የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግብፅ የህዳሴ ግድብን እንደምታፈርስ መናገራቸውን ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደርን በመጥራት ማብራሪያ ጠይቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ ተቀማጭ የሆኑትን የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ሬይኖርን የጠሩ ሲሆን ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከሱዳንና ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ጋር በስልክ ባደረጉት ውይይት ስለ ግድቡ የተናገሩትን ነገር ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቀዋቸዋል።
ዶናልድ ትራምፕ በስልክ ንግግራቸው “ግብፅ ግድቡን ታፈነዳዋለች” ከማለት በተጨማሪ ኢትዮጵያ የገነባችው የህዳሴ ግድብ “ውሃ ወደ ናይል እንዳይፈስ ያቆማል ማለታቸው ከእውነት የራቀና ስህተት ነው” ያሉት አቶ ገዱ “የህዳሴ ግድብ የናይልን ፍሰት አያስቆመውም” ብለዋል።
አቶ ገዱ አክለውም በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል እንዲህ ጦርነት የሚያጭር ነገር ከተቀማጭ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መሰማቱ የሁለቱን አገራት የቆየ ግንኙነትና አጋርነት አያሳይም እንዲሁም አገራቱን በሚገዛው የአለም አቀፍ ህግም ተቀባይነት የለውም ማለታቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ አመላክቷል።
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷ የመጣ ለማንኛውም ማስፈራራያ እንደማትንበረከክና አሁንም ቢሆን በአፍሪካ ህብረት በተጀመረው የሶስትዮሽ ድርድር ፀንታ እየሰራች መሆኑንም ለአምባሳደሩ መንገራቸውን ከውጭ ጉዳይ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትናንትናው እለት ጥቅምት 13፣ 2013 ዓ.ም ሱዳን እና እስራኤል ግንኙነታቸውን ለማደስ የደረሱበትን ስምምነት አስመልክቶ ከሱዳን ጠቅላይ ምኒስትር ዐብደላ ሐምዶክ እና ከእስራኤሉ ጠቅላይ ምኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ጋር በስልክ በተነጋገሩበት ወቅትም ነው የህዳሴ ግድብን ጉዳይን ያነሱት።
“ግብፅ በዚህ መንገድ መቀጠል ስለማትችል ሁኔታው አደገኛ ነው። ግብፅ የህዳሴ ግድብን ታፈነዳለች፤ አሁንም በግልፅ እናገረዋለሁ ግብፅ በድጋሚ ታፈነዳዋለች” በማለት በተደጋጋሚ የተናገሩት ትራምፕ “ስምምነት ለአገራቱ ባቀርብም ኢትዮጵያ ስምምነቱን ሳትቀበል ቀርታለች። አንደዚያ ማድረግ አልነበረባቸውም ይህ ትልቅ ስህተት ነው። በዚህም ምክንያት የምንሰጣቸውን ብድር አቁመናል። ስምምነቱን ካልተቀበለች በስተቀር ኢትዮጵያ ያንን ገንዘብ አታየውም ” ብለዋል።
“ውኃ ወደ ናይል እንዳይፈስ የሚያቆም ግድብ ገንብተዋል። ግብጽ ትንሽ በመበሳጨቷ ልትወቅሷት አትችሉም” በማለትም “ግብፅ የህዳሴ ግድብ እንዲገነባ መፍቀድ አልነበረባትም” በማለት ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
ይህንንም በማስመልከት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በግድቡ ዙሪያ የሚሰጡ ማስፈራሪያዎች ከመረጃ ክፍተት የሚነሱ፣ ውጤታማ ያልሆኑ እና የዓለም አቀፍ ሕግን የጣሱ ናቸው በማለት መግለጫ አውጥቷል።
የጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ ጽህፈት ቤት የትናንት ማታውን የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተያየት ተከትሎ ማለዳውን ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው ኢትዮጵያ ከግድቡ ግንባታ ጎን ለጎን የናይል ውሃ ፍትሃዊ ክፍፍል ላይ ያላትን ቁርጠኝነት መግለጿን አመልክቷል።
የጽህፈት ቤቱ መግለጫ እንዳመለከተው፣ ኢትዮጵያ ፍትሃዊ ወዳልሆነ ስምምነት ውስጥ እንድትገባ “የሚሰጡ ጠብ አጫሪ አስተያየቶች ተቀባይነት የላቸውም” ብሏል።
በተጨማሪም “ኢትዮጵያ ለማንኛውም ማስፈራሪያ አትንበረከከም እንዲሁም በቅኝ ግዛት ለተመሰረተ ውልም እውቅና አትሰጥም” በማለት አስፍሯል።
የፕሬዚዳንቱ ንግግር በርካታ ኢትዮጵያውያንን አስቆጥቷል፤ አስደንግጧል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ “የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ያደረጉት ንግግር በግድየለሽነት የተሞላ ነው። ይህንን በማለቴ አዝናለሁ ግን ፕሬዚዳንቱ ስለሚያወሩት ነገር አያውቁም። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን እንዲህ ባለ ኃላፊነት በጎደለው አስተያየት ፍራቻ አይገባቸውም። ታሪክ ሁሉንም ያስተምራል” በማለትም መልእክታቸውን በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።
Source: BBC Amharic