nile
Opinion

ተከዜን ወደ ፖርት ሱዳንና ሪያድ (ሳዑዲ ዓረቢያ) ?

በገረመው አራጋው – Gheremew Araghaw

ከፋይል ማህደር ፟፟ ከ7 ዓመት በፈት ለንባብ የቀረበ ስለውቅቱ ሁኔታ ምን ነብር ያልው፡፡

ግብፅ እጅግ ውድ የሆነውን ውኃ በበረሃ ሩዝና ሸንኮራ አገዳ እያመረተች እንዲሁም ልቅ የሆነ የጎርፍ መስኖ በመጠቀም ውኃን ለትነት እያጋለጠች እንደምታባክን በአደባባይ የሚታይ ድርጊት ነው፡፡ የሆነው ሆኖ የናይልን ወንዝ ከተፈጥሯዊው መስመሩ እያወጡ ወዳሰኛቸው ቦታ መውሰድ ለግብፃውያኑ የተከለከለ አይመስልም፡፡ ሌሎች የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ያን እናድርግ ብለው ቢነሱ የግብፃውያኑ መልስ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ ሆኖም ግን “የአዲሱ ናይል ሸለቆ ፕሮጀክት” ብለው የሚሠሯቸው ሥራዎች ቶሽካም ሆነ አል ሰላም ሁሉም ናይልን ከተፈጥሯዊው መፍሰሻው የሚያስወጡ ናቸው፡፡ ለምሳሌ አል ሰላም ቦይ በአንዋር ሳዳት ዘመን ሲወጠን ዋና ዓላማው የናይልን ውኃ ከሲና በረሃ አሳልፎ ወደ ኔጂብ በረሃ በመውሰድ ለእስራኤል መስጠት ነበር፡፡ ደፋሮቹ ግብፃውያን በ1980ዎቹ መጨረሻና በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ አንዱን የናይል ታላቅ ቅርንጫፍና ገባር የተከዜን (አትባራ) ወንዝ ጠልፎ ወደ ሪያድ ሳዑዲ ዓረቢያ በቀይ ባህር በኩል ለማሻገር ዕቅድ እንደነበራቸው ዳንኤል ክንዴ የተባሉ ምሁር እ.ኤ.አ በ1999 ባወጡት መጣጥፍ እንዲህ ገልጸውታል፡፡

“በሰዓት 4.5 ሚሊዮን ሊትር የሚሆን ውኃ ከአትባራ (ተከዜ) በመጥለፍ ወደ ቀይ ባህሯ የወደብ ከተማ ፖርት ሱዳን ከዚያም ወደ ሪያድ ሳዑዲ ዓረቢያ በቀይ ባህር በኩል ለማሻገር በግብፅ ሙሉ ድጋፍ የሁለት ቢሊዮን ዶላር ሥራ በአርቃቂዎች ተጀምሮ ነበር፡፡ እንደ ዕቅዱ ከሆነ ሱዳን በሁለት መልኩ የምትጠቀም ሲሆን አንድም ከአትባራ (ተከዜ) በስተምሥራቅ የሚገኘውን ጠፍ መሬት ለማልማት የሚያስችላት ሲሆን፣ እንዲሁም በቀይ ባህር ዳርቻ ያሉ ፏፏቴዎችን በመጠቀም በሰዓት ከ7,000 ኪሎ ዋት በላይ ኤሌክትሪክ ለማምረት ያስችላታል፡፡ ሳዑዲዎቹም ግብፅንና ሱዳንን (በዚህ ፕሮጀክት ምክንያት) ለሚያጡት የመስኖ ውኃ በግብርና ካፒታል ኢንቨስትመንትና በኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች ያካክሱታል፡፡”

ፕሮጀክቱ ተጠናቆና እንደ ዕቅዱ ሄዶ ቢሆን ኖሮ የሳዑዲ ዓረቢያዋ ከተማ ሪያድ ለመጠጥ የሚሆናትን ውኃ ከተከዜ (አትባራ) ልታገኝ ነበር ማለት ነው፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ካለው የውኃ እጥረትና ድርቀት አንፃር ይህ ፕሮጀክት ለሳዑዲዎች ታላቅ ገነትን የመፍጠር ያህል ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ይህ ፕሮጀክት ተግባራዊ አልሆነም፡፡ ሆኖም ግን ካለው የሳዑዲዎች የውኃ ፍላጎት አንፃር ጠፍቷል ማለት ይከብዳል፡፡ ሆኖም ይህን ዕቅዳቸውን አዳፍነውት ሊሆን ይችላል፡፡ ምንም ያስቡ ምን ግን የውኃ ፖለቲካ ተንታኙ ወዳጄ አቶ ወንድወሰን ሚቻጎ እንዳሉት የዚህ ፕሮጀክት ዕቅድ ይዳፈንም ሸልፍ ላይ ይቀመጥም ሊሳካ አይችልም፡፡ እንደ ዋና ምክንያት የሚያቀርቡትም አንድም ኢትዮጵያ ተከዜ ላይ የገነባችው ግድብ ግብፅና ሱዳን ወደ ሪያድ ውኃ እንላክ ቢሉ ከየትም ሊያመጡ እንደማይችሉ ያስታውሳቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ቀዳዳውን ከደፈነችው ደፈነች ነውና፡፡

ሁለትም የላይኛው ተፋሰስ አገሮች በአጠቃላይ የናይልን ውኃ ከተፈጥሮ መፍሰሻ መስመሩ ለማስቀየስ የሚደረግን ማናቸውም ድርጊት መቃወማቸው አይቀርም፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ግን የኢትዮጵያና የሌሎቹ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ከሚገኙበት አንፃራዊ ሰላም አኳያ በዓባይ/ናይል ወንዝ ላይ የራሳቸውን ፍላጎቶች ለማሟላት የልማት ሥራዎችን መጀመራቸው፣ በታችኞቹ ተፋሰስ አገሮችም ሆነ ከሩቁ የናይልን ወንዝ ለመጠጣት ምራቃቸውን ሲውጡ ለነበሩ አገሮች (ሳዑዲ ዓረቢያ) በቀላሉ የሚዋጥ አይሆንም፡፡ ስለዚህም ያገኙትን ማናቸውም አጋጣሚ በመጠቀም የዓባይ አውራና እናት የሆነቸውን ወደ 86 በመቶ ውኃ የምታበረክተውን ኢትዮጵያን መወረፍ የሚያስገርም አይደለም፡፡ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ምንጊዜም ቢሆን ቋሚ ጥቅም እንጂ ቋሚ ወዳጅ መፈለግ ሳር ውስጥ መርፌን መፈለግ ያህል ነው፡፡ እንግዲህ እንደኔ እይታ የምክትል መከላከያ ሚኒስትሩ ንግግር ብሶት የወለደው ጉርምርምታ ሲሆን ካላቸው ፍላጎት አንጻር መንግሥታቸውን አይወክልም ለማለት አያስደፍርም፡፡

ይህም የዓረቡን ዓለም ራስን እንደ አንድ የመቁጠርና ግብፅ ኢትዮጵያን ከሌላው ዓለም ለመነጠል ከምታደርገው ጥረት፣ እንዲሁም ኢትዮጵያና ሳዑዲ ዓረቢያ ካላቸው ጂኦፖለቲካዊ ሽኩቻና በምሥራቅ አፍሪካ ላይ ካላቸው የጥቅም ግጭት አንፃር የሰውየው ንግግር ተመክሮበትና ተዘክሮበት የተወረወረ እንጂ፣ በከንቱና በድንገት የተወረወረ ቃል አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር አንዳንድ ነጥቦችን እንደሚከተለው እናያለን፡፡

ዓባይ ኢትዮጵያና ሳዑዲ ዓረቢያ ከሚለው ፅሁፍ የተወሰደ
በዘሪሁን አበበ ይግዛው
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው zerihun.yigzaw@graduateinstitute.ch ማግኘት ይቻላል፡፡

posted by Gheremew Araghaw

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *