በመንግስቱ ሙሴ – ከዳላስ
የማይረሳው የ 100% አሸናፊነት እና መጭው ምርጫ በኢሕአዴግ ሸናፊነት ይጠናቀቃል
ለ28 አመታት በስልጣን ላይ የቆየው ኢሕአዴግ በስውር ስብሰባው የወሰነውን ባናውቅም እራሱን ለሁለት ከፍሎ ለምርጫ እየሄደ መሆኑን ግን እያየን ነው። ከዚህ ቀደም የኢሕአዴግ/ህወሓት ተቃዋሚ ነን የሚሉ ትቂት ስብስቦችም ሌላ ቀርቶ በወጉ ሀገራዊ እርቅ እና በግልጽ ተነጋግሮ ሂሳብ ባልተወራረደባት ኢትዮጵያ ከሁለቱ የኢሕአዴግ ጎራ በአንዱ ተጨምረው ምርጫው እንዲካሄድ በጉጉት ከሚጠይቁት ውስጥ ሆነው ስናይ እነዚህ ሰወች ድሮም የኢሕአዴጉ ጨቋኝ አገዛዝ የስውር አካላት ነበሩ ወይ? እንድንል አድርጎናል። ለነዚህ ኃይላት ከኢሓዴግ ጋር መቧደን እንደምክንያት የሚቆጥሩት የህሊና እስረኞች መፈታትን እና ድርጅቶች በነጻ መንቀሳቀስን ይሉናል። ይህ አባባላቸው በብዙ መልኩ ተቀባይነት እና እውነትነት የሚጎድለው መሆኑን ግን ተደጋግሞ ተነግሯል።
በ2009-10 ኢሕአዴግ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሲሰይም እንዴት እንደሰየመ የኢትዮጵያ ሕዝብ አያውቅም። ግን ልክ እርስ በእርስ ግጭት ተደርጎ አንዱ አሸናፊ ሌላው እና ጨቋኙ ክፍል ተሸናፊ እንደሆነ ሲነገረን በመንጋ ጭብጨባ ሌላ እንዲቀበል ተደርጓል። እውነታው ግን ወያኔም ሆነች ቀሪ አባል ድርጅቶች በምርጫ ለአሸናፊው ተገዥ በመሆን እና በሰላም ስልጣኑን አጽድቀዋል። በሕዝባዊ አመጽ ትናጥ! የነበረች ሀገራችን እና መድረሻ አጥተው የነበሩት ገዥወቻችን የሕዝቡን ጥያቄ በከፊል መመለሱ ግድ ሆኖባቸው ተወጥረው የተያዙበት ጊዜ በመሆኑ የህሊና እስረኞችን ፈተዋል። ይህ እስረኞችን የመፍታቱ እርምጃ የአንድ ወይንም የኢሓዴግ ቀና ተግባር ተደርጎ እንዲቆጠርም አድርጓል። እውነቱ ግን ኢሕአዴጓ ጉሩንቦዋን ተፈጥርቃ በሕዝብ አመጽ የተያዘችበት ጊዜ በመሆኑ ለቃቂው ጠቅላይ ሚኒስቴሯ ሁሉንም እስረኞች እንዲፈቱ ማድረጉን በሀገር ውስጥ ዜና እና በአለማቀፍ የዜና አውታሮች ለሕዝብ እንዲሰማ ሆኗል። ባጭሩ የእስረኞች መፈታት የዚህ ወይንም የዚያ አለያም የኢሕአዴግ አስቦ እና ተጨንቆ ያደረገው ሳይሆን ሳይወድ በግድ ተፈጥርቆ በመያዙ የተገደደበት ሁኔታ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል።
Enhance the Democratic Process
ዛሬ ኢሕአዴግ ለሁለት ተከፍሏል። ይህ አከፋፈል ውስጠ ሚስጢሩን ባናውቅም ምክንያቱም ውሳኔወች በጋራ ሲወሰኑ በዝግ ስብሰባ እና ሕዝብ እንዲያውቃቸው ሆኖ ሳይሆን በመግለጫ ከምንሰማው ባለፈ የምናውቀው እንደሌለ ግን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። እናም ዛሬ አንዱ ኢሕአዴግ መቀሌ ላይ ሰብስቦ የፌደራሊስት ሲል ሌላው ኢሕአዴግ አዲስ አበባ ላይ ሰብስቦ ብልጽግና ብሎናል። በነዚህ ሁለት ጎራወች ዘው ብለው የገቡ እንዳሉም እያየን ነው። ለምሳሌ ፌደራሊስ ነኝ ካለው ጎራ {በእርግጥ ግን ኢሓዴግ ፌደራል} ሆኖም አያውቅ እነመረራ ጉዲናን ያህል ተቃዋሚ ነን የባንቱስታን አይነት ስርአትን በሀገራችን ማየት አንፈልግም፣ እንታገላለን በሚል ብዙ ያጃጃሉን ሳይቀር ከሁለቱ በአንዱ ለመጨመር እና የጨዋታው አካል በመሆን ላይ ናቸው። በብልጽግናው ይፋ ባይሆንም እያኮበኮቡ ያሉ የድሮ ተቃዋሚ ነን ባዮች እና የእስካሁን ፖሊሲውን በጥብቅ ደጋፊ የሆኑት የጨዋታው አካል እንደሚሆኑ የሚገመት ነው። እነዚህ የብልጽግናው ጎራ የድሮ ተቃዋሚወች በይፋ ተደባልቀዋል ባይባልም የብልጽግናን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መሰረቱን ሁሉ እንደሚደግፉ ይፋ ሲያደርጉ ቆይተዋል የግዜ ጉዳይ እንጅ የጨዋታው አካል እንደሆኑ ሁሉ አብረው እሯጭ እንደሚሆኑም ይገመታል።
የተቃዋሚው እጣ ፈንታ
ህወሓት/ኢሕአዴግ (ፌደራሊስት/ብልጽግና) ለ28 አመታት ያመሷትን ሀገር እና በማንነቱ ያፈናቀሉትን፣ የገደሉትን፣ የአሰሩትን የገረፉትን ሕዝብ በቅጡ ይቅርታ ጠይቀው እና ስልጣኑን ለሕዝብ አስረክበው ሳይሆን በተቃውሞ የላላ አገዛዛቸውን በተለየ እንደገና በሁለት ጎራ አጠናክረው የመቀጠላቸው እርግጠኛ እየሆነ መጥቷል። የብዙ ሀገራት ተመክሮ የሚያስተምረን ጨቋኝ አገዛዞች ተወግደው ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለመሸጋገር የሕዝብ ውክልና ያለው አሸጋጋሪ መንግስት መስርተው እንደነበር ከደቡብ አፍሪካ እስከ አርጀንቲና አሳይቶናል።፡ጨቋኝ ገዥወች ከሕዝብ የዘረፉትን እና ያጠፉትን ሁሉ ከፍለውበት በእርቅ በንስሀ ወደ ሕዝብ እንዲደባለቁ ተደርጓል። ይህ ግን በሀገራችን ሊተገበር አልቻለም። ለመተግበር እንዳይችል ዋነኛው ምክንያት (1) ተቃዋሚ ነን ብለው የተሰለፉት ብቃት የለሽነት እና ሁሉም በሚያስብል በውጭ ሀገር ሆነው፣ ከሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ያልተገናዘበ የትግል ስልት መከተል ሲሆን።፡በሀገር ውስጥ የነበሩት በአንድ ወይንም በሌላ ስርአቱ አልፈስፍሷቸው እና አመራሮቻቸውን በራሱ ሰወች ሞልቶት ስለነበር፤ ጠንከር ብለው ስርአቱን ሊያፈርሱ ይችሉ የነበሩት እንደኦሮሞ ነጻነት ግንባር አይነቶች የስርአቱ ስር ነቀል ተቃዋሚ ሳይሆኑ አኩራፊወች በመሆናቸው፡እና ይህን አጋጣሚ ካገኙ በኋላ ስርአቱ እንዳይፈርስ በጥብቅ ከሚታገሉት ጎራ መደባለቃቸው ሲሆን።፡በዚያም ሆነ በዚህ በጋራ መታገል እና የጋራ ጠላትን በጋራ አስወግዶ ሕዝባዊ ስርአት ከመፍጠር ይልቅ ተቃዋሚ ነን ባዮች ሁሉ እንኳንስ ከሌላው ሊቧደኑ እና ጠንካራ ኃይል በጠንካራ ቃልኪዳን ፈጥረው ተፎካካሪ ከመሆን ይልቅ የእራሳቸውን ስጋ ቦጭቀው የሚጨርሱ ህልም አልባ አለን ባዮች በመሆናቸው ዛሬ ኢሓዴግም ሆነ ህወሓት አፈር ልሰው የተጠላ የመከራ ጠሪ ስማቸውን ቀይረው ይባስ ብሎም ስርአቱን እንቃወማለን ያሉትን ሳይቀር በፍቅር ማርከው ስልጣኑን ለመጭው 100 አመታት ለመጨበጥ ያለማወላወል እየተጓዙ ነው። ተቃዋሚ እንላቸው የነበሩት ብዙወች ቢሚያስብል ተመልሰው የህወሓት ወይንም የኦነግ/ኦህዴድ/አዴፓ ደጅ ጠኝ ሲሆኑም እያየን ነው።
ከሞላ ጎደል የማይናቅ የተቃውሞ/የተቀናቃኝ ጎራ መፍጠር እንደሚቻል ግን በእርግጥ ለማሳየት ይሞከራል። ዋና ከተማዋን በባላደራ እና በሀቅ ተነስተው የታገሉ ወገኖች ከሌሎች ትቂት እና እውነተኛ ተቀናቃኞች ጋር ተቧድነው የማንንም ምርቃት ሳይሹ ስርአቱን ሊፈታተኑ ይቻላቸዋል። ይህ የሚሆነው ግን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ለዘመናት እንዳየነው እከሌን አልወደውም ወይንም የነእከሌን ድርጅት አልፈልግም ከሚል ሳይሆን ትልቁን አደጋ ተመልክቶ የሚታረም ጥቃቅን አመልን አስወግዶ ሰፊ የህብረት እና የትብብር ቃልኪዳን ሲደረግ ነው። ሌላው ከመንጋ ፖለቲካ መውጣት ለሀገራችን ዋነኛ እና ድርጅቶች አባሎቻቸውን ወይንም ደጋፊወችን አሰባስበው ያለውን ሁኔታ በማወያየት መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል። ሰፊ ግንባር ከሁለቱ የኢሕአዴግ ጎራወች የተለየ መፍጠር ለመጭው ዘመንም ሆነ ጠንካራ የማይደፈር ስርአት ለመፍጠርም አስተማማኝ ይሆናል።
መጭው ምርጫ
ምርጫ መካሄድ ያለበት ሰላምን፣ መረጋጋትን ለሕዝብ ሰጥቶ ሕዝብ ነጻ፣ ግልጽ እና ፍትሀዊ ምርጫ እንዲያደርግ በመፍቀድ ነው። የሁለቱ ጎራ የዚህ ስርአት ደጋፊወች እና የስርአቱ ባለቤቶች ግን እጅግ volatile በሆነው የሀገራችን ሁኔታ ምርጫ ለማድረግ ወስነው እየተንቀሳቀሱ ነው። ለዚህ ደግሞ አሁንም የበሬ እንትን ይወድቅልኛል ብላ ስትከተል እንደዋለችው ቀበሮ ሁሉ ከከተማ ከተማ ተንቀሳቅሰው ሕዝብ መሰብሰብ እና ቢሮ ከፍተው የሀገሪቱን ሕዝብ ሊያደራጁ ያልቻሉት “ተቃዋሚወች” ሳይቀር የምርጫው ይምጣ አዳማቂውች ሆነው ሲያራግቡ ሲታይ አሳማኝ የሆነ ሎጅካቸው ምን ላይ እንደሆነ እንኳ ለሕዝብም ሆነ ለአባሎቻቸው አይገልጹትም።
ዛሬ እንኳን የብሔራዊ ሀገራዊ ድርጅት ቀርቶ ትግራይ ውስጥ ትግራዊ ሆኖ መንቀሳቀስ እንደከበዳቸው አረና እና አሲምባ ፓርቲወች እየተናገሩ ነው። የዶክተር አረጋዊ ፓርቲ መንቀሳቀስ ቀርቶ እራሱ ዶክተር አረጋዊ መቀሌ ለሀዘን መድረስ በሄደበት የደረሰበትን የህወሓት ዱርየወች ድብደባን ከራሱ አፍ ሰምተናል። አገራዊ ፓርቲ ማለትም መላ ኢትዮጵያን እወክላለሁ ሊል የሚችል ድርጅት ትግራይ ሄዶ ማደራጀት አይደለም ማሰቡ እራሱ የሚታሰብ አይደለም። በኦሮሚያ ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ከትግራይ ቢብስ እንጅ የኢተናነስ አይደለም። በሰሞኑ ያውም በአገዛዙ ደጋፊ በሆነው ኢዜማ በተባለው ድርጅት ቢሮ ናዝሬት ተፈጸመ የተባለውን ድርጅቱ ዘግቦ ተመልክቻለሁ። ጅማ፣ ሀረር፣ አዋሳ፣ ነቀምት፣ ሻሸመኔ ወዘተ የሚታሰብ አይደለም። አነሰም በዛ ድሮም ኢትዮጵያ ስላለ በጠላትነት በተፈረደበቱ የአማራ ክልል ብቻ ካልሆነ በሌሎች ክልሎች ከክልሉ ድርጅት ውጭ መንቀሳቀስ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ የሚታሰብ አይደለም። ይህ ከሆነ ቁም ነገሩ ታዲያ ለምን ተቃዋሚ ነን የሚሉት በይበልጥም ከዘር ስብስብ ውጭ ያሉት ይህን መጭ ምርጫ ለመሳተፍ ፈለጉ? ወይንም ለምን ዝምታን መረጡ? ጥያቄ ነው።
የኢሕአዴግ የቁጩ ፌደራሊም እና ዴሞክራሲ
ብልጽግና በሉት ፌደራሊስት ለ28 አመታት ከተጓዝንበት የዘረኝነት፣ የስደት እና የመፈናቀል ጎዳና ሊያወታን የሚችል ፕሮግራም (Roadmap) የላቸውም። ስምን መቀየር እና በሁለት ጎራ መሰለፍ ስርአቱን መቀየር ወይንም በነበረው ዘረኛ እና ከፋፋይ ስራትን በስርነቀል ለውጥ ማስወገድ እንዳይደለ ሊታወቅ ይገባል። ኢሕአዴግ/ህወሓት ፌደራል የሚለን አስተዳደር ጅማ ወይንም ሀረር፣ አለያም አዋሳ ሕዝቡ በመረጠው የራሱ ሰው ሲተዳደር አላየንም ወደፊትም የሚታሰብ አይደለም። የ28 አመታቱ ኢዴሞክራሲያዊ የሆነው የውሸት ፌደራሊዝም በይበልጥ በዘረኛ ሀገራት እንዳየነው እንደዋነኛ አመላካችም የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ አገዛዝ እስኪወገድ ድረስ እንደነበረው ክልሎችን ባንቱስታ በተባለ አስተዳደር ዘረኛ የሆነ የክልል አስተዳደር፣ አንዱ ከሌላው የማይገናኝበት በመዘርጋት ሕዝብ ከሕዝብ ተለያይቶ እንዲኖር አንድ ሀገር አንድ ሕዝብ በመመስረት እና ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሀዊ አስተዳደር ከማስፈን ይልቅ በአንድ ደቡብ አፍሪካ ብዙ የባንቱስታን ግዛቶች አስፍኖ የነጭ ገዥወች በተባበረ የጥቁር ሕዝብ አንድነት ስልጣናቸው እንዳይፈርስ የሰሩበት እንደሆነ ይታወቃል። የእኛን ሀገር ለ28 አመታት ያስተዳደሩት ኢህአዴግ/ህወሓት እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ፌደራል ስርአት ሳይሆን የተለያዩ አንድነት የሌላቸው የዘር አስተዳደሮች መስርተው እስከዚህ ቀን አድርሰውናል። በዘር በተከፋፈለች ሀገር ፌደራሊዝም ይቻላል እንኳን ቢባል የኢሕአዴግ/ህወሓት ኢትዮጵያ ግን ዴሞክራሲ የተባለው የፌደላዚም የጀርባ አጥንት የሌላት በይበልጥም የአንድ ዘር የበላይነት ለ 27 አመታት ተንሰራፍቶ የከረመባት ነበረች። ያ ለውጥ ተብሎ በሕዝባዊ አመጹ ግፊት ስልጣን ከተነቃነቀች በኋላ የተካው ገዥ መልክ፣ ስም እና ቋንቋው ከመለየቱ ውጭ እስከአሁን የአንድ ዘር የበላይነት የተንሰራፋበት መሆኑ የሚክድ ሊኖር አይችልም።
ዛሬ ምርጫ ተብሎ ከበሮው መጎሰም ሲጀመር የተዘየደው አዲስ ታክቲክ ደግሞ በደይ የነበረው ስርአት እስከ አሰስ ገበሱ እና እስከ የደህንነት እና ወታደራዊ አደረጃጀቱ፣ በይበልጥም ኢ ፍትሀዊ በሆነ ዘረፋ የተግበሰበሰውን የሀገር ንብረት ሳይመለስ አዲስ ምርጫ ልናደርግ ነው ተብሎ ሲንደፋደፉ ማየት የምርጫው ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ለመተንበይ የሚሳን እንዳልሆነ አሳውቆ ማለፉ ተገቢ ነው።
ባልተረጋጋች ሀገር፣ ሀብት ንብረቷ ተዘርፎ በትቂት ሰወች እና የፖለቲካ ድርጅት በተወሰደበት ሁኔታ፣ የሀገሪቱ የደህንነት መረብ አሁንም በቆየው የአሰራር ልምዱ በቀጠለበት፣ ኢትዮጵያ ለሁሉም ሳይሆን ክልል ለባለክልሉ በተባለበት እና ያ እየተከበረ ባለበት ሁኔታ ወደምርጫ መሄድ የስርአቱ ቁንጮወች አሁንም ያለተወዳዳሪ ስልጣኑን እንዲጠቀልሉ እና ሕጋዊነት አገኘን በሚል ለቀጣይ 100 አመታት የሚያስኖራቸውን መደላድል የሚረከቡበት ከመሆን ውጭ ፍትሀዊ እና ነጻ ብሎም ዜጎች በሰላም ያለተጽእኖ ከቀረበላቸው ውጭ የሚመርጡበት ሊሆን ግን አይችልም። ነጻ ምርጫ እና ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር በሀገራችን እንዲሰፍን ከተፈለገ እና ቁርጠኝነት ካለ የመጨዋቻው ሜዳ ለሁሉም ነጻ የሚሆንበት ሁኔታ መደላደል ይኖርበታል። ከሁሉም በፊት ጅማ የሚኖር የጎንደር ተወላጅ ወይንም ትግራይ መቀክሌ የሚኖር የወለጋ ተውላጅ አለያም አዋሳ ተወልዶ ያደገ የሽሬ ሰው የሚመስለውን እንዲመርጥ እና ለምርጫው ደግሞ ከልካይ እና ገዳቢ የሌለው የምርጫ ሁኔታ ኖሮት ያሻውን ይሰራልኛል ይወክለኛል የሚለውን ያለተጽእኖ የሚመርጥ ካልሆነ በሀገሩ ባእድ ሆኖ ከታየ እና የእርሱ ያልሆነን፣ ልቦናው የልፈቀደውን እና ያላመነበትን ፓርቲ እና ግለሰብ እንዲመርጥ መገደድ ከድጡ ወደማጡ እንጅ ዴሞክራሲያዊ ሊሆን አይችልም።
ምርጫው ይራዘም ሲባል
አብይ አህመድ ወርዶ አብይ አህመድ መልሶ እንዲመረጥ ከሆነ ፍላጎቱ ዴሞክራሲያዊ ማድረግ፣ ሰላም በሰፈነበት፣ በተረጋጋ፣ እና ዜጎች ወጠን ድምጽ ብንሰጥ የሚደርስብን የለም ብለው በአመኑበት ግዜ እና ሁኔታ ቢሆን ህጋዊነቱንም ሆነ ፍትሀዊነቱ ያጠነክራል እንጅ አያዳክመውም። ምርጫው ይራዘም የሚል አስተሳሰብም የሚመጣው መራጩ በድፍረት ያለሰቀቀን ለምርጫ የሚወጣበት ግዜ እስኪደርስ ማለት ነው።
አብያተ ክርስቲያናት እና መስጊዶች በሚቃጠሉባት ሀገር። ዜጋው በሚናገረው ቋንቋ ተነጥሎ ልቀቅልን በሚል ሁኔታ ገና ያልተረጋጋ እና ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሰላም እና መረጋጋት በሌለበት ወደምርጫ እንሄዳለን ማለት አሁንም የ 100% አሸነፍሁን መልሶ ለምድገም እና ያው ከተለመደው እገዛለሁ አልገዛም አዙሪት ውስጥ ከመግባት ውጭ ሌላ ሊሆን አይችልም። የዛሬ አምስት እና አስር አመታት በአይነደረቅነት የመቶ ፐርሰንት አቸናፊነትን ዛሬ በተለየ ታክቲክ ከመድገም ውጭ ሌላ ሊሆን እንደማይችል ምርጫው ሊታወቅ ይገባል። ገዥወች ስም እና ቀለም እየቀያየሩ ሲያስጨበጭቡ ሌላው አብሮ አጨብጫቢ መሆን ለነጻነቱ እና ለሀገሩ አይበጅም። ስላም በሌለበት ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማድረግ አይቻልም!
Adios!