News

በቀጣይ ምርጫና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁኔታ ላይ ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)

 

ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)
Ethiopian People’s Revolutionary Party (EPRP)

 

 

ግንቦት 2012 ዓ.ም.

በኢትዮጵያ የፖለቲካዊ መስተዳድሮች መነሳትና መውደቅ የታሪካችን አንዱ መገለጫ ከሆነ ሰነባብቷል። አሰያየማቸውና ይዘታቸው ከውዝግብ የጸዳ ባይሆንም የሥርዓት ለውጦችም ተደርገዋል። የአፄ ሃይለ ሥላሴን መንግሥት የተካው ደርግ የኢትዮጵያን ህዝብ ለ 17 ዕመቶች ካዳሸቀ በኋላ፣ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግሥት ደግሞ ለተጨማሪ 27 ዓመቶች አመሰቃቅሎታል። ለ 27 ዓመታት ህወሓት/ኢህአዴግ በጫነው አምባገነናዊ አገዛዝ ስንማቅቅ ቆይተን ከአፈናና የጭለማ አገዛዙ መሀል ያልተጠበቀ ድምጽ በመሰማቱ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ሊመጣ ነው ብሎ ያልፈነደቀ አልነበረም፡፡ ለኢትዮጵያ ቀን ሊወጣላት ሕዝቧም የዲሞክራሲ በር ሊከፈትለት፣ የታየው ጭላንጭልም ብርሃን እንዲሆን ሲጠብቅ፣ የተሰጠው ምስጋና ከጆሮ ሳይጠፋ፣ ያጨበጨበባቸው እጆች ሳይታጠፉ፣ የታለመውም ህልም ሳይፈታ፣ በነፃነት ለመሮጥ ያኮበኮቡ እግሮች ሳይራመዱ … የበቀለባት ዘረኝነት እና የጥላቻ ትርክት፣ ግለኝነት፣ የስልጣን ጥማት፣ የአንደበትና የተግባር ያለመስማማት፣ ወዘተ… የሕዝቧን እንደገና መፈናቀል፣ የዜጎችን መገደል፣ መራብና መጠማት፣ መታገትና ደብዛ መጥፋት፣ ሰቆቃና እንግልት አስከትለዋል፡፡

ሀገራችን ከኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች በተጨማሪ፣ ውስብስብ የፖለቲካና የፀጥታ ችግሮች ዛሬም አሏት። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፣ በእነዚያ ችግሮች እየተናጠች ባለችበት ወቅት፣ ዓለምን ያንበረከከው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተከስቶ ሀገር ቀውጢ ሁኔታዎች ዉስጥ ገብታ የአስቸኳይ ጊዜ እወጃን ግድ ብሏል፡፡ ይህም ከአገራዊ ምርጫው ጊዜ ጋር በመግጠሙ የተነሳ ከሁለት ዓመታት በፊት የፈነጠቀው የተስፋ ጭላንጭል ብርሃን እንደገና ወደ መጨለሙ የሚሄድ አስመስሎታል፡፡ ኢትዮጵያ ልትነሳ ነው ሲባል ወደ መንሸራተት እየተጓዘች፣ ከድጡ ወደማጡ እንዳንዘፈቅ አጥብቀን ልናስብ፣ በሙሉ የሀገርና የወገን ፍቅር ተነሳስተን ሁኔታዎችን ልንመረምር ይገባናል፡፡

ዛሬ ሀገራችን አጣብቂኝ ውስጥ ገብታለች፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምድራዊ ተስፋ በማጣት ወደ ሰማይ አብዝቶ ይመለከታል፤ ለዚያውም በተለመደ መንገድ የአምልኮ ሥርዓቱን መፈጸም ባለመቻሉ በተሰበረ ልብ፣ ሁሉም በየዕምነቱ፣ በምልጃና በጸሎት ቀንና ሌት ይተጋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ያገባናል ብለን የተደራጀን ፖለቲከኞችም “የልም ይዣት” ለሆነ የፖለቲካ ሥልጣን ሽኩቻ ውስጥ ልንገባ፤ ስልጣን በእጁ ያለውም ያንን ሥልጣን ወገንን ከመታደጊያነትን ሀገርን ከማቆያነት ውጭ ሊጠቀምበት አይገባም እንላለን።

እርግጥ ነው የማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ትግሉ የሚካሄደው፣ የመጨረሻው ዓላማው የፖለቲካ ስልጣን መያዝና የፖለቲካ ራዕዩን ለመተግበር መቻል ነው። ክርክሩ የሚጦፈው ያን የሁሉን ፖለቲከኛ ዓላማዎቹን ለመሳካት የሚያስችለውን በትረ ስልጣን ለመጨበጥ ነው፡፡ ዛሬ ዓለም በደረሰችበት የዲሞክራሲ አስተሳሰብ ስልጣን የሚገኘው ከሕዝብ ድምጽ ነው፤ ለዚህ ደግሞ የሕዝብን ልብ ማሸነፍ ግድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እስከዛሬ ባለፈችበት ታሪክ የሕዝብን ልብ አሸንፎ ወደ ስልጣን የወጣ መንግሥት ለማየት አልታደለችም፡፡ በሕዝብ ይሁንታ ያልተያዘ ስልጣንን በቀላሉ የሚለቅ/የለቀቀ መንግሥት አይታወቅም፡፡ በአንፃሩ ይህ አማላይ በትረ ስልጣን በበርካታ ሀገሮች ሃላፊነት በማይሰማቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች እጅ ሲገባ ህዝብን መበደያና ሀገርንም መጉጅያ ሊሆን ስለሚችል፣ ዜጎች ሁልጊዜም የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዳይጨፈለቁ፣ እንዳይዳመጡ ነቅተውና ተደራጅተው ሊታገሉ ይገባል። አምባገነኖች እንዲበቅሉ የሚያደርገው የህዝቡ መዘናጋት ነውና! የፖለቲካ ሥልጣንን ወገንና ሀገርን ለመጥቀሚያ ሳይሆን፣ ለራስ መጠቀሚያነት የሚሹ ካሉ፣ እንዳይደርሱበት ማድረግ የህዝቡ ፈንታ ነው።

ለስልጣን መሮጥ ምንም ስህተት የለውም፤ ነገር ግን ሀገር እና ሕዝብ ከዚህ ሩጫ ያተርፉ ዘንድ ስልጣን ለምን? ለማን ምን ለማድረግ?… የሚሉ ጥያቄዎችን በሚገባ መመለስ ያስፈልጋል ብሎ ኢሕአፓ ያምናል፡፡ ፖለቲካን እንደ መኖሪያ ሥራቸው አድርገው የሚጓዙ እንዳሉ ብናውቅም፣ በፖለቲካ መሳተፍ ለግል ጥቅም መሆን የለበትም ብሎ ኢሕአፓ ያምናል። ፖለቲካ እንደማንኛውም ማኅበራዊ ሳይንስ፣ በዕውቀት ላይ ሊመሠረትና የሕዝብን ጥቅም ለማራመድና ሀገርንም ለማሳደግ በሚያስችሉ ዐውራ ሃሳቦች፣ መርሆዎች፣ ላይ ተመሥርቶ መመራት አለበት። ከግል ፍላጎት ጋር ሲቆራኝ ፖለቲካ ግቡ እጅጉን ይኮማተራል። ተዋናዮቹንም ያሳንሳቸዋል። ስለሆነም፣ በጊዜያዊ የማስመሰል ትርክት በሕዝብ ላይ የሚጫን ፖለቲካ ሊበቃን ይገባል ይላል ኢሕአፓ፡፡ ከመወነጃጀልና ከመጠላለፍ የራቀ ፖለቲካ መፍጠርም ይገባናል፡፡

ዛሬ ሀገራችን ዉስጥ የምናየው ግን ወደዚህ ትክክለኛ መንገድ የሚወስድ አይደለም፤ በገዥው ፓርቲ የሚነገረው የዲሞክራሲ አሠራር መሬት ካለው ዕውነታ ጋር የሚሄድ አይደለም፤ ይልቅስ ግልጽነትንና መከባበርን በአንደበትም ሆነ በተግባር ማሳየት ያለመቻሉን ያመላክታል፡፡ በሌላ በኩል የተወሰኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ማቅረብ፣ ሌሎችን ማግለል፣ ትክክለኛ አሠራር አይደለም። ሁሉም በሀገር ጉዳይ ላይ ያገባቸዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚገባቸው ክብር አለ፣ ይህንን ማወቅ ተገቢ ነው። የኢትዮጵያ ጉዳይ የሁላችንም እንጂ የገዥው ፓርቲና የጥቂቶች አይደለም። በምን መስፈርት እንደሆነ ግልጽ ባልሆነ መንገድ የተመረጡ ጥቂት ፓርቲዎችን በመጥራት በታላቅ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ መምከርና መወሰን በምንም መልኩ ዲሞክራሲያዊ ሊሆን አይችልም፡፡ ሰሞኑን የተስተዋለው ተፎካካሪነት፤ ፓርቲዎችን በማሳተፍ ስም የተመረጡ ጥቂቶችን ጠርቶ፤ ብታምኑበትም፣ ባታምኑበትም ልትቀበሉ የሚገባችሁ ውሳኔ ይህ ነው በማለት የአንድ ፓርቲን ሀሳብ መጫን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ይጣፍጥም ይምረር የሌሎችን ሃሳብ ከልብ መስማት፣ ጊዜ ወስዶ መነጋገርና ወቅቱን የጠበቀ የጋራ መፍትሔ መስጠት ዲሞክራሲያዊ አሠራር መሆኑንና ከመጨረሻ ሰዓት ወከባ እንደሚታደግ ባለማወቅ የተከሰተ አይደለም፡፡

ኢሕአፓ ኢትዮጵያን የሚያፈቅሩና የሚወዱ ዜጎች የሚወስዷቸው ማናቸውም እርምጃዎችና ውሳኔዎች፣ የሩቁን እንጂ በዕለት ከዕለቱ ላይ ብቻ የማያተኩሩ፣ ሀገሪቱን አሁን ከምትገኝበት ሁኔታ ወደ ከፋ ደረጃ የማይወስዱ፣ ከቡድናዊ የሥልጣን ፍላጎትና ጥቅም ይልቅ ለሀገርና ለሕዝብ አንድነት ቅድሚያ የሚሰጡ፣ ሀገሪቱ ወደሌላ የጦርነት አዙሪት ውስጥ እንዳትገባ፣ ሰላም እንዲሰፍን የሚጋብዙ ሊሆኑ ይገባል ብሎ ያምናል ፡፡

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንደሚያውቀው ኢሕአፓ ዘመናዊ የፖለቲካ አመለካከትን በመያዝ፣ ግልጽ የፖለቲካ ጥያቄዎችን በማንሳት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በአደባባይ ወጥቶ ሕዝባዊ ጥያቄዎችን ያሰማ ፓርቲ ነው፡፡ መሬት ለአራሹ እንዲሠጥ የሚለውን ትልቅ የፖለቲካ ጥያቄ በመጀመሪያ ያቀረበ፣ የኢትዮጵያ ተማሪዎችን ንቅናቄ ወደ ተደራጀ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አሳድጎ፣ በኋልም ፓርቲ መሥርቶ፣ እስከ ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም ጥያቄ ደረስ ይዞ የዘለቀ፣ እጅግ የከፋ መስዋዕትነት የከፈለ ሀገራዊና ኅብረብሔር ፓርቲ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ላቆጠቆጡ በተለይ ሕብረብሔራዊ ፓርቲዎች ምንጭ የሆነውም ኢሕአፓ ነው፡፡ ኢሕአፓ ለአፍታ እንኳን በኢትዮጵያ ሕልውና ላይ ተደራድሮ የማያውቅ እና ለድሆችና ለተገፉ ሁሉ ለዘመናት የቆመ ነው፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት በስደት ቆይታው ኢትዮጵያ ውስጥ ለተካሄደው ትግል የጀርባ አጥንት ሆኖ የቆመ ፓርቲ መሆኑንም ብዙዎች የሚመሠክሩለት ሲሆን በአገር ውስጥም የሕቡዕ ትግሉን ለአፍታ እንኳን አቋርጦ አያውቅም፡፡

ሬም ኢትዮጵያ ከገባችበት አጣብቂኝ ትወጣ ዘንድ የበኩሉን ከማድረግ ወደኋላ የማይለው ኢሕአፓ፤ ገዥው ፓርቲ ያቀረባቸው አራት አማራጭ መንገዶች በመጨረሻም በህዝብ እደራሴዎች ምክርቤት የፀደቀው አማራጭ ብቸኛ መንገድ ነው ብሎ አያምንም፡፡ ኢትዮጵያ በሰከነና በበሰለ የፖለቲካ ደረጃ ላይ የምንገኝ ፓርቲዎች ብንኖራት ኖሮ ሀገራችን ሠላም የሠፈነባት፣ የሕግ የበላይነት የተረጋገጠባት፣ በሥልጣን ላይ ያለው የፖለቲካ ድርጅትም በነፃ፣ ርትዓዊና ተዓማኒነት ባለው ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ወደ ሥልጣን የመጣባት፤ ስለሆነም ማንም ሥልጣኑን ሊቀናቀነው የማይገባ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ለየት ያሉ አማራጮችን መፈተሽ በተቻለ ነበር። ኢሕአፓም ትክክለኛው መፍትሔ ፖለቲካዊ መሆን ይገባዋል ብሎ ገዥውን ፓርቲና መንግሥትን በሞገተ ነበር። ነገር ግን የሰከነና የዳበረ የፖለቲካ አሠራር በሌለበት ሁኔታ ሊያስኬዱ ይችላሉ የሚባሉ ሌሎች መንገዶችን መሞከር ደግሞ ወደ ከፋ አደጋ ሊያስገባ እንደሚችል በመስጋት ኢሕአፓ ቆም ብሎ ማሰብን መርጧል፡፡

በመሆኑም አንድ እግሩን አስገብቶ፣ ዜጎቻችንን መግደል የጀመረውን የወረርሽኝ ፈተና መወጣት ከሁሉ በፊት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ሁላችንም ልናምን ግድ ነው ይላል ኢሕአፓ። ያለሕዝብ ሀገር አይኖርም፣ ምድረ በዳ እንጂ!? ያለሀገር ደግም ፖለቲካ በዓየር ላይ የሚደረግ አክሮባቲክስ አለዚያም ፌዝ ነው የሚሆነው።

ስለዚህም፡

  1. የግልና የፓርቲ አጀንዳዎቻችንን ለጊዜው ወደጎን በማስቀመጥ የሀገርን ህልውና እና የህዝብን ሕይወት መታደግ የውዴታ ግዴታችን መሆኑን አበክረን እንገልፃለን፡፡ በዚህ ቀን ያበቃል ብሎ መወሰን የማይቻለው የኮቪድ 19 ችግር እስከሚያበቃ ከዚያም እስከ ምርጫው ድረስ አሁን ያለው መንግሥት እንዲቀጥል ኢሕአፓ ስምምነቱን ይገልፃል፡፡ በእያንዳንዱ ሀገርን የማዳን እና የሕዝባችንን ጤንነትና ሕይወት የመታደግ ሥራ ውስጥ ከመንግሥት ጎን እንደምንሰለፍ ስንገልጽ መንግሥትን ለመገዳደርም ሆነ የተጠቀሱትን ሀገራዊ ቅቡልነት ያላቸው ተግባሮች ለማደናቀፍ የሚወሰዱ እና ሀገርን የሚጎዱ ማናቸውንም በእልህና በማን አለብኝነት ላይ የተመሠረቱ እርምጃዎችን እንቃወማለን፡፡
  2. የወረርሽኙ መስፋፋትና እድገት፣ እያደረሰው ያለው ጉዳት፣ እየቀነሰ መጥቶ፣ ሁኔታዎች ፍፃሜውን ሲያመላክቱ፣ ቀጣዩ ምርጫ መቼ እንደሚካሄድ በሚደረገው ውሳኔ ላይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚኖራቸውን ተሳትፎ ባለመገደብ፣ ገዥው ፓርቲ “እኔ በምቀድላችሁ ቦይ ፍሰሱ” ከሚል አካሄድ በተላቀቀ መልኩ፣ ከራሱ ውጭ ካሉት የፖለቲካ ሃይሎች ጋር በዕውነተኛ ተፎካካሪነት ላይ የተመሠረተ ምክክር እንዲያደርግና የጋራ ውሳኔ እንዲሰጥ አበክረን እንጠይቃለን፡፡
  3. በዚህ ሂደት ውስጥ፣ ወረርሽኙ ተግትቶ፣ ሀገራችንም ህልውናዋን ጠብቃ፣ የምርጫ ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት፣ ገዥው ፓርቲ እንደተለመደው የመንግሥት ስልጣኑን ለፖለቲካዊ ፍጆታ ማዋሉን እንዳይቀጥል አበክረን እናሳስባለን፡፡ በተፈጠረው አጋጣሚ በመጠቀም የሚያካሂዳቸውን የምረጡኝ ዓይነት ስውር ቅስቀሳዎች እንዲያቋርጥና የተጣለበትን ሀገር የማዳን ሃላፊነት እንዲወጣ እንጠይቃለን፡፡ ይህንን ስንል በከፍተኛ የስልጣን እርከን ላይ ብቻ ሳይሆን እስከወረዳ ያለውን መዋቅርም በማካተት ነው፡፡ መንግሥት አስቸኳይ/አሳሳቢ ጉዳዮችን በተመለከተ “አጣርተን እንገልፃለን” ከማለት ባለፈ በተግባር ሲገልጽ አይደመጥም (ለምሳሌ ደምቢዶሎ እንደታገቱ ደብዛቸው ስለጠፋው ተማሪዎች) በመሆኑም ተመሳሳይ ጉዳዮችን ለህዝብ የማሳወቅ ልምዱን እንዲፈትሽ ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም በየወረዳው በሚንቀሳቀሱ አባሎቻችን ላይ የሚደርሰው መዋከብ፣ በአንዳንድ ሥፍራዎች የሚያጋጥሙ እስራቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ፤ የታሰሩትም እንዲፈቱ እንጠይቃለን፡፡
  4. በመጨረሻም የሀገርን አንድነትና የሕዝብን ደህንነት በማስቀደም ፖለቲካ ውስጥ አብሮ ለመሥራት ከሚፈልጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ጋር ለመሥራት ኢሕአፓ ሙሉ ፈቃደኛ መሆኑን እንገልፃለን፡፡

ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!

Share10

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *