tuluforca
Articles Features

ቱሉ ፎርሳ

In the memory of May Day – የሰራተኞችን ቀን መታስቢ እንዲሆን

ቱሉ ፎርሳ
*********
ቱሉ ሠላሳ ዓመቱ ነው።ወይም ወደዚያ ግድም ነው። እና ቱሉ ቁመቱ ረጅም ነው። የቱሉ እጆች ትላልቅ ናቸው።የቱሉ ክንዶች ጠንካሮች ናቸው።የቱሉ መዳፎች ሸካራ ናቸው። ቱሉ ከማካሮኒ ፣ፓስታና ፓስቲኒ ፋብሪካ ውስጥ ወፍጮ ክፍል ነው የሚሠራው። ወፍጮ ክፍል ስድስት ዓመት ሠርቷል።
..
የፋብሪካው ባለቤት ሙሴ ጋሌብ ናቸው። ጌታ ጋሌብ እዚች ሃገር (ይቺው የኛይቱ የምንላት)ሲገቡ ቤሳቤስቲን አልያዙም።እዚህ ከገቡ በኋላ ነው ይህንን ሁሉ ያፈሩት፣ ያንን ሁሉ ቪላ ሠርተው የሚያከራዩት፣ያንን ሁሉ ሱቅ የከፈቱት። ጌታ ጋሌብ የናጠጡ ዲታ ናችው።አቤት ሠራተኛ ሲፈራቸው።ጌታ ጋሌብ ሽማግሌ ናቸው።አጭር ፣መላጣ ባርኔጣ የማይለያቸው አማርኛ አቀላጥፈው የሚያውቁ ዕድላም ሰው ናቸው። ሰለ አበሻ ሲናገሩ <<አበሻ ሥራ አይወድም።አበሻ ሠነፍ ነው።ለዚህ ነው ሃብታም የማይሆነው እንደኔ>>ይላሉ።
….
ቱሉ ፎርሳ በወር ሠላሳ አምስት ብር ያገኛል።ያ ደመወዝ ነው። ቱሉ ፎርሳ ሲሏችሁ ፎርሳ የአባቱ ስም እንዳይመስላችሁ።አይደለም።የወፍጮ ቤት ሥራ አታውቁትም እንዴ?ስንዴ በካሚዮን ይመጣል። ከካሚዮን ወደ መጋዘን ይጋዛል።ከመጋዘን ወደማንጠርጠሪያው የወንፊት ሞተር ቤት ይወስዳል።ከዚያ ይታጠባል።ከዚያ በሞተር ይደርቃል። ከስንት ጣጣ በኋላ ይፈጫል። ዱቄት በጆንያ እየታሰረ ወደ ቡኮ ክፍል ይተላለፍል።ይህንን ሁሉ የሚያደርገው የሰው ትከሻ ነው።ካሚዮን ሲመጣ ካቦው ሰው ይጠራል እንዲያወርዱ፤ <<አንድ ሁለት ፎርሳ ….>>ከመኪናው ላይ ኩንታሉን እየተሸከሙ ወደ መጋዘን ትንንንን…..
.
እና በስራ ቱሉን የሚያህል የለም። ኩንታል ተሸክሞ ሲበር ጭብጥ ላባ የያዘም አይመስልም። ሁል ጊዜ በጩኸት <<አንድ ሁለት ፎርሳ ….>>ይወዳል ።ለዚህ ነው ቱሉ ፎርሳ ተብሎ የቀረው እንጂ ያባቱ ስም ሆኖ አይደለም።
..
የቱሉ ሚስት ጠንፌ ነው የምትባለው። እንጀራ ለመግዛት ጉልት የሄደ ሁሉ ጠንፌን ያውቃል። መሽት ሲል ወደ ጉልት ብቅ ያለ ጠንፌና የእንጀራ ሰፌዷን ይለምዳል። መሸት ሲል የቀን ሠራተኞች ወደቤታቸው ይመጣሉ። እግረ መንገዳቸውን እንጀራ ይገዛሉ ሲመሽ የእንጀራ ገበያ ይደራል።
..
<<እሲኪ እንጀራው?>>ይላል ጠጋ ይልና።
<< ይኸው ወርቅ የመሰለ እንጀራ >>ይባላል።
<< ጤፍ ነው ቅይጥ ይላል ላፉ።>>
<< ንጹሕ የበቾ ጤፍ >>ተብሎ ይነገረዋል።
ጠንፌ ዘንድ ግን ብዙዎቹ እንዲያ ብለው አይጠይቁም። ብዙዎቹ ስለሚያቋት ዝም በለው ነው የሚገዟት አንዳንዴም ከተጠየቀች።
<< ጤፍ ነው ?>>
<< ትንሽ ዘንጋዳም አለበት >>

የቀን ሠራተኞች ላፋቸው ነው የሚጠይቁት። ያገኙትን ነው የሚገዙት። የሚገርመው ነገር የቀን ሠራተኞቹ ወንደላጤዎች ናቸው።የቀን ሠራተኞቹ ወጥ አይሠሩም። የቀን ሠራተኞቹ ብዙ ሆነው በትንሽ ቤት ውስጥ ነው የሚኖሩት።ታዲያ ለምን ዳቦ(ሞፎ)ገዝተው አይበሉም?ሞፎ ወጥ አያስፈልገውም። ሞፎ የወንደላጤ ምቹ ምግብ ነው። ግን የቀን ሠራተኞቹ እንጀራን ይመርጣሉ። ደርቅ እንጀራ ማላመጥ ደስ ይላቸዋል። ምንአልባት የቀድሞ ቤታቸውን ፣ የወትሮ ትዳራቸውን የሚያስታውሳቸው እየመሰላቸው ይሆናል።እንጀራ የወደፊቱ የተስፋ ምልክት እየመሰላቸው ይሆናል።
..
ጠንፌ አንድ ሃያ አምስት ዓመት ይሆናታል።ጠንፌ ከሁለት ዓመት በፊት ቱሉ ፎርሳን አገባች። በፊትም ከአያቷ ጋር ስትኖር የመንደር እንጀራ ጋጋሪ ነበረች፡፤እንጀራ መጋገር እንዴት ዓይነት ሥራ መሰላችሁ?አንዱ ቤት ሰላቢ ነች ይላሉ፣ ሌላ ቤት ማገዶ አይመክታትም ይላሉ፣ ሌላው ቤት እንጀራ ታወፍራለች ፣ ሌላው ቤት ታሳሳለች……..ጣጣ ነው። በመጨረሻ አያቷ ሲሞቱ ጋግሮ ከማብላት ይልቅ (በሦስት ብር ተቀጥሮ )ጋግሮ
መሸጥ ይሻላል ብላ በነጋዴነት ተጠቃለለች፡፤ከቱሉ ጋር የተዋወቁት በእንጀራ ደንበኝነት ነው። ሆሆይ!!ይሄ ደግሞ እራሱን የቻለ ታሪክ እኮ ነው።

ታዲያ ጠንፌ ወንድ ልጅ ወለደች። ልጁ ደግሞ ጤና የለውም፤ እሷንም ጤና ነሳት እቴ። የእንጀራ ንግዱም አላዋጣ አለ እንደ ዱሮ እርካሽ ዱቄት ፍለጋ መንከራተት አለ፣ ማገዶ ፍለጋ አገር ጥሎ መሄድ አለ።…እረ ስንቱ ።በዚህ ላይ ልጇ ጤና የለውም ። ባሎች ሁሉ ሚስቶቻቸውን ይማታሉ።

ባሎች ሁሉ ይሰክራሉ።ቱሉ ግን አይማታም ፣ አይሰክርም ፣ ከጠንፌ ምንም አይደብቅም።አምላኩ ጠንፌ ናት ።ያለ ጠንፌ ምን ሕይወት አለውና!ጠንፌም ባሏን ትወዳለች ፣ ታከብራለች።
– ጠንፌ
– አቤት
– ዛሬ ደመወዝ ተቀብዬ ከጓደኞቼ ጋር ጠላ ቤት ገብቼ ስልሳ ሳንተም አጠፋሁ።
– ደግ አረክ። ጠንፌ ቀና ብላ አታየውም ። ጠንፌ ለቱሉ ቱሉ ለጠንፌ የተፈጠሩ ይመስላሉ። ትሳሳለታለች።
– ጠንፌ ዛሬ ደመወዝ ተቀበልኩና ስመጣ ሉካንዳ ቤት ገብቼ የሃምሳ ሳንቲም ሥጋ ገዛሁልሽ።
– ጥሩ አረክ።
– ከዚያ በፊት አማረኝና አንድ ብርሌ ጠጅ ጠጣሁ። ምነው ጠንፌ ከፋሽ እንዴ?
– እኔቴ።
.
ቱሉ ሚስቱን ትኩር ብሎም አያያትም። የምትሟማ ይመስለዋል። ይሳሳላታል። ታዲያ ልጁ እያደር ይታመም ጀመር። በተወለደ በአስር ወሩ የጠና ሕመም ታመመ። ይቃትት ጀመር። ያጣጥር ጀመር።
<<ሀኪም ቤት ውስጂው >>ይላሉ ጎረቤቶቹ ።
<< የትኛው ሀኪም ይሻላል?>>
<< አሮጌው አውሮፕላን ጣቢያ ያለው ጥሩ ነው። >>
<< እሺ እስቲ >>ትላለች ጠንፌ ።
ለበሏ ግን አትነግረውም። ምን ብላ ትንገረው ? የቤት ኪራይ አስር አራት ብር ፣ የቤት ጣጣ ሌላውን ይወጣዋል። ምን ብላ ትንገረው ?
.
እንጨቱ ውድ፣ እህሉ ውድ፣ የኩራዝ ጋዝ እንኳ ካቅሙ ዱሮ ሁለት ፍራንክ የሚሸጠው ዛሬ በአራትም ፍራንክ አይገኝም። ሁሉ ቀጥሏል። የረከሰ ቢኖር የሰው ነፍስ ነው። ታዲያ ምን ብላ ትንገረው ? ልጁ ጠናበት ። የሰው አፍ ደግሞ አይጣል ነው። <<በቅሎ ግዙ ግዙ ፤ አንድ ጨው ላይገዙ >>ማለት ያ ነው።
.
<< ኸረ ባካችሁ ሀኪም ውስዱት ?>>አሉ አንድ ቀን ማታ ሊጠይቁ የመጡ የመንደር አሮጊት ።
<< የትኛው ይሻላል ?>>አለች ጠንፌ ።
<< የውሬሏ ጥሩ ናት ሲሉ ሰምቻለሁ። >>
<< እንዲህ እንዳይመስልሽ ፣ አሁን የዛች የቀለሟ ልጅ ታማባት ፣ እንዲው በጠና ተይዛባት እዛ ሄዳ እንደው ባንድ መርፌ አዳነቻት። ደግሞ ዋጋው ትንሽ ነው። ሁለት ብር ከፍሎ ካርኔ መቁረጥ ነው በቃ ። >>
.
ጠንፌ ልቧ ስንጥቅ አለ። የውሬሏ ሀኪም ሁለት ብር። ሲመሽ የታመመው ዕፃን ከቶውንም ጡት መሳብ ተሳነው። ያ የፈራችው ሊመጣ ነው። ወልዶ መቅበር ላይቀርላት ነው።አዬ ሰው መሆን።

ቱሉ? ምን አልሺኝ ጠንፌ ?
ሁለት ብር አለህ?
አይ አሁን?……እንዴት ?እኔ ሁለት ብር ነው ያልሺኝ?
አወን ሁለት ብር ለውሬሏ ሀኪም የሚከፈል።
ሀኪም መሄድ ያስፈልጋል?
አታየውም ትኩሳቱን ??”
“እ …..ይሁን….ጠዋት እበደራለሁ፣ ግድ የለም ጠንፌ አታስቢ። ”
..
ሕፃኑ መቃተቱን ቀጠለ። ከቶውንም ማልቀስ እያቃተው ሄደ። ጠንፌ ለባሏ የሚበላውን ሰጠ

Source: https://www.facebook.com/eprpinfo

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *