በአፋር ክልል
News

በአፋር ክልል የትምህርት ሚኒስቴር ሰራተኞችን ጨምሮ 10 ሰዎች የተገደሉት “በአሸባሪዎች” ነው ተባለ

በትናንትናው ዕለት ጥቅምት 17፣ 2013 ዓ.ም በአፋር ክልል ገዳማይቱ በምትባል አካባቢ በትምህርት ቤት ውስጥ የተገደሉት የትምህርት ሚኒስቴር ሁለት ሰራተኞች አሸባሪ በሚባሉ ኃይሎች እንደሆነ አቶ አህመድ ካሎይታ የአፋር ክልል ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አስታውቀዋል።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የመማር ማስተማር ሁኔታ ለመቆጣጠር የተሰማሩት የትምህርት ሚኒስቴር ሰራተኞች አቶ ሙላት ፀጋዩ እና አቶ አበባው አያልነህን ጨምሮ በክልሉ በደረሰ ጥቃት አስር ሰዎች ተገድለዋል።

በክልሉ ዞን ሶስት ገለሎ በምትባል ወረዳ፣ ሰርከሞና ቴሌ ቀበሌ በሚባል መንደር የሚገኙ የአርብቶ አደር ማሕበረሰብ ላይ ጥቅምት 16፣ 2013 ዓ.ም ከሌሊቱ 10 ሰዓት በተፈፀመ ጥቃት ስምንት ሰዎች ተገድለዋል።

አቶ አህመድ “የሽብር ጥቃት” ያሉትም ሴቶችና ህፃናት ላይ እንዳነጣጠረም ጠቅሰዋል። የትምህርት ሚኒስቴርም ሰራተኞች በጥይት መገደልም ከዚህ “የሽብር ጥቃት ብለው” ከሚጠሩት ጋርም የተያያዘ ነው ይላሉ።

በክልሉ የተለያዩ ግጭቶች እንደሚያጋጥሙ የሚናገሩት አቶ አህመድ እንዲህ አይነት “መሰል የሽብር ጥቃት” ሲያጋጥም ግን ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን ይናገራሉ። ከዚህ ቀደምም በባለፈው አመት በአፋምቦ ወረዳ ኦግኖ ቀበሌ በተመሳሳይ መልኩ ሌሊት ላይ ሴቶችና ህፃናት ላይ ያነጣጠረ “የሽብር ጥቃት ተፈፅሞ” መገደላቸውን ያስታውሳሉ።

ጥቃት የደረሰበት አካባቢ የኢትዮ-ጂቡቲ አውራ ጎዳናና አለም አቀፍ መተላለፊያ ድንበር እንደሆነም ይገልፃሉ። ጥቃቱን ያደረሱት አካላት ማንነትን በተመለከተ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄም።

በህገ ወጥ ንግድ (ኮንትሮባንድ) ተሰማርተው የነበሩና ያ እንቅስቃሴያቸው የተገታባቸው ኃይሎች “በአካባቢው የሚኖሩ የሶማሌ ኢሳ ጎሳ ማህበረሰቦችንም ከለላ በማድረግ” ህዝቡን እያጠቁ ይገኛሉ ብለዋል

“አሸባሪ ለየትኛውም አይወግንም እነሱን ከለላ አድርጎ ከመጣ የነሱን ሰላም ሊያውክ የሚችል ኃይል እንደሆነ ታውቆ እነሱም በነሱ ውስጥ አቋርጠው እዛ ቦታ ላይ ሽብር ሊፈጥሩ የሚችሉ ኃይሎችን ቀድሞ መከላከልና መቆጣጠር መቻል አለባቸው” ይላሉ።

በአካባቢው የሽብር ጥቃት እየተደጋገመ መምጣቱን የሚናገሩት አቶ አህመድ በቅርቡም በክልሉ በደረሰው የጎርፍ አደጋ ድጋፍ ለማድረግ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ልዑካኖችም ላይ በደረሰ ጥቃት የአንድ ፀጥታ ኃይል ህይወት ያለፈ ሲሆን አንዱም ተጎድቷል።

ልዑካኖቹ ድጋፋቸውን አድርሰው ሲመለሱ በፀጥታ ኃይሎቹ ላይ ባነጣጠረ ጥቃትም ህይወት መጥፋቱን አስታውሰዋል።

“አገሪቷ ላይ የመጣውን ለውጥ የማይደግፉና የሚፃረሩ ከውጭም የራሳቸው የሆነ ተልእኮ ያላቸው ኃይሎች አገሪቷ የጀመረችውን የብልፅግናና የአንድነት ጉዞም ለማደናቀፍ የሚሞክሩ ናቸው” የሚሏቸው ኃይሎችም በክልሉም የሚፈፀመው ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃትም ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ።

እነዚህ ኃይሎች በድንገተኛ ሁኔታ ጥቃት እያደረሱ የሚገኙ ሲሆን በከባድ መኪና አሽከርካሪዎችም እንዲሁ ጥቃቱ እየተፈፀመ ይገኛሉ ብለዋል።

ይሄ መስመር አለም አቀፍ መተላለፊያ ድንበር እንደመሆኑ መጠን የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት መጠበቅም ኃላፊነት የፌደራል ፖሊስና መከላከያ ኃይል በመሆኑም እነሱም የሚችሉትን እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።

“የኮንትሮባንድ ንግድ የተቋረጠባቸው ሊኖሩ ይችላሉ እነዚሁ ኃይሎች ናቸው ተደራጅተው የሽብር ጥቃት ፈፅመው የሚመለሱት።” የሚሉት ኃላፊው እንደዚህ ጥቃት የሚፈፅሙ ኃይሎችን የሶማሌ ክልልም ይሁን ሁሉም ሊያወግዝ ይገባል ይላሉ ።

“የኢሳ ማህበረሰብ በተለይም ገዳማይቱ አካባቢ የሚኖሩ ማህበረሰቦችም ከውስጣቸው ወጥቶ ሌሎች ላይ ጉዳት አድርሶ የሚመለሱ ኃይሎችን መታገል አለባቸው። ፀጉረ ልውጦችም ከታዩ ቀድሞ ለፀጥታ ኃይል መረጃ ሊሰጥ ይገባል። ሽፋን ከመሆን ይልቅ መከላከል ይገባል።” ብለዋል

በባለፈው አመትም እንዲሁ ተመሳሳይ ችግር አጋጥሞ ከአገሪቱ ሰላም ሚኒስቴር እንዲሁም ከሶማሌ ክልልም ጋር ችግሩን ለመፍታትና ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙም የተናገሩት ኃላፊው ክልሉም የማጣራት ሰራውን እንደሚቀጥልና የህዝብ ለህዝብ ውይይትም ይቀጥላል ብለዋል።

በተለይም ክልሉ በጎርፍ ክፉኛ ተጠቅቶ ኃብቱና ንብረቱን ባጣበት ወቅት ማጋጠሙም አሳዛኝ እንደሆነ የሚገልፁት ኃላፊው ጥቃቱ የደረሰባቸው አርብቶ አደር ማህበረሰብ እንዲሁ በጎርፉ ኃብትና ንብረቱን የተቀማ ነው ይላሉ።

በክልሉም በሰራ ላይ እያሉ በተተኮሰባቸው በተተኮሰባቸው ጥይት ህይወታቸውን ላጡት ሁለት የትምህርት ሚኒስቴር ሰራተኞች በዛሬው ዕለት ሽኝት መደረጉን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል።

ሰራተኞቹ ወደ አፋር የተንቀሳቀሱት ጥቅምት 13፣ 2013 ዓ.ም ሲሆን በትናንትናው ዕለትም ወደሚሰሩበት ቦታ ገዳሚቱ በምትባል ቦታም ትምህርት ቤቱም ውስጥ ስራ እየሰሩ እያለ ነው ባልታወቁ ሰዎች በጥይት መመታታቸውን የትምህርት ሚኒስቴር ኮሚዩኒኬሸን ጉዳዮች ዳይሬክተር ሐረጓ ማሞ ይናገራሉ።

ሰራተኞቹም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የመማር ከማስተማር ከማስቀጠልም በተጨማሪ በልጅነት እድሜና በሌሎች ምክንያቶች ወደ ኋላ እየቀሩ ያሉ ሴቶችንም አትኩሮት በመስጠት ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግም ነው ወደ ቦታው ያመሩት።

ጂቡቲ መስመር ላይ አንዳንድ አለመረጋጋቶች በሳምንቱ መጀመሪያ ሰኞ እለት፣ ጥቅምት 16፣ 2013 ዓ.ም ተከስቷል የሚሉ መረጃዎች መውጣታቸውን በማስመልከት የትምህርት ሚኒስቴሩ መረጃ አልነበረውም ወይ ተብሎ ዳይሬክተሯ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሰራተኞቹ ከተባለው ቀን በፊት ቀደም ብለው እንደወጡና ከሰኞ በፊት በነበረውም ሁኔታ ሰላም የነበረ መሆኑን ይናገራሉ።

ከሄዱበት እለትም ጀምሮ የተለያዩ አካባቢዎችም ስራ መስራትም ችለው እንደነበርም ተናግረዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሰራተኞቹን በቡድን ወደተለያዩ ቦታዎች የላከ ሲሆን እነዚህ ሰራተኞችም በአጋጣሚ እንደተገደሉም ሐረጓ አስታውቀዋል።

የሰራተኞቹ አስከሬን ከአፋር ክልል በዛሬው ዕለት፣ጥቅምት 18 2013 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባም ገብቷል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች እና ሰራተኞችም ለሰራተኞቹ አስከሬን ወደየአካካቢያቸው ሽኝት ማድረጋቸውንም መረጃው ጠቁሟል።

በወቅቱም ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) የአበባ ጉንጉን ከማኖር በተጨማሪ በሰራተኞቹ እልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ኃዘንም ገልፀው ለወዳጅ፣ ዘመዶቻቸውና ቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ተመኝተዋል።

ሁለቱ ሰራተኞች በተገደሉበት ወቅት የመቁሰል አደጋ ያጋጠመው ሌላኛው የትምህርት ሚኒስቴር ሰራተኛ አቶ ደምሴ ታምሬ የህክምና ክትትል እያደረገ መሆኑንም ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያገኘነውን መረጃ ገልጿል።

Source: BBC Amharic

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *