ደምቢዶሎ
News

‹‹በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ በታገቱ ተማሪዎች ጉዳይ መንግሥት ግልጽ መረጃ ሊሰጥ ይገባል›› የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም

የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የ2012 በጀት ዓመት የመጀመርያውን የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፣ የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አጋቾችን በተመለከተ በመንግሥት በተወሰደው ዕርምጃ ለሕዝብ የተሰጠው መረጃ ምሉዕነት የጎደለውና እጅግ የዘገየ ነበር አለ፡፡ መንግሥት ግልጽ መረጃ መስጠት አለበት ሲልም አሳስቧል፡፡

በዋና ዕንባ ጠባቂ እንዳለ ኃይሌ ግዛው (ዶ/ር) ሰኞ ጥር 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ተፈርሞ በወጣው መግለጫ፣ ማንኛውም ሰው መረጃን የመጠየቅ፣ የማግኘትና የማስተላለፍ መብት እንዳለው የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 እንደሚደነግግ አስታውሷል፡፡ በዚህ መሠረት በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ የታገቱ ተማሪዎችን አስመልክቶ ስለተወሰደው ዕርምጃ ለሕዝብ የተሰጠው መረጃ መዘግየቱ ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ የመንግሥት አካላት የሚሰጡ መረጃዎች እርስ በርሳቸው የማይጣጣሙና ይመለከታቸዋል የተባሉ አካላት ወደ ሌላው የመግፋትና እኔን አይመለከተኝም የሚለው የበዛ ችግር ሆኗል ሲል አስታውቋል፡፡

‹‹ተለቀቁ ስለተባሉ ተማሪዎች መንግሥት ለማሳያነት ያቀረባቸው ማረጋገጫዎች ባለመኖራቸው፣ ሕዝቡ በመላምት እንዲያስብና በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ጥርጣሬ እንዲፈጠርና አለመተማመን እንዲጠናከር አድርጓል፤›› ካለ በኋላ፣ ስለዚህ አሁንም የሚመለከተው የመንግሥት አካል በታገቱት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጉዳይ ግልጽ መረጃ ሊሰጥ ይገባል ብሏል፡፡

ተማሪዎቹን ለማስለቀቅ እየተደረገ ያለ ጥረትን አስመልክቶ ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌለ ያስታወቀው ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ በዜጎች ያውም በሴቶች ላይ የደረሰን በደል ለማስቆም መንግሥት ተለሳላሽነት እንዳሳየ አብዛኛው ሕዝብ ድምዳሜ ላይ እየደረሰ በመሆኑ፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት መረጃ በመስጠትም ሆነ ችግሩን በመፍታት ረገድ የተፋጠነ ምላሽ እንዲሰጡ አሳስቧል፡፡

‹‹ተመሳሳይ ሁኔታዎችና ችግሮች ሲከሰቱ ሕዝብ ከመጠየቁ ወይም በማኅበራዊ ሚዲያ ቀድሞ ያገኘውን መረጃ እውነት ነው ብሎ ከመቀበሉ በፊት፣ የሚመለከተው የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥት አካል ለዜጎች ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ የመስጠት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል፤›› ሲልም አስግንዝቧል፡፡

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት የመስጠት ሰፊ መሠረታዊ ተልዕኮ ቢሰጥም፣ ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒ ተቋማቱ ይህንን ተልዕኳቸውን እንዳይወጡ ማስተጓጎል፣ የተማሪዎችን ሕይወት ማጥፋት፣ የአካል ጉዳት ማድረስና የሕዝብን ሀብትና ንብረት የማውደም ድርጊቶች ይስተዋላሉ ብሏል፡፡ በእነዚህ ድርጊቶች ላይ የተሳተፉ አካላትን በአግባቡ አጣርቶ ዕርምጃ መውሰድ እንደሚገባ፣ በዚህ ረገድ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡

‹‹በሌላ በኩል በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሁከት የፈጠሩ አካላትን ከጀርባቸው ሆኖ፣ ይህንን እኩይ ተግባር እንዲፈጽሙ የሚመራ የተደራጀ ቡድን እንዳለ ይገለጻል፡፡ ስለዚህ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን አካላትን ለሕዝብ ማሳወቅ፣ ሕዝቡን የጉዳዩ ባለቤትና በወንጀል መከላከል የራሱን ሚና መጫወት ስለሚያስችለው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፤›› ብሎ፣ ከፊት ተሠልፈውም ሆነ ከኋላ በደጀንነት ቆመው ችግሩን እየፈጠሩ ያሉ አካላት ላይ የማያዳግም ዕርምጃ በመውሰድና ከምንጩ ለይቶ በማድረቅ፣ የሕግ የበላይነት ልዕልና በተሟላ መንገድ ተግባራዊ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የመገናኛ ብዙኃንን በተመለከተም ባለፉት ስድስት ወራት ባደረገው ክትትል በአንዳንዶቹ የግልም ሆነ የመንግሥት ሚዲያዎች ወቅታዊና ሚዛናዊ መረጃ ለኅብረተሰቡ በመስጠት ረገድ፣ መልካም ያልሆኑ ዝንባሌዎች መስተዋላቸውን ገልጿል፡፡ ተቆጣጣሪው የመንግሥት ተቋም ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አስረድቷል፡፡ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባቸውን ሚዛናዊ ለማድረግ የፌዴራልም ሆኑ የክልል መንግሥታት ኃላፊዎች መረጃ ሲጠየቁ፣ ለመስጠት ተባባሪ የማይሆኑ አካላት መኖራቸውንና ቅሬታዎች እንደሚቀርቡለት ጠቁሟል፡፡

የቅርብ ጉዳዮችን ለአብነት በማንሳት የትግራይ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ በክልሉ ውስጥ ባሉ የወረዳና የዞን ጥያቄዎችን በተመለከተ፣ የአዲስ አበባ ቤቶች ኤጀንሲ ቤት ለኅብረተሰቡ የሚያከፋፍልበትን ሥርዓት አስመልክቶ፣ የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ስለታገቱት ተማሪዎች በተመለከተ መረጃ እንዲሰጡ ተጠይቀው ተባባሪ ካልሆኑት መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡

‘አንተ ካልተናገርህ ሌሎች ስለአንተ ይናገሩልሃል’ ነውና ብሂሉ፣ በስም የተጠቀሱ ተቋማትም ሆኑ ሌሎች መረጃን በመከልከልና ተባባሪ ባለመሆን የተጠመዱ የመንግሥት አካላት፣ ከድርጊታቸው ሊታቀቡና አሠራራቸውን ሊያስተካክሉ ይገባል እንላለን፤›› ብሏል፡፡

የሃይማኖት ተቋማትንና አማኞችን መነሻ ያደረጉ ጥቃቶችን፣ የተፈናቃዮችን ጉዳይ፣ የተለያዩ አቤቱታዎችን፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና የወሰዱ ዜጎች የገጠማቸውን ችግር፣ ለመንገድ ሥራ ይዞታ ለሚለቁና ባለንብረቶች ካሳንና ወሰን ማስከበርን፣ የአካባቢ ብክለትንና ኃላፊነትን አለመወጣትን፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ የሚሹ ጉዳዮችንና ከሕገ መንግሥቱ ጋር ተቃርኖ ያላቸው አሠራሮችና ሕጎችን በተመለከተ የተፋጠነ ምላሽና መፍትሔ እንዲሰጥ በሪፖርቱ ማሳሰቡን ተቋሙ አስታውቋል፡፡

መንግሥት የታገቱ ተማሪዎች በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ መረጃ እንዲሰጥ በሰላማዊ ሠልፎች ተጠየቀ

Source: ethiopianreporter

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *