ዛሬ፣ እሁድ፣ ጠዋት ለጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ እና ለፓርቲያቸው ድጋፋቸውን ለመስጠት ሠልፍ በወጡ ሠልፈኞች ላይ በተወረወረ ቦምብ ቢያንስ 29 ሠዎች መቁሰላቸውን የአምቦ ከተማ አስተዳደር እና ጸጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ ለቢቢሲ ተናገሩ።
ኃላፊው አቶ ሂንሰርሙ ደለሳ እንዳሉት ቦንቡ የተወረወረው ለድጋፍ ሰልፍ በወጡ ፈረሰኞች ላይ ነው።
ጉዳት ካጋጠማቸው መካከል የህክምና እርዳታ ተደርጎላቸው ከሆሰፒታል የወጡ እንዳሉ ሁሉ የተለያዩ የጉዳት መጠን ያስተናገዱ መኖራቸውን አቶ ሂንሰርሙ ተናግረዋል።
• “መንግሥት ጠንከርና መረር ያለ እርምጃ ለመውሰድ ተገዷል” ጄነራል ብርሃኑ ጁላ
• የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አባላት በንስሐ እስኪመለሱ ክህነታቸው ተያዘ
• በአወዳይ በመንግሥት ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች መካከል ግጭት ተፈጠረ
ከወንጀሉ ጋር ተያይዞ ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች መኖራቸውን የተናገሩት ኃላፊው “በጫካ ውስጥ ታጥቆ የሚንቀሳቀስው ኃይል ወንጀሉን ሳይፈፅም እንደማይቀር እንጠረጥራለን” ብለዋል።
በጥቃቱ በርካታ ፈረሶችም መጎዳታቸውን ቢቢሲ ከአምቦ ከተማ ነዋሪዎች ባገኘው መረጃ ለማወቅ ችሏል።
ከቀናት በፊት በአወዳይ ከተማ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ድጋፋቸውን ለመግለጽ በወጡ ሰዎችና በተቃዋሚዎች መካከል ግጭት አጋጥሞ ለሰልፍ በወጡ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን መዘገባችን ይታወሳል።
ሰሞኑን በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አስተዳደርና ለአዲሱ ፓርቲያቸው፣ ብልጽግና፣ ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ ነዋሪዎች በተከታታይ ሰልፍ እያደረጉ ነው።
አርብ እኩለ ቀን ላይ ለአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ቡራዩ ውስጥ የከተማዋ ፖሊስ አዛዥ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች በተፈጸመባቸው ጥቃት ሲገደሉ ሌሎች ሦስት ሰዎች ደግሞ ቆስለው ሆስፒታል መግባታቸው ተዘግቧል።
• የጠቅላይ ሚኒስትሩ የድጋፍ ሠልፍ እና የኦፌኮ ስብሰባ መከልከል በጅማ
ፖሊስ በቡራዩም ሆነ ዛሬ እሁድ በአምቦ ከተማ ከተፈጸሙት ጥቃቶች ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ ሰዎችን መያዙን ያሳወቀ ሲሆን እስካሁን ግን ለጥቃቱ ኃላፊነት የወሰደ ወገን የለም።
Source: BBC amharic