ኦነግ ሸኔ
News

በቡራዩ “የጃል ማሮ” ፎቶ ጨረታ አፈናከተ፤ “ቡራዩ ሆኖ ከሃዲን ማሞካሸት አይቻልም” ነዋሪዎች

በቡራዩ የተከሰተውን ረብሻ አስመልክቶ ቢቢሲና የመንግሥት ሚዲያዎች የተሟላ መረጃ አለማቅረባቸውን የቡራዩ ነዋሪዎች ለጎልጉል ገለጹ። እነሱ እንዳሉት በአንድ መጠነኛ ሆቴል ምረቃ ላይ ለተነሳው ጸብ መነሻው በሽብር ተግባሩ የሚታወቀውና ጃል ማሮ (ኩምሣ ድርባ) የሚባለው የኦነግ ሸኔ ሽፍታ መሪ ፎቶ በጨረታ እንዲሸጥ መቀረቡን ተከትሎ ነው።

ነዋሪዎቹ ለጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ ሲያስረዱ በምረቃው ላይ ጃል ማሮን የሚያወድሱ ሙዚቃዎች በዝተው ነበር። የውዳሴው ሙዚቃ መብዛቱ ከቡራዩና አካባቢው ወይም በተለምዶ የ“ሸዋ” የሚባሉትን ኦሮሞዎች አላስደሰተም። ሙዚቃው ቅይጥ እንዲሆን ቢጠየቅም ሰሚ አልነበረም።

“በዚህ ስሜት ውስጥ እያሉ ነው ጃል መሮ የሚባለው የኦነግ ሸኔ ሽፍታ መሪ ምስል ለጨረታ የቀረበው” ሲሉ በስፍራው የነበሩ ምስክሮች ያረጋግጣሉ። አክለውም “የዚህን ጊዜ ንትርክ ተነሳ። በንትርኩም “ይህ አገር ሻጭ፣ ከሃጂ፣ አሸባሪ፣ ሽፍታ ማን ስለሆነ ነው ፎቶው ለጨረታ የሚቀርበው? የት እናውቀዋለን? ለናንተም አልጠቀመም” በማለት ተቃውሞ ያላቸው ተቆጡ።

“ምክንያቱ በውል ለማይታወቅ ጉዳይ ጫካ ሆኖ ከወያኔ ጋር በማበር አገር የሚወጋ ከሃዲ ፎቶ ለጨረታ መቅረብ የለበትም በሚል አካባቢ ጠቅሰው መሟገት ጀመሩ። ጉዳዩ ከረረና እገሌ ከገሌ ሳይባል እርስ በእርስ መፈናከት ተጀመረ። የዚህን ጊዜ ፖሊስ ጣልቃ ገባ” በወቅቱ በቦታው የነበሩ ለጎልጉል የሰጡት ቃል ነበር።

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፣ አስቀድመው የተፈናከቱት እርስ በርስ መሆኑ እየታወቀ፣ የጸቡ መነሻ የጃል መሮ ፎቶ ጨረታ መቅረብና ከልክ በላይ በዘፋኞቹ መሞገስ መሆኑ እየታወቀ በተጠቀሱት ሚዲያዎች አለመጠቆሙ የቡራዩ ነዋሪዎችን አሳዝኗል።

አዲስ ስታንዳርድና ቢቢሲ አማርኛ ነዋሪነቷ ኖርዌይ የሆነች ሴት ላይ የደረሰውን ፍንከታ አጉልተው ዘገቡ እንጂ በጠርሙስ ጉዳት የደረሰባቸው በርካታ እንደሆኑ የቡራዩ ነዋሪዎች አስረድተዋል።

ሃዊ ኤች ቀነኒ የምትባለው ይህቺው የኖርዌይ ነዋሪ “በወቅቱ ዘፍነን እየወጣን ነበር። የተጠራው ሰው እየተበተነ ባለበት ወቅት ፖሊሶች ወደ ሆቴሉ መጥተው ኦነግን አሞካሽታችኋል በሚል ነው ድብደባውን የጀመሩት” ስትል ለቢቢሲና ለአዲስ ስታንዳርድ የተናገረችው ሰባራና ያልተሟላ፣ ሃቁን የሸሸገ መሆኑንን በስፍራው የነበሩ ይናገራሉ። አንዳቸውም ሚዲያ ስለ ጃል መሮ ፎቶ ጨረታ ጉዳይ አላነሱም።

ነዋሪዎች የቡራዩ ፖሊስ ጥንቃቄ መርጦ መሸፋፈኑ ሌሎች ሚዲያዎችም ዋናውን ጉዳይ እንዲደብቁት ድጋፍ ማድረጉን በትችት ገልጸዋል። መጠነኛም ቢሆን ሆቴሉ ከወለጋ መጣ የተባለ ሰው እንደሆነም አክለው ተናግረዋል።

የጸቡን መነሻ ያስተዋሉና የተከታተሉት እንደሚሉት ጃል መሮ የሚባለው አሸባሪና ሽፍታ ላይ በኦሮሞ ተወላጆች ዘንድ የተለያየ አቋም መኖሩን ሲሆን፣ ጉዳዩ የመጪውን ምርጫ ውጤት አመላካች እንደሆነም ጠቁመዋል።

ጃል መሮ መንግሥትና ሕዝብ ላይ ጦርነት ያወጀ፣ የውጪ አገር ዜግነት ያላቸው ገንዘብ በማሰብሰብ የሚመሩት የኦነግ ሸኔ አንድ ጉራጅ መሆኑ ይታወቃል። ዜግነታቸውን መመለስ ስለማይፈልጉ ወደ ውጭ መውጣት የመረጡ ክፍሎች የሚረዱትና የሚመሩት፤ ጦርነት የመረጠ ቡድን በርካታ ንጹሃንን ኢሰብዓዊ በሆነ መንገድ መግደሉ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል።

በኖርዌይ የበርገን ነዋሪዎች እንዳሉት ከዚሁ ከጃል መሮ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ኦሮሞዎች አካባቢና ጎራ በመለየት መነጋገር ካቆሙና የጎሪጥ መተያየት ከጀመሩ ሰንብተዋል።

በአገር ውስጥ ደግሞ በ“ዲቃላ” የፖለቲካ ጦስ እየታመሰ በሚገኘው ኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ጎራ እየለዩ መከታከት እየተለመደ መጥቷል። በኦሮሞነት ከተመዘገበው ህዝብ ቁጥር ውስጥ እጅግ በርካታ የሆነው የተዳቀለ በመሆኑ በሰሞኑ የ“ዲቃላ” ፖለቲካ ዲስኩር ዙሪያ ይፋ ሆኖ ባይወጣም፤ ትንሽ የማይባል ቁጥር ያለው ሕዝብ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ቁጣውን እየገለጠ ይገኛል።

ከወራት በፊት የኦሮሞ ድርጅቶች እና ታዋቂ ሰዎች በተገኙበት ሁሉም ተሰብሳቢዎች በሙሉ ድምጽ በወለጋ በአሸባሪነት እየተንቀሳቀሰ በሚገኘው ቡድን ላይ የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድ በፊርማ ማረጋገጣቸው ይታወሳል።

ጃል መሮ የተባለው ወንበዴ የመንግሥት ጥቃት በወለጋ በሚደርስበት ወቅት ትግራይ ስለመታየቱ የዓይን ምስክር ነን ያሉ በወቅቱ መናገራቸውን በተለይ በፌስቡክ የተሰራጨ ጉዳይ ነበር።

በውጭ አገር የሚኖሩ ኃይሎች ጃል መሮን የሚደግፉት በዚህችው ሃዊ ቀነኒ በኩል እንደሆነ በስፋት እየታወቀ ሳለ የጃል መሮ ፎቶ ለጨረታ በመቅረቡ ግጭቱ ስለመቀስቀሱ አንድኛውም ሚዲያ ያለመዘገቡ የቡራዩ ነዋሪዎችን ያሳዘነ ብቻ ሳይሆን ጥያቄ የፈጠረም ጉዳይ ሆኗል።

 

Source: http://www.goolgule.com/

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *