ጀነራል ጃገማ
News

ጀነራል ጃገማ ኬሎን

ጀነራል ጃገማ ኬሎን ታዉቋቸው እንደሆነ አላውቅም፤ ግን ጄነራሉ ገና በዐሥራ አምስት ዕድሜያቸው አካባቢ፣ ኢጣልያን ሀገራችንን ከወረረ በኋላ፣ ሽማግሌና ሕፃን ሳይለይ ሲገድል፣ ያገሩን ሀብት ሲዘርፍ፣ ሚስት ሲደፍር፣ ያልተከለውን ዛፍ ለገበያው ሲቈርጥ፣ ያላሳደገውን ፈረስ ቀምቶ ሲጋልብ፣ ያላቀናዉን መሬት ከሕዝብ ዘርፎ ከባሕርማዶ ላመጣው ወገኑ ሲሰጥ፣ ቤቶችንና ቅዱሳት ስፍራዎችን ሲያቃጥልና ሲያረኵስ አይተው፣ ወንድሞቻቸውንና እኅቶቻቸውን አስከትለው፣ ሊዋጉ ጫካ የገቡና፣ ኋላም በዚህ አፍላ ዕድሜያቸው፣ የሦስት ሺ ዐምስት መቶ አርበኞች መሪ የነበሩ፣ በብዙ ጐራ በመዋላቸውየበጋው መብረቅ” የሚል ስያሜ የተሰጣቸው፣ ነፃነት ከመጣ በኋላም ለጄነራልነት ማዕርግ የበቁ መሪ ነበሩ።

የኦሮሞ ብሔረ-ሰብ እንደመሆናቸው፣ የልጅነታቸው ትልቁ ሕልማቸው፣ መላልሰው እልፍ ጊዜ ስለሰሙት፣ ሺ ግዳይ እንደጣሉት እንደቅድመ አያታቸው ጎዳና ነሞ፣ ብዙ ሰው በመግደል ጀግና መሆን ነበር። ታዲያ ይኸንን የሰማ አንድ ጋዜጠኛ ጀኔራል ጃገማን፣ “ልጅ ሳለህ ሕልምህ ለምን እንደቀድሞ አያትህ ሰው በመግደል ብቻ ተወሰነ” ብሎ ቢጠይቃቸው፣ ጃገማ በጣም ሳቁና፣ “አየህ ጐበዝ፣ በዚያን ጊዜ ከሽማግሌዎቹና ከሞግዚቴ እሰማ የነበረው የቅድመ-አያቴን ታሪክና ጦርነቱን ብቻ ነው።

ሌላው ቀርቶ ከእረኛ ጋር እንኳ በቀበሮ ጒድጓድ ሁነህ ዓሣ ነባሪ ይታይሃለን። አይታይህም። ስለዚህ እንዳሁኑ ልጆች ሐኪም፣ መሐንዲስ፣ ፓይለት፣ ሳይንቲስት … ለመሆን ላሰብ አልችልም። ምክንያቱ ደግሞ በኔ ዘመን ይኸ አልነበረም። እንደማንኛውም ልጅ ሕልሜና ምኞቴ ከምሰማውና ከማየው የወጣ አይደለም” ብለው መለሱ። በጣም ጥሩ መልስ። ጃገማ እንዳሉት ሰው የቀዬው ፍጡር ነው። አሳቡም ሆነ ምኞቱ የሚቀረፀውና የሚያንፀባርቀው በአካባቢውና በጊዜው ካለው፣ ካየው፣ ከሰማው ነው። ያንድ መሪም ሆነ ሥራው መፈረጅ ያለበት እሱ በነበረበት ጊዜና ወቅት አንፃር እንጂ ለምን በኔ ጊዜ እንደሚሠራና እንደሚታሰብ አልሠራም ወይንም አላሰበም ማለት አይቻልም

(ፕ/ር ኃይለማርያም ላሬቦ)

Source: ZeHabesha

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *