልያም አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ቢፈፀምበት ማንስ ይታደገዋል?!?
.
የዶ/ር አብይ መንግስት የራያን ህዝብ የመረረ ጩኸት ፥ በደልና ግፍ የሚመለከትበት ግዜ እጅጉን ይናፍቃል!!! የመከላከያ ሰራዊት ከቶ ወዴት አለህ? የሰላም ሚኒስቴር የራያን ህዝብ ሰቆቃ የሚሰማበት ጆሮ የለውምን? የሴቶች እና ህፃናት ሚኒስቴር የራያ ሴቶችና ህፃናትን እንደ ዜጋ ቆጥሮ በአገልግሎቱ ተደራሽ ማድረግ ለምን ተሳነው? የጠቅላይ አቃቤ ህግ ተግባር እና ድርሻ የራያን ህዝብ አያካትት ይሆን? የፌደራል ፖሊስ በራያ ወረዳዎች እንዳይገባ ማን ነው የከለከለው?!?
.
እናንት ባለስልጣናት ይህች የተደፈረችው ታዳጊ የእናንተ ልጅ ብትሆን ምን ይሰማችሁ ይሆን?!? መች ይሆን ፍትህን በራያ ላይ የምታሰፍኑት? የራያ ህዝብ ኢትዬጵያዊ አይደለንምን? ኧረ የፍትሕ ያለህ!!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *