News Politics

የዴሞክራሲያዊ መብቶችን በሚያፍነው የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ ሕግ ላይ ከ57 የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሰጠ የጋራ መግለጫ፣

የኢትዮጵያ ህዝብ በያለበት ሆኖ በተደራጀም ሆነ ባልተደራጀ መልኩ ስለመብት እኩልነትና ነፃነት ጥያቄ ማንሳት ከጀመረና ለሰላም፣ ለፍትህና ለዴሞክራሲ መታገል ከጀመረ ረጅም ዘመናትን አስቆጥሯል፡፡ ይህ የረጅም ሂደት የህዝብ ትግል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሔድ ከውስጡ የሕዝብን ጥያቄ አንግበው የሚታገሉ በርካታ የትግል ሀይሎችን ሊወልድ ችሏል፡፡ እነዚህ በሕዝቡ የመብት፣ የነፃነትና የዴሞክራሲ ትግልና ጥያቄ ውስጥ ተፀንሰው የተወለዱ የትግል ሀይሎችና ታጋዮች በየደረጃው ከሕዝብ ጎን በመሰለፍ የሕዝብን የእኩልነት፣ የነፃነት፣ የሰላም፣ የፍትህ፣ የዴሞክራሲና የልማት ጥያቄን አንግበው ለረጅም ዘመናት ሲታገሉ ቆይተዋል፡፡

ይህ በሀገራችን በዚህ መልኩ ሲካሔድ የቆየው ትግል መላው የትግል ሀይሎችም ሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚያውቀው ለሀገራችንና ለሕዝባችን የተሻለ እኩልነትንና ነፃነትን ለማምጣት፣ የተሻለ ሰላምና ፍትህን ለማስገኘት እና ግልጽና አስተማማኝ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለማምጣት የተደረገ ትግል ነው፡፡ ይህ መላው ሕዝብም ሆነ የዴሞክራሲያዊ ሀይሎች የታገሉለት፣ መስዋእትነት የከፈሉለት፣ የሞቱለትና ሲቃይና መከራ የተቀበሉለት ትግል ዋናው ምክንያት የእኩልነት፣ የነፃነት፣ የሰላም፣ የፍትህና የዴሞክራሲ ጥያቄና ዓላማ ነው፡፡ በመሆኑም በመላው ሕዝብና በዴሞክራሲያዊ ሀይሎች በተደረገው እልህ አስጨራሽ ትግልና በተከፈለ ከፍተኛ መስዋእትነት በሀገራችን አሁን ያለው ለውጥ ሊመጣ ችሏል፡፡

በእኛም በኩል ይህ በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብና በዴሞክራሲያዊ ሀይሎች ትግልና መስዋዕትነት የመጣው ለውጥ እውን መሆን ከጀመረም በኃላ ለውጡ እንዳይቀለበስና ተጠናክሮ እንዲቀጥል፤ የለውጡ ሂደት ግልፅነትን የተላበሰ እንዲሆን፣ የለውጥ ሀይሉም ሆነ መላው ሕዝብ ለሰላም፣ ለፍትህና ለዴሞክራሲ እንዲቆም በማበረታታት ያለማቅማማትና ያለመጠራጠር ከለውጥ ሀይሉ ጎን ቆመን የበኩላችንን አስተዋፅኦ ስናበረክትና ስንደግፍ እንደነበርን ግልጽ ነው፡፡ ይህንንም በመጋቢት ወር በ2011 ዓ ም በጋራ በፈረምነው የጋራ ቃል ኪዳን ሰነድ አረጋግጠናል፡፡ ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ከለውጥ ሀይሉ ጎን በመሰለፍ በተደጋጋሚ ድጋፍ ሰጥተናል።

በአሁኑ ጊዜ ለውጡን እየመራ ያለው የፖለቲካ ሃይል፣ መንግስትና የመንግስታዊ አካላት በሚያዘጋጁት ልዩ ልዩ መድረኮች የህግና የፍትህ ጉዳዮች ማሻሻያ ምክር ቤት በሚያዘጋጃቸው መድረኮች በመሳተፍ አስተዋጽኦ ስናበረክት ቆይተናል። በዚህም ለሀገራችን የለውጥ ሂደትና ለለውጥ ሀይሉ ጠቃሚና ገንቢ የሆኑ ሃሳቦችን አቅርበናል ብለን እናምናለን፡፡ እንዲሁም እያንዳንዱ ፓርቲ በግልም ሆነ እንደ ቡድን በመሰባሰብ ሃሳብ እንዲያቀርብ በተጠየቅንባቸው ልዩ ልዩ መድረኮች ላይም ለለውጡ ካለን ድጋፍና ፍላጎት የተነሳ ለሀገርና ለሕዝብ የሚጠቅሙና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው ጠቃሚና ገንቢ የሆኑ ሀሳቦችን በቃልም ሆነ በጽሁፍ ስናቀርብ ቆይተናል፡፡ ሁሉን የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚያሳትፍ የጋራ ምክር ቤት ሲቋቋምም በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሃሳባችንን የምናራምድበት ተጨማሪ የጋራ መድረክ በመሆኑና የፓርቲዎችን የጋራ ጉዳይና ሀሳብ ሊወክል የሚችል ተቋም ይሆናል ብለን ስላመንን ድጋፍ ሰጥተን ከሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ሆነን አቋቁመናል፡፡

ይሁን እንጂ፣ “የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕግ” ረቂቅን በሚመለከት፣ እኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያየ ጊዜያት በመንግስት ለተቋቋሙ አካላትና ተቋማት፣ በተለይም ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድና ለሕግ ማሻሻያ ምክር ቤት ጭምር በቃልና በጽሁፍ ያቀረብነው ሀሳብ ወደ ጎን ተገፍቶ፣ የኛ ሃሳብ ታፍኖ፣ አብዛኛዎቻችን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያልተስማማንበት ሃሳብ እንደተስማማንበት በማስመሰል ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኩል አድርጎ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበው የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ህግ ረቂቅ በሀገራችን ውስጥ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት የሚቀለብስ፣ ዴሞክራሲያዊ መብትን የሚገድብ፣ የመደራጀት መብትን የሚያፍን እጅግ ኋላቀርና እንከነ-ብዙ በመሆኑ የፖለቲካ ምህዳሩንም አደጋ ላይ የሚጥል ሆኖ አገኝተነዋል። የምርጫ ቦርዱ የተቋቋመበት ሕግ፣ ገና ከፀደቀ ሶስት ወራትን ሳያስቆጥር ነው በተግባር የተጣሰው። በማቋቋሚያ ሕጉ ገለልተኛ ሆኖ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያወያያል የተባለው የምርጫ ቦርድ፣ የረቂቅ ሕጉ አቅራቢና ተከላካይ ሆኖ ቀርቧል።

በተለይም በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስተባባሪነት የተቋቋመው የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ይህን በዜጎች መብትና ነፃነት እና በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው ሂደት ላይ ግልጽና ቀጥተኛ አደጋን በደቀነው የህግ ረቂቅ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሰብስቦ ማወያየትና ሀሳባቸውን በማድመጥ ለሚመለከተው ክፍል ሊያቀርብ ሲገባው ይህን አለማድረጉ ሲታይ በሁሉም በኩል የነበረን እምነት እንዲሸረሸር አድርጓል፡፡

ስለሆነም አሁን ለምክር ቤት የቀረበው የህግ ረቂቅ በድጋሜ ለፓርቲዎች ውይይት ቀርቦ ፓርቲዎች የሚመክሩበት ሁኔታ እንዲፈጠር ሀምሌ 25 ቀን 2011 ዓ ም በሰጠነው መግለጫ ግልጽ ጥያቄ አቅርበናል። በተጨማሪም ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለህግና ለፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተለያየ መንገድ ጥያቄዎችን አቅርበናል፡፡ ሆኖም ለምናቀርበው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥም ሆነ ሀላፊነት የሚወስድ አካል ማግኘት አልተቻለም፡፡ ስለዚህ እኛ በሀገራችን በሰለማዊ መንገድ ተደራጅተን በመንቀሳቀስ ላይ የምንገኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚሻሻሉ ልዩ ልዩ የህግ ጉዳዮች ላይም ሆነ በሌሎች ሀገራዊና ሕዝባዊ ጉዳዮች ላይ ያለንን ሀሳብ እና የምናቀርበውን ጥያቄና ቅሬታ በተመለከተ፡-

1ኛ. መንግስትና የመንግሥት ሥልጣን የያዘው ገዥው ፓርቲ የአግላይነትና ገፊነት አካሔዳቸውንና አሰራራቸውን አቁመው ጥያቄያችንን በማድመጥ ፈጣንና ተገቢ ምላሽ እንድሰጠንና አጠቃላይ ባሉን ጥያቄዎች ላይ ግልጽ የሆነ የውይይት መድረክ እንዲፈጠር እንጠይቃለን፡፡

2ኛ. በአሁኑ ወቅት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ ህግ ከመጽደቁ በፊት ለፓርቲዎችና ለሕዝብ ውይይት ክፍት እንዲሆንና በህጉ ረቂቅ ላይ ፓርቲዎች ያቀረቡትና የሚያቀርቡት የማሻሻያ ሀሳብ በተገቢው መንገድ መካተቱን የምናረጋግጥበት መድረክ እንዲፈጠር እንጠይቃለን፡፡

3ኛ. መንግስት ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ ውስጥ በነበረው የዴሞክራሲ መብት መታፈን ምክንያት የተዳከሙ የዴሞክራሲያዊ ሀይሎችን እንቅስቃሴ ለማጎልበትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደቱን ለማገዝ ለፓርቲዎች አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ አደርጋለሁ ሲል ለሕዝብም ሆነ ለዴሞክራሲያዊ ሀይሎች በግልጽ የገባውን ቃል እንዲያከብርና በተግባርም እንዲፈጽም እንጠይቃለን፡፡

4ኛ. የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር፣ ክቡር ዶክተር ዐብይ አህመድ፣ ህዳር 18 ቀን 2011 ዓ.ም.፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ስብሰባን በከፈቱበት ቀን፣ አብረን በመነጋገር የሀገራችንን ሠላም ለማምጣትና ዕድገትዋን ለማፋጠን፣ “ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ የማናሻሽለው ነገር አይኖርም” ሲሉ የገቡትን ቃል እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩልን በአጽንዖት እንጠይቃለን።

5ኛ. መንግስትም ሆነ መንግስታዊ አካላት የዜጎችን መብትና ነፃነትን ከሚገድብ እንቅስቃሴ፣ የሕዝብን፣ የብሔር ብሔረሰቦችንና የማሕበረሰቦችን መብትና እኩልነትንከሚጥስ ተግባር፣ የዴሞክራሲያዊ ስነ ምህዳሩን ከሚያጠብ እርምጃ፣ የዜጎችንና የሕዝቦችን በነፃነት መደራጀት፣ ተደራጅቶ የመንቀሳቀስ፣ ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትና ነፃነትን ከሚጥስ ማንኛውም አይነት ተግባርና ሂደት ተቆጥበው የተጀመረው ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ሳይሸራረፍ ግልጽ፣ አሳታፊና አካታች ሆኖ እንዲቀጥል እንዲያደርግ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

ሰላም፣ ክብርና አንድነት ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ይሁን!!!

የአስተባባሪ ኮሚቴው ነሀሴ 17 ቀን 2011 ዓ ም

አዲስ አበባ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *