– የትግራይ ሕዝብ ለአንድነት ቅድምያ እንዲሰጥ ተጠየቀ
– “ከፈለገ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ለብቻው ይገንጠል”
– “የጦርነት ጉሰማ የሚበላው ድሃውን የትግራይ ሕዝብ ነው”
ህወኃት የትጥቅ ትግል የጀመረበትን 45ኛ አመት የካቲት 11 ቀን 2012 ባከበረበት ወቅት መልዕክት ያስተላለፉት የትግራይ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገ/ሚካኤል፤ “በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ አስጊ ነው፣ አገሪቱም ወደ መበታተኑ እያመራች ነው፤ ሠላም ጠፍቷል፣ ለውጡም አቅጣጫውን ስቷል” ብለዋል፡፡
በፓርላማ ለሚገኙ የትግራይ ተወካዮች ባስተላለፉት መልዕክታቸውም፤ ‹‹የሥልጣን ጊዜያችሁ ከማለቁ በፊት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ጣልቃ ገብነት፣ በተለይም ትግራይን በተመለከተ በመሪዎች ደረጃ የተሰጡት የጥላቻና የፀረ – ሕዝብ ንግግሮችን በይፋ ኮንኑ፤ ይህ የማይሆን ከሆነም፣ ትግራይ ራሷን የቻለች አገር መሆኗን አውጁ፤ ሀገር በመበተን ሂደት ተሳታፊ ነበሩ ተብላችሁ በታሪክ እንዳትወቀሱ ግዳጃችሁን ተወጡ ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በትግራይ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮችና አባላት የካቲት 11ን አስመልክቶ ለትግራይ ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ህዝቡ ለአገራዊ አንድነት ቅድሚያ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በሌሎች አካላት በትግራይ ሕዝብ ላይ የሚሰነዘሩ የጥላቻ መልዕክቶች እንዲቆሙም የትግራይ የብልጽግና አመራሮች ጠይቀዋል፡፡
‹‹አኩሪው የትግራይ ሕዝብ የፀረ ጭቆና ትግል በከሰሩ ሀይሎች አይራከስም፤ የጥቂቶች የቡድናዊ ፍላጎት መጠቀሚያም አይሆንም›› ያለው የትግራይ የብልጽግና ፓርቲ አመራር፤ “የሕዝብ ትግል አላማ ላልተገባ የፖለቲካ ጨዋታ እየዋለ ነው” ብሏል፡፡
የሕዝብን ተጋድሎ ከንቱ የሚያደርግን ያልተገባ የፖለቲካ ጨዋታን የትግራይ ወጣቶች እንዲረዱና እንዲሁም ለሁሉም በእኩል የምትሆን ኢትዮጵያን ለመገንባት ከሚደረገው ጥረት ጎን እንዲሰለፉ ጽ/ቤቱ ጠይቋል፡፡
‹‹በአሁኑ ወቅት የከሰሩ የፖለቲካ ሀይሎች የመስዋዕትነቱን አላማ ወደ ጎን ብለው ሕዝብን ማደናገር የሙሉ ጊዜያቸው ተግባር አድርገዋል›› ያለው የትግራይ ክልል የብልፅግና ፓርቲ የአመራሮቹ መግለጫ፤ ‹‹የትግራይ ሕዝብ መስዋዕትነት ከፍሎ ካገኘው ድል በርካታ አመታት በኋላ የትግራይ ሕዝብ አሁንም ያልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል›› ብሏል፡፡
የሕዝቡን ትግል የቡድን ትግል አድርገው የሚመለከቱ ሀይሎች የዚህ ችግር ፈጣሪዎች መሆናቸውን ያስረዳው መግለጫው፤ ይሄን አካሄድ ካልቀየሩ ኪሳራቸው ይበዛል ብሏል፡፡
አክቲቪስቶች ሕዝብን ከሕዝብ ከማጋጨት እንዲቆጠቡ፣ መገናኛ ብዙሃን በሃላፊነት እንዲሰሩ የጠየቀው መግለጫው፤ መላው የትግራይ ሕዝብ ከቀሪ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር በአንድነትና በትብብር አገሩንና ራሱን እንዲያበለጽግም ጥሪ አቅርቧል፡፡
የህወኃት መስራች አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው፤ “ደብረፂዮን ከፈለገ ብቻውን ይገንጠል፤ የትግራይ ህዝብ አሁን ያለው ችግር ውስጥ ነው፤ አብዛኛው እየኖረ ያለው በምግብ ለስራ ነው፤ በእርዳታ እየኖረ ያለውን ህዝብ ልክ እነሱ እያኖሩት ያለ ይመስል ወደ እሣት ለማስገባት መነሳታቸው እጅግ አሳዛኝ ነው” ብለዋል፡፡
የቀድሞው የህወኃት አባልና የህወኃትን አካሄድ ተቃውመው ከፓርቲው የለቀቁት በአሁኑ ወቅት በዲሞክራሲ ግንባታ ማዕከል በሚኒስትር ማዕረግ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ዛዲግ አብርሃ በበኩላቸው፤ “ትግራይ ውስጥ የጦርነት ጉሠማ እየሠማን ነው፤ ይህ የጦርነት ጉሠማ ዞሮ ዞሮ የሚበላው መሄጃ የሌለውን ድሃውን የትግራይ ህዝብ እንጂ በአውሮፓ ተቀማጥለው የሚኖሩትን የስብሃት ነጋ ልጆች አይደለም፤ ይሄን የትግራይ ህዝብ ልብ ሊል ይገባል” ብለዋል፡፡
ምንጭ: አዲስ ማለዳ