warning
Opinion

ይድረስ ለዶ/ር አብይ መሀመድ (እጂግ አሳሳቢ ጉዳይ)

ሰመረ አለሙsemere.alemu@yahoo.com

በእርግጥ ታስቦበት ይሁን የዶ/ር አብይ ይሁንታ ተጨምሮበት አገራችን ላይ ብዙ ተስፋዎች መክነዉ ከአንድነት ይልቅ ትርምስ ሀገር በእዉቀትና በጥበብ ከመመራት ይልቅ ለኢትዮጵያ በማይመጥኑ ደካማ ምስለኔዎች አማካይነት አንዴ ወደግራ አንዴ ወደቀኝ እየተናጠች ዛሬ ላይ ደርሳለች። ዶ/ር አብይ  አጀማመራቸዉ  በኢትዮጵያዊነት  የተቃኙ ለመሆኑ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ በማለት ፍንጭ ስላሳዩ በሀገርም ከሀገር ዉጭም የተሰጣቸዉ ድጋፍ እስከዛሬ ካየናቸዉ መሪዎች የገዘፈ ነበር። ታዲያ ምን ይሰራል ብዙም ሳይቆይ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ከ60ዎቹ ጀምሮ ኢትዮጵያን ሲያተራምሱ የኖሩ የኢትዮጵያና የአንድነት ጠላቶችን በወንጀል የሚፈለጉ አዛዉንት ቄሮዎችንና ጁዋር መሀመድን እስከ ጥላቻ መንዣ መሳሪያዉ (ኦ ኤም ኤን) አስይዘዉ ወደ ሃገር ቤት በክብር አስገቡ።

በእርግጥ የችግራችን ሁሉ መሰረቱ ፈረንጂ ለሻቢያ፤ ሻቢያ ለወያኔና ለኦሮሞ ነገድ ታጋይ ነን ለሚሉት የመመሪያ ሰነድና መሳሪያ  በመስጠቱ ሲሆን ለዚህ ማምከኛ በኛ በኩል በበቂ ባለመሰራቱ ችግሩ ተጠራቅሞ ዛሬ ላይ ፍዳችንን እያበላን ዉሉ ጠፍቶን ቁጭ ብለናል።  ዛሬ ህወአቶች  የጥጋባቸዉ ማእክል የሆነዉን አዲስ አበባን የበረቱት ጥለዉ ሲሸሹ  የቀሩት ደግሞ ጥላቸዉን እየሸሹ በቀን ቅዠት ላይ ይገኛሉ።

ይህንን  በዚህ ላይ አንጠልጥዬ  ልተወዉና ዛሬ እረፍት የነሳኝ የግብጾች በአባይ ዙሪያ የሚያደርጉት ጫናና  አመራሩ፤ ምሁራንና፤ ህዝባችን  ለዚህ ታላቅ ነገር በቂ ዝግጅት ያለማድረጉና ለጉዳዩም ትኩረት ባለመስጠቱ  ነዉ።  መለስ ዘራዊ የአረብ ሀገራት ነዉጥ አካባቢዉን ሲያተራምሰዉ በመመልከት  በዉርደት ጆሮዉን ተጎትቶ መዉረዱ የማይቀር መሆኑን በመገንዘብ የህዝቡን ተቃዉሞ ለማለዘብና በተነሳዉ የተቃዉሞ ትግል ላይ ዉሀ ለመቸለስ  በዉኑ አስቦት የማያዉቀዉን ፐሮጀክት አባይን እገነባለሁ ብሎ በመለፈፉ ኢትዮጵያዉያን  በአንድነት አባይ ላይ ተረባርበዉ ፕሮጀክቱን ለማሳካት ትልቅ ጥረት አድርገዉ ነበር።በዚህ ክስተትም ታላቁ ኢትዮጵያዊ ኢንጂነር ስመኝም ህይወቱን ገብሮ ስለ አሟሟቱም በኮሚሺነር ዘይኑ ጀማልና ዶ/ር አብይ የሚያሳዝን መግለጫ ተሰጥቶበታል። እንደዉ ማ ይሙት ሰዉ ለመሞት ለመሞት ቤቱ አይሻለዉም መስቀል አደባባይ ሂዶ ከመሞት?

ከዚህ በላይ ያተትኩት እንደ መንደርደሪያ ታይቶልኝ የዛሬዉ የጽሁፌ ማጠንጠኛ የአባይ ድርድርን  በተመለከተ ይሆናል። ማንኛችንም እንደምናዉቀዉ ዉሃን ለግብጽ የምትሰጠዉ ኢትዮጵያ ሁና ሳለ ግብጽ እንዲህ መላ ቅጡን ስታጣ አመራሩ  የኢትዮጵያ ተስፋ ስለሆነዉ የሀገር ሀብት ብዙም ያሳሰበዉ አይመስልም። ዶር አብይ አባይን አስመልክተዉ የጦር፤የኢኮኖሚ፤የታሪክ፤የሳይኮሎጂ አማካሪዎችን ሰብስበዉ ሲመክሩም ለህዝቡም ስለ ሁኔታዉ የእለት ተእለት መረጃ ለመስጠት ሲጨነቁም አይታዩም። ባንጻሩ የግብጹ መሪዎች ይህንን ፕሮጀክት ለማጨናገፍ ከጅምሩ ጀምሮ ያልወረወሩት ድንጋይ የለም። ኢትዮጵያ ነገር ሁሉ ተዘጋግቶባት ወደብ የማግኘቱንም ተስፋ በራሳቸዉ በዶር አብይ ከጨለመ በሗላ ብቸኛዉ ጠቀም ያለ ገቢ የምናገኝበትና ለሀይል ፍጆታ የምንጠቀምበት አባይ መሆኑ እየታወቀ እንዲህ ያለ ለዘብተኛ አቋም መዉሰድ ትንሺ ግራ ያጋባል።

ኮለኔል መንግስቱ ጠበቅ ጠበቅ ያለ የጦር መሳሪያ ማምረት ከጀመሩ በሗላ በኢትዮጵያዊ ወኔ “በገዛ ወንዜ ያሻኝን ባደረግ አዛዥ ናዛዢ የለብኝም” ያሉትን ምን ብንጠላቸዉ እዚህ ላይ መጥቀሱ ግድ ይላል። በኢትዮጵያ ጠላቶችና መድረሻቸዉን ባላወቁ በኢትዮጵያ ተማሪዎች ባይዋከቡ ኑሮ  አባይን የኢትዮጵያ ያደርጉት ነበር የሚል እምነትም አለ። መለስ ዜናዊም  በአሜሪካ ቴሌቭዢን ስለ ግድቡና የግብጽ ዛቻ ተጠይቆ ሲመልስ “ግብጾች ጦርነት እንሞክራለን ካሉ አብደዋል ማለት ነዉ ህክምና ያስፈልጋቸዋል” ነበር ያለዉ ቃል በቃል።  የሲነን ክሊፕ ወደ  ሗላ መልሶ መመልከትም ይቻላል።ታዲያ የትላንት መሪዎች በተጨናነቀ ሁኔታ አባይን አስመልክቶ እንዲህ ጠንከር ያለ አቋም ሲወስዱ ያሁኑ አመራር ግን ለዘብተኝነቱ ከምን የመጣ ሊሆን ይችላል?

ባለፉት ጊዜያት ገንጣይና አስገንጣይ  በመተባበር  ኤርትራ በወንበዴዎች ጫና ተገንጥላ ሄደች ኢትዮጵያም ያለወደብ ቀረች።ስዩም መስፍን በኤርትራ ድምበር ዉዝግብ ሻቢያ ያልጠየቀዉን መሬት ሁሉ በመስጠቱና የአልጄርሱ ዉሳኔ ይግባኝ የሌለዉ ነዉ ብሎ ብሎ መለስ ዜናዊ በመፈረሙ ኢትዮጵያም በታሪካዊ ጠላቶችዋ በመወከሏ ሻቢያ ያላሰበዉን መሬት ተረክቦ ስዩም መስፍንም ባዶ እጁን ተመለሰ።፡ይህ እፍረት የሌለዉ ሰዉ በቴሌቭዢን ቀርቦ ደስ ይበለን ከጠበቅነዉ በላይ ተሰጥቶናል ብሎ የኢትዮጵያን ህዝብ ቀጠፈ። አሁንም እንዲህ ያለ አሳፋሪ ስምምነት ላይ ይደረሳል ብለን እንሰጋለን።

ኢህአፓ የብሄራዊ ጥቅማችንን ከግምት ሳያስገባ በሗላ የሚደርሰዉን ንትርክ አቆይቶ ለሀገር ጥቅም ባለመቆሙ  ጅቡቲን የኢትዮጵያ አካል ለማድረግ  የነበረዉ ተስፋ በጥቂት ሀገር በቀል አራሙቻዎች በመደናቀፉ ኮለኔል መንግስቱ  የጅቡቲን መንግስትነት እቀበላለሁ ብለዉ እዉቅና በመስጠታቸዉ ጅቡቲ የኢትዮጵያ አካል ሳትሆን ቀረች። ዛሬ ትዉልዱ ጂቡቲ የኢትዮጵያ ግዛት መሆንዋን የሚያዉቀዉ ስንቱ እንደሆነ ማወቅ ይቸግራል። እድሜ ለመለሰ ዜናዊ በነጻነት ስም ትዉልዱ አካባቢዉን እንደ ሀገር በመቁጠር  እራሱ ላይ ቆልፎ አጠና እየመዘዘም መጨፋጨፍ ይዟል።ዛሬ ግብጾች ባለሐይላቸዉ በመጠቀም የአባይ ጉዳይ በፈለጉት መንገድ እንዲሄድ ያለመታከት አለማቀፍ ጫና በማድረግ ላይ ናቸዉ። በሐገር ዉስጥም የነጁዋር መሀመድ፤ የኢዝላሚስትን፤ የኦሮሞ ጽንፈኞችን እንቅስቃሴ ሙሉ ድጋፍ እንደሚሰጡ በሚንሰተሮቻቸዉ ዉይይት ላይ በቀጥታ በሚሰራጭ  ስብሰባ ላይ ከሞላ ጎደል ተመልከተናል። ጁዋር መሀመድም  ዶ/ር አብይ ሶቺ (ሩሲያ) ላይ ከአል ሲሲ ጋር ሲነጋገሩ ሀገር ቤት የሌለ ምክንያት ፈጥሮ ማስረበሹ ለግብጽ  ድምጽ ለመሆን በተግባር ያስመሰከረበት የረቀቀ የፖለቲካ አካሄድ እንደነበር ስለ ፖለቲካ ግንዛቤ ያለዉ ዜጋ ይረዳዋል

ግብጾች በአለም ባንክ በትላልቅ ተቋማት ከፍ ያለ ስፍራዎችን  ይዘዋል የአረብ ሀገርንም የሚያሺከረክሩት እነሱዉ ናቸዉ።  በአሜሪካ የገቢ ሰንጠረዥ 29% ግብጻዊ አመታዊ ገቢዉ በአማካይ 90000 ዶላር ሲሆን 17% ደግሞ 140000 ዶላር ነዉ  ግብጻዉያን እጅግ ትላልቅ ተቋማት ዉስጥ በሃላፊነት ይሰራሉ በአሜሪካ መንግስትም በተለያየ ደረጃ ከመስራታቸዉም በላይ የአለም ባንክን በመሳሰሉ ግዙፍ የፋይናንስ ተቋማት ዉስጥ በከፍተኛ ደረጃ አመራር ሰጭ አካላትም ናቸዉ። የግብጽ ህዝብ ክርስቲያን፤እስላምና አይሁድ ነዉ ነገር ግን ግብጽን በተመለከተ ከእኛ በተጻራሪ ማንኛዉም ግብጻዊ ለሀገሩ ጉዳይ ቅድሚያ ይሰጣል ተናንቆም ይሞታል። ለምሳሌ ኤርትራን አጣድፎ ከኢትዮጵያ የመገንጠል ፕሮግራም የተከወነዉ በቡተሮስ ጋሊ የኮፕቲክ ክርስቲያን እምነት ተከታይ አማካይነት ነዉ። ያለመታደል ሁኖ በእኛ በኩል ግን ከኢትዮጵያዊነታቸዉ ይልቅ አረብነታቸዉን የሚያልሙ አራሙቻዎች ከመሀል ሁነዉ በሀይማኖትና በጎሳ ስም ወገንተኝነታቸዉን ከግብጽና ከአረቡ አለም ጋር ያደርጋሉ።

በዶር አብይ የተለሳለሰ አካሄድ የኢንጂነር ስመኘዉ ግድያ፤ ተርባይኖቹ ከ4 ወደ 3 መቀነሳቸዉ፤ የዶ/ር አብይ ጉልበት የሌለዉና ጫና የማያሳደር እንቅስቃሴን አገጣጥመን ስናየዉ  በዚህ ጉዳይ ዳግም እንደ ባድሜዉ ሁሉ ቁማሩን መበላታችንን ያመለክታል። ሀገሪቱ በወደብ ማጣት ያጣችዉን ሀብት ሊያሟላልን የሚችለዉ ይህ የኢኮኖሚ ዘርፍ ሁኖ ሳለ ዶ/ር አብይ ለዜጎች በዚህ በኩል ያላቸዉን አቋም ማስረገጥ ያለመቻላቸዉ ኢትዮጵያዉያንን እረፍት ይነሳል። ዶር አብይ የኮሎኒያሊስቶችን ስምምነት የማክበር ግዴታ የለባቸዉም ዉሃን በተመለከተ እስራኤል ቱርክና ሌሎች አገሮች ቅድሚያ ለሀገራቸዉ ሰጥተዉ ዉሀቸዉን ለሃገራቸዉ ጥቅም ያዉላሉ የነሱም ታሪካዊ ዳራዉ ከእኛ የተለየ አይደለም።

አሁን የምናየዉ ሁኔታ ዶ/ር አብይ እርዳታ ፈላጊ አልሲሲ ሰጭ የሆነበት ሁኔታ በጠንካራ ድርደርና ዜጎችን ከጎን ባሰለፈ አቅጣጫዉን ማስለወጥና በኢትዮጵያ በኩል ሰጭ የመሆን ሳይኮሎጅን ግብጽ ላይ ማሳደር ካልተቻለ የወደፊቱን ትዉልድ ትልቅ ኪሳራ ላይ ይጥላል ኢትዮጵያም ከድህነት አረንቋ እድሜ ልኳን ተሰንቅራ ትኖራለች ። የዶ/ር አብይ መንግስት ሁሉን አዉቃለሁ  የሚለዉን አባዜ ትቶ ለሀገራቸዉ እረፍት የሌላቸዉን እዉቅ  ምሁራንን  እወቀትና ልምድ ያካበቱ ዜጎችን የታሪክና የዲፕሎማቲክ ጠበብቶችን በክብር ጋብዞ ማወያየት ግድ ይለዋል። ባካባቢያቸዉ  አረጋዊ በርሄ፤ዳዉድ ኢብሳ፤ሌንጮ ለታ፤ህዝቅኤል ጋቢሳ፤ዲማ ነገዎ፤ወርቅነህ ገበየሁ መሀመድ አዉሎን ሌንጮ ለታን  ….. የመሳሰሉ እይታቸዉ የተሰበሰበ ፍጡሮችን  ሰብስቦ አገር ላይ ከመቀለድ ይልቅ የሀይል ሚዛን ሊደፉ የሚችሉ እርሶ የተባሉ ምሁራንን ከሀገር ቤትና ከዉጭ ሀገር አሰባስቦ ለሀገር  ጥቅም ሲባል በዝግ ስብሰባ አንድ ዉሳኔ ላይ እነዲደረስ በአጽንኦት እንጠይቃለን።  ለዚህ ታላቅ ድርድር የድርድር ጥበብ የሌለዉ የአማራን መሬት ለትግሬ መርቆ የሰጠ ገዱ አንዳርጋቸዉ በአባይ ዙሪያ ጫና ያሳድራል ብሎ መገመት ሆነ ተብሎ ድርድሩ ከጅምሩ አንካሳ እንዲሆን ሆነ ተብሎ የተሸረበ ያስመስላል።፡የልኡካኑም ቡድን ዶናልድ ትራምፕ አጠገብ ተሸማቆ ሲቆም የግብጽ ልኡካን ግን ያሰቡትን ማግኘታቸዉን የሚያሳይ የፎቶ ሹትም ያሳያል ዛሬ ስዩም መስፍን በወንጀል እንዳልተጠየቀ ሁሉ ነገ እነዚህ ሰዎችም እንደማይጠየቁ ያዉቁታል ዛሬ አረጋአዊ በርሄ ከዚህ ሁሉ ወንጀሉ በሗላ በድፍረት ፓርቲ መርቶ ለዳግም ጥፋት እድል ይሰጠዉ ነበር?።

ኢትዮጵያ በዚህ ጉዳይ በአሜሪካም ሆነ በግብጽ ወይም በአረብ አገራት ጫና ምንም ፊርማ መፈረም አይኖርባትም ።የግብጽ ጭንቀት የዉሃዉ ጉዳይ አሳስቧት ሳይሆን ወደፊት ኢትዮጵያ ከተጠናከረች ዉሀዉ ላይ ጫና ማሳደር ትችላለች በሚል ስጋት ከወዲሁ ወጥሮ ለመያዝ የታቀደ የድርድር ጥበብ ነዉ።  ይህም ግብጾች ከ11ኛዉ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በፖሊሲ ደረጃ ሲተገብሩት የኖሩት አጀንዳቸዉ ስለሆነ ትዉልዱ የአባይ ጉዳይ አሁን አገር ቤት ካለዉ ከማንኛዉም ችግር የበለጠ መሆኑን ተገንዝቦ  በነገድ የሚጨፋጨፈዉ ትዉልድ ይህን ጉዳይ እንደ ብሄራዊ ጥሪ ተቀብሎ አጠናዉን አስቀምጦ ለሁኔታዉ መሳካት የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግ እንመክራለን። ዶ/ር አብይ እንደ ግብጽ መሪዎች ለሀገር በጽናት መቆምን፤ የመምራትና የመደራደር ብቃታቸዉንም ያሳዩን እንላለን። በተለሳለሰ ስምምነት ወደፊት ዉሀችን ላይ የአየር ንብረት በተለወጠ ጊዜ ወይም ደግሞ ኢኮኖሚያችንን ለማሳደግ ዉሀችንን ለመጠቀም በተፈለገ ጊዜ የዶክተር አብይ ስምምነት መሰናክል እነዳይሆንብን ስምምነቱን ክፍት አድርገዉ መተዉ ለወደፊቱ ትዉልድ የተሳካ ህይወት ወሳኝ ነዉ ብለንም እናምናለን። አሁን የምናየዉ ለግብጽ የተመቸ በሚመሰል መልኩ በግብጾች አጀንዳ ብቻ ተቀርጾ ስንነታረክ  ብልሆቹ ግብጾች ያገራቸዉን ሰዉና ኢትዮጵያ ዉስጥ ያሉትን ባንዳዎች በማሰባሰብ ያሰቡት ላይ እንደሚደርሱ ጥርጥር አይኖርም። ስምምነትን በተመለከተ ጂቡቲን፤ኤርትራን፤ያካባቢ ከተሞችንና፤ወደባችንን አጥተናል።

እዚህ ድርድር ላይ ነገር መንገዱን ከሳተ ተጎጅዋ ግብጽ እንጂ ኢትዮጵያ ያለመሆኗን ወገን ሊገነዘበዉ ይገባል። በወታደራዊ ታክቲክ ግብጽ ያላት ምርጫ  ከሀገሯ ተነስታ ወረራን ማካሄድ ነዉ ይህ ከቦታዉ እርቀት አንጻር በፍጹም የማይሞከር ሲሆን ። ሌላዉ አማራጯ ሱዳንን መጠቀም ነዉ የኢትዮጵያ አምላክ ምስጋና ይግባዉና የሱዳን ህልዉና እራሱ በኢትዮጵያ እጅ ላይ በመሆኑ ይህም ሊያሳስብ አይገባም። ሱዳን ተሳስታ ለግብጽ ወታደሮችና አየር ሀይሎች ቦታ ከሰጠች በእሳት መጫወት በመሆኑ አትሞክረዉም፤ የግብጽ አየር ሐይል ከግብጽ ተነስቶ ግድቡን አጥቅቶ ለመመለስ  ከቦታ እረቀት ምክንያት ባለመቻሉ ይህም ሊያሳስበን አይገባም፤ በመጨረሻ ያለዉ እድል  የኮማንዶ ቡድን አሰርጎ ግድቡን መምታት ይሆናል ኢትዮጵያ  እንዲህ ያለ ትልቅ ፕሮጀክት ስትቀርጽ በእዉቀት፤ በሰዉ ሀይል፤ በቴክኖሎጂ የታገዘ ጥበቃ ስለምታደርግ ይህም ተስፋዉ የተሟጠጠ ሙከራ ነዉ። ግድቡም ከተሞላ በሗላ ግድቡን ቢመቱትም ሱዳንና ግብጽ እራሳቸዉን መቱ ይባላል። በማንኛዉም መንገድ ኢትዮጵያ ደህንነቷ በአምላክ እርዳታ ቀደም ብሎ የተጠበቀ በመሆኑ ዶ/ር አብይ ከማማዉ ላይ ሁነዉ ለኢትዮጵያ በሚመች መልኩ መደራደሩ የሚያሳስባቸዉ ጉዳይ አይሆንም።

አልሲሲ ሶቺ ላይ በተደረገዉ ስብሰባ በምን አይነት ጭንቅ ላይ እንዳለ መገመት ይቻላል ዶር አብይ የግብጾችን የቀልድ ፈገግታ ችላ ብለዉ አስረግጠዉ ለኢትዮጵያ እንደ አንድ ጠንካራ መሪ ይቁሙ እንላለን። ግብጾቹ የኢኮኖሚ አሻጥር ጽንፈኞችና ኢዝላሚሰቶችን ከማደራጀት አልፈዉ ሲመቻቸዉ በዲፕሎማሲ ሳይመቻቸዉ ደካማ ዜጎችን በመጠቀም መጠነኛ ግርግር ሊያደርሱ ይችሉ ይሆናል ነገር ግን 110 ሚሊዮን ህዝብን  የሚያምበረክክ ምድራዊ ሀይል አይኖራቸዉም።

ባጠቃላይ ዶ/ር አብይ ቢያንስ በዚህ ስራቸዉ እንኳን ጥንካሬን አሳይተዉ በጾረና ፤ ባድሜና አዋሳኝ የኢትዮጵያ ድምበሮች የተደረገዉን የተልፈሰፈሰ ስምምነት ሳይደግሙ መሪ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ወታደር መሆናቸዉንም ለያሳዩ ይገባል ብለን እንመክራለን። ወላድ በድባብ ትሂድ በዘር ሳይሆን በኢትዮጵያዊነት መስፈርት አዋቂዎችን ከመረጡ እንኳን ለሀገራችን ለአለም የሚበቁ ልምድ ያካበቱ በኢትዮጵያዊነት ፍቅር የተሞሉ ምርጥ ዜጎች ስላሉን ቂምን ወደሗላ አድርገዉ የአባይን ስምምነት ከግቡ እንዲያደርሱ አበክረን እንጠይቃለን። የአባይ ጉዳይ የሀገር ጉዳይ ነዉ አባይ የኢትዮጵያ እንጂ የሌላ አይደለም ይህንን አስረግጦ ሳይታፈር ለግብጽ መነገር አለበት ግብጽ ስምምነት አለ የምትለዉን  ኢትዮጵያ የመቀበል ግዴታ የለባትም።  ዉሀ ሰጭዋ ኢትዮጵያ በፈለገችዉ መንገድ ስምምነቱን ማስቀመጥ ተፈጥሯዊ መብቷ ነዉ። ግብጾች ይህንን ያዉቁታል አላማቸዉ ኢትዮጵያ ጠንካራ ኢኮኖም እንዳይኖራት በመሆኑ ያለዉ መንግስት ኢትዮጵያዊ ነኝ ካለ ኢትዮጵያን በሚጠቀም መልኩ በጥንካሬ እንዲደራደር እናሳስባለን። አሜሪካም አረብም አገር መሄድ አያስፈልገንም በታዛቢነትም ዳረጎት የተቀበሉ የዉጭ ባለሙያዎች ጫና እንዲያሳድሩ እድል መሰጠት የለበትም። ለግብጾች ሊገለጽ የሚገባዉ ኢኮኖሚዬን በማይጎዳ ሁኔታ ዉሀዉን እለቅላችሗለሁ ነዉ መባል ያለበት ።

በእኔ በኩል  ዶ/ር በፍቃዱ በቀለ ከጀርመን፤ዶ/ር አክሎግ ቢራራ፤ፕሮፌሰር (ጌታቸዉ ሐይሌ፤ሐይሌ ላሬቦ)፤ ሻለቃ ዳዊት፤ኢንጂነር ይልቃል፤ ኮለኔል ጎሹ፤ በዉጭ ሀገርና በሀገር ዉስጥ በሙያዉ ልምድ ያላቸዉ ዜጎች ከያሉበት በመብራት ተፈልገዉ መምከር ይገባቸዋል እላለሁ።   አረጋዊ በርሄ፤ ሌንጮ ለታ፤ ሐይለ ማርያም ደሳለኝ፤ወርቅነህ ገበየሁ የተለያዩ ችግሮችን ለመፍታት በዶ/ር አብይ ከተመረጡ በዚህ ወሳኝ ጉዳይም ጁዋር መሀመድን ሐጂ ናጅብንም ላለመምረጣቸዉ ማስተማመኛ አይኖርምና በዚህ ነገር ልዩ ጥንቃቄ እንዲደረግ እንማጸናለን።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር

ሰመረ አለሙ

 

 

Source: ZeHabesha

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *