young lady in oromia
Articles Current

በወለጋ በተከታታይ ለሚካሄደው የአማራ ሕዝብ እልቂት ተጠያቂዎች የኢትዮጵያ ፌደራል መንንግሥት ባለሥልጣናት ናቸው

አክሎግ ቢራራ (ዶር)

“ጣልያንም መጣ፤ ሄደ ተመለሰ፤
እንግሊዝም መጣ ሄደ ተመለሰ፤
ግብፅም ከጀለ ሄደ ተመለሰ፤
ህወሓትም ካደ፤ ሄደ ተመለሰ፤
ማን ቀረ ኢትዮጵያን እያተራመሰ?”

ቅይጥ ጥቅስ

ክፍል አንድ
ስለ ውክልና ጦርነት አደገኛነት በተከታታይ ሳቀርብ የነበረውን ሃተታና የመርህ አቅጣጫ ለጊዜው ወደ ጎን ትቸዋለሁ። የማፈቅራትና የምሳሳላት ትውልድ ሃገሬ ኢትዮጵያ ለአማራው ሕዝብ ሲዖል እና የእልቂት መናኸርያ ሆናለች። እንኳን ኢትዮጵዊ ነኝ ለሚል የሰው ፍጥረት ቀርቶ መላውን ዓለም የሚያሳዝን፤ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን አሳፋሪ እልቂት እየተካሄደ ነው።

ተስፋ ያላት ኢትዮጵያ ሁሉን አሳታፊ፤ በሕግ የበላይነት የሚመካና የሚገዛ፤ ግልጽነት፤ ሃላፊነትና ተጠያቂነት የሚያንጸባርቅ የመንግሥት አመራር የላትም ለማለት የሚያስደፍር ገጽታ ታሳያለች። ያለ ጉቦ፤ ሙስናና አድልዎ የሚሰራ አንድም ነገር የለም ለማለት እደፍራለሁ።
ለመሆኑ መንግሥት አለ ወይንስ የለም? የሚለው ጥያቄ አግባብ አለው። ከዚህ በላይ ግን እኔን የሚያሳስበኝና የሚያሳዝነኝ፤ እኛ ኢትዮጵያዊያን እንዴት እንደዚህ ጨካኝ ሆንን? ይህችን ታሪካዊና ገና ያልተዳሰሰ እምቅ ኃብት ያላትን አገር ወደ የት እየወሰድናት ነው? የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት።

ይህ ሃተታ ስለ ዘውጋዊው የፌደራል ስርዓት ትችትና አማራጭ ለማቅረብ አይደለም (The imperative of reforming ethnic federalism). ሃተታየና ትችቴ የዚህ ዘውጋዊ ስርአት የአገዛዝና የአስተዳደር አሳፋሪነት፤ አጥፊነት፤ ሙሰኛነት፤ አድሏዊነት፤ ጸረሰላምነት፤ ጸረ-አብሮነት፤ ጸረ-ብሄራዊ አንድነት፤ ጸረ-የህግ የበላይነት እና አገር አፍራሽነት ፍጹም አደገኛ ወደ ሆን ደረጃ ተሸጋግሯል የሚል ነው።

በአሁኑ ወቅት፤ ማንም ሊክደው በማይችልበት ደረጃ እጅግ የሚዘገንን ዘውግ ተኮር እልቂት በአማራው ሕዝብ ላይ እየተካሄደ ነው። ከታች እንደሚታየው እናቶች፤ ልጆች፤ ዘመድ አዝማዶች እያለቀሱ ነው። በአጠቃላይ ስገመግመው የዐማራ ሆነ፤ የኦሮሞና ሌላ፤ በአገር ደረጃ ራሱን ኢህአዴግን ተክቻለሁ ብሎ የሚጠራው የብልፅግና ፓርቲ፤ የኦሮምያ ብልፅግና ፓርቲ፤ የዐማራ ብልፅግና ፓርቲና ሌሎች ባለሥልጣናት ይህንን የሚዘገንን የአማራ ሕዝብ እልቂት ሲያወግዙ፤ ገዳዮቹን በማያሻማ ደረጃ ሲያሳድዱና ለፍርድ ሲያቀርቡ አይታይም። ታሪክ ግን ባለሥልጣናቱን እንደሚፋረዳቸው አልጠራጠርም።

አንዳንድ ተቆርቋሪዎች፤ ተመልካቾችና ታዛቢዎች እንደሚሉት ኢትዮጵያ ሕግን የሚያስከብር መንግሥትና ጠንካራ፤ ለህሊናው ተገዢ የሆነ አመራር የላትም። ይህንን አደገኛ፤ ሰለባዊና አገር አፍራሺ ሁኔታ ያባባሰው ደግም የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ መሪዎች ህወሃትና ኦነግ
በጋራ ተመከካረው የመሰረቱትን ዘውግ ተኮር ፌደራሊዝም እንደ መጽሃፍ ቅዱስ ስለሚቀበሉትና አዳዲስ ተጠቃሚዎች ስለተፈጠሩ፤ አንነካውም፤ ትክክል ነው በሚል ብሂል ሊያሻሽሉት ስላልደረፉ ነው።

ዘውግ ተኮሩ የፌደራል ሕገ መንግሥት ስርዓት፤ የአስተዳደር መዋቅር ሰንሰለት እና የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ልሂቃን የበላይነት ይገባኛልነት/ተተኪነት የሚያንጸባርቅ ስርዓት ነው። በአማራ ጥላቻ፤ ጥቃትና እልቂት ላይ ትኩረት ለሚያደርገው ለተተኪነት ፖለቲካ አመች ነው።

የአማራን ጥላቻንና እልቂትን ከመሬትና ሌላ የኢኮኖሚ/ፋይናንስ ባለቤትነት ለይቸ አላየውም። ስርአቱና አስተዳደሩ ለመሬትና ሌላ የኃብት ሽሚያ እና ለሙስና አመቻች ነው። ህወሃት እንዴት ኃብት እንዳካበተና ለሃያ ሰባት ዓመታ እንደ ገዛ ያዩ ኃይሎች የእኛም ተራ ደርሷል (It is our turn to eat, steal and rule) ቢሉ አይፈረድባቸውም። ይህንን ከባድ ሸክም ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊሸከም
አይችልም።

ህወሓት ወልቃይትን፤ ጠገዴን፤ ጠለምትንና ራያን በኃይል ይዞ፤ አማራውን ጨፍጭፎ፤ የሕዝቡን ስርጭት ቀይሮ “ምእራብ ትግራይ” የተባለ የታላቋ ትግራይ አካል የመሰረተው ሕገ መንግሥቱን መሰረት አድርጎ ነው። ይህ የመሬት ነጠቃና የህዝብ ስርጭት ግድፈት ያስከተለውንና ወደፊትም ሊያስከትል ሚችለውን አደጋ በሁለቱ ዓመታት የጦርነት ወቅት አይተነዋል። ከዚህ እልቂትና ውድመት ግን ብዙም የተማርን አይመስለኝም።

በተመሳሳ፤ ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ የአስተዳድሩ አካል እውቅና የሰጣቸው የኢትዮጵያ መለያ ሰንደቅ አላማና የአማርኛ ቋንቋ ተወግደው የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር ሰንደቅ አላማና አፋን ኦሮሞ ይተኩበት የሚለው የጽንፈኞችና ብሄርተኞች እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን ከአንድ አስጊ የእርስ በእርስ ጦርነት ወደ ሌላ የእርስ በእርስ ግጭግት እየገፋት ነው። ይህ ሁኔታ ያሳስበኛል፤ ያስጨንቀኛል።
ለችግርፕቻችን ፈረንጆችን ከመውቀስ ይልቅ መጀመሪያ ቤታችን ብናጸዳ ይሻላል ወደሚል ድምዳሜ አምርቶኛል።

ብሄርተኝነትና ተተኪነት ኢትዮጵያን ያፈርሳታል።
የኦሮሞ ዘውጋዊ ጽንፈኞችና ብሄርተኞች ህወሃትን በመተካት የፖለቲካውንና የማህበረሰባዊ ኢኮኖሚ የበላይነቱን ይዘውም ቢሆን፤ አሁንም ልክ እንደ ህወሃት መሪዎች በጠላትነት የፈረጁትና ኢላማ ያደረጉት የአማራውን ሕዝብ ነው። ለራሱ ነጻነት ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ነጻነት፤ ክብርና ግዛታዊ አንድነት ከፍተኛ አስተዋፆ ያደረገው የአማራ ሕዝብ ከኦሮሞው ወይንም ከትግራዩ ሕዝብ የበለጠ ጥቅም አግኝቶ አያውቅም። እንዲያውም፤ የአማራው ተራ ሕዝብ ኑሮ ሲገመገም፤ በሁሉም የማህበረሰባዊ እድገት መስፈርቶች በድህነትና ኋላ ቀርነት የተበከለ ሕዝብ ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ በኢትዮጵያ በተከታታይ የጥቃትና የጭፍጨፋ ኢላማ የሆነ ሕዝብ አማራው ነው።

ይህ በከፍተኛና በተቀነባበረ ደረጃ የሚታይ ዘረኝነትና ብሄርተኛነት ከቀጠለ ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ በሚያስብል ደረጃ ወደ አደገኛ የእርስ በእርስ ጦርነት እየወሰዳት ነው። ኢትዮጵያን በበላይነት የሚመራው መንግሥት የተወሳሰቡና ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች የሚንጸባርቁባትን ኢትዮጵያን በምን አይነት ራእይ እንደሚመሯት፤ ወደ የት ሊወስዷት እንደሚፈልጉ አላውቅም። ለመሆኑ አንዲት
ኢትዮጵያ የምትባል አገር አለችን? በዚች አገር ማህበረሰባዊ፤ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትሥስር ላይ እንረባረብ የሚለውን እንቀበላለን? ሌላው ቀርቶ አንድ የጋራ ወይንም አገራዊ የመግባቢያ ቋንቋ እንዲኖረን የሚገባ መሆኑን ብንረዳም አሁንም ስምምነት የለም። አማርኛ ይወገድና እንግሊዝኛ የኢትዮጵያ አገራዊ/ብሄራዊ/ኦፊሲያላዊ ቋንቋ ይሁን ቢባል አይገርመኝም።

የተዛባ ፖለቲካ መርህ ውጤቱ የተዛባ ፖሊሲ ነው።
አሁን የምናየው አሳፋሪና አስጊ ሁኔታ ከስድሳዎቹ የወጣቱ ትውልድ የእምቢተኛነት አመታት ጀምሮ (1960s) እስካሁን ድረስ መልስ ያላገኘው ጥያቄ የተዛባ ዘውግ ተኮር አመለካከት የፈጠረውና የሚያሰተጋባ አመለካከት ውጤት ነው። ብሄር፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የልዩነቶቻችን መገለጫ እንዲሆኑ እነ ዋለልኝ መኮነን ከሶቢየቶች የቀዱትን ትርክት ይዘው መሆኑን አሰምርበታለሁ። ዋናው ትርክት አማራውን የጥላቻና የቂም በቀል ኢላማ አድርጎት ስር ሰዷል።

ስም የሚስብ ቢሆንም ቅሉ፤ የብልፅግና አመራር ይህንን አማራ-ጠል ትርክት ትክክል አይደለም ያለበት ጊዜ የለም። ሰው የዘራውን ይሰበስባል እንዲሉ፤ የአማራው እልቂት የተዘራው የጥላቻ ፋሬ ወይንም ዘር ውጤት ነው።

ህወሃት ተወግዷል ቢባልም ቅሉ፤ በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ላይ የተከለው፤ ስር የሰደደው የዐማራ ጠል ተቋማት፤ አስተዳደር፤ ትርክትና ድርጊት ግን ሊፈታ አልቻለም። ለዚህ ነው፤ ተደጋግሞ ቢለፈፍም የሕግ የባለይነት በኢትዮጵያ ሊሰራ ያልቻለው። ሌብነት፤ ጉቦና ሙስና ሊቀረፍ የሚችልበት ሁኔታ አይታይም። አሳ የሚገማው ከአናቱ ነው እንደሚባለው ስርዓቱ በሙስና፤ በአስተዳደር ብልሹነት፤
በህግ-ወጥነት ተበክሏል። የኑሮው ውድነትን ለመቅረፍ አስቸጋሪ የሚሆነውም ለዚህ ነው። ውሳኔው ሁሉ የፖለቲካ ሥልጣን የበላይነት መርህ ሆኖ አጥፊነቱ እየከረረ መሄዱ ሊካድ አይችልም። ብልህነት ያለው አመራር መቸ ይሆን ብቅ የሚለው? ብለን እንጠይቅ።

አገር ውስጥ ሆነ ውጭ የምንኖር ኢትዮጵያዊያን ንፁህ ዜጎች ሲፈፈጨፉና ከቀያቸው ሲባረሩ በተከታታይ ስላየን፤ እኛ ደንዝዘናል ብል አልሳሳትም። ይህ ሁኔታ የተለመደ መሆኑ ለአማራው ሕዝብ እልቂት ድምጽና አቤቱታ ላለማሰማት ግብአት እየሆነ ነው። ይህች ከታች የምትታየው ወጣት አማራ ምን ወንጀል ሰራች ብለን ራሳችንን እንጠይቅ፤ ህሊናችንን እንቀስቅስ፤ በጋራ ሆነን የዐማራ ሕዝብ እልቂት ይቁም ለማለት እንድፈር። በኔ ግምገማና እምነት የዐማራው ሮሮና ለቅሶ የኢትዮጵያም ጭምር መሆኑን አሰምርበታለሁ።

በአዲስ አበባ የሚካሄደውን የብሄር ጽንፈኞችና ተረኞች ደባና ሴራ ስመራመር፤ በዚች አምስት ሚሊየን ሕዝብ በሚኖርባት ታላቅ ከተማ ያንዣበበው የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲከሰት የሚደረግ እንቅስቃሴ ለማንም አያዋጣም።

ኢትዮጵያን ከድጡ ወደ ማጡ በመሸጋገር ላይ ናት። የኦሮሞ ልሂቃን እና የፖለቲካ መሪዎች “እኔም ኦነግ ሸኔ ነኝ” ብለው ሲናገሩ ስሰማ፤ ትዝ ያለኝ፤ የትግራይ ስደተኞችም (ዲያስፖራ) “እኛማ ህወሓት ነን” ያሉትን ነው። በኦነግ ሽኔና በህወሃት መካከል ምንም ልዩነት የለም ማለት ነው። ሁለቱም ሽብርተኞች፤ ጸረ-እትዪጵያና ጸረ ሰላም ኃይሎች ናቸው።

የብልፅግና አመራር ይህንን የአንድ ሳንቲም ግልባጭ ሴራ ግን በሚገባ አላስተዋሉትም፤ ወይንም፤ ጸረ-ዐማራ ስለሆነ ራሳቸው ችላ ብለውታል፤ አንዳንዶች እንደሚኩት ደግሞ አመቻችተውታል።

young lady in oromia
ለማንኛውም፤ በአማራ ስም ሆነ በኦሮሞ፤ በቤኒ-ሻንጉል ጉሙዝ ስም ሆነ በሶማሌ፤ በትግራይ ሆነ ሌላ ለእልቂቱና ላንዣበበው አደጋ ተጠያቂዎቹ በአሁኑ ወቅት በሥልጣን ላይ ያሉት የብልፅግና ፓርቲ ባለሥልጣናት እና የመከላከያ ኃይል ሃላፊዎች ናቸው።

ኢትዮጵያን የሚያዋጣት ሕገ መንግሥት የዘውግ ፌደራሊዝም አለመሆኑን በተደጋጋሚ አሳስቤ ነበር። በተለይ ባለፉት ሁለት የጦርነት ዓመታት። በዘላቂነት ስመለከተው የሚያዋጣት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በዜግነቱ መሰፈርት ዲሞክራሳዊና ሰብአዊ መብቱ/መብቷ የሚከበርበት ስርዓት ሲመሰረትና በሕግ ሲከበር ብቻ ነው።

የአማራ፤ የትግራይ፤ የአፋር፤ የሶማሌ፤ የአኟክ፤ የኦሮሞ ወዘተ እናቶችና ልጆች ተከታታይ ለቅሶና ምሬት ሊቀሰቅሰን ካልቻለ ምን ሊያንነሳሳን ይችላል? በክልል ሆነ በፌደራል ደረጃ የኢትዮጵያ ባልሥልጣናት ለኦነግ የነጻነት ተዋጊ ኃይል (OLA) ሰለባ ለሆኑት የዐማራ ወገኖቻች እንባና ጩኸት ካልደረሱላቸውና አስችኳይ መፍትሄ ካልተገኘ እንዴት ሆኖ ነው ዘላቂ ሰላም፤ እርጋታ፤ ፍትሃዊ ልማት፤
ብልፅግና ስኬታማ ሊሆን የሚችለው?

እኔ ሳስበው ልቀበለው ባልችልም እንኳን፤ የዐማራው ሕዝብ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ምድር እንዲጠፋ ይፈለጋል የሚሉ ታዛቢዎች ብዙ ናቸው። ይህ የፈጠራ አስተያየት አይደለም። እኔ እስከማውቀው ድረስ፤ የአማራው ህዝብ ባለፉት አምሳ ዓመታት የጥላቻ ትርክት
ባስከተለው ግፍ፤ በደልና እልቂት ተካሂዶበታል፤ አሁንም በባሰ ደረጃ እየተካሄደበት ነው። አዲሱ የኢትዮጵያ ህዝብ ወጣት ትውልድ በድንቁርና እንዲበከል ተደርጓል። ከዚህ ድንቁርና መካከል እርስ በእርሱ ሊገናኝበት የሚጠቅምና አግባብ ያለው የጋራ ወይንም አገራዊ ቋንቋ እንዳይኖረው መደረጉ አንዱ ምክንያት ነው።

የተለያዩ የክልል መንግሥታት መስርቶና አዳዲስ ተጠቃሚዎች ፈጥሮ አንድ አገርና አንድ ኢትዮጵያዊ የሚባል መለያ የተቀብለ ህዝብ አለ ለማለት አንችልም። ኢትዮጵያን የጋራ አገራችን ናት የሚል እምነት ያለው የአማራ ሕዝብ “መጤ ነህ፤ ወራሪ ነህ፤ ጨቋኝ ነህ፤ ተስፋፊ ነህ” ወዘተ እየተባለ ይጨፈጨፋል፤ ይሳደዳል፤ ይዋረዳል።

ለዚህ በነጻነቱ የሚኮራና አገሩን የሚያፈቅር ሕዝብ ሊደርስለት የቻለ ወይንም የሚደፍር ባለሥልጣናት ፈልጌ ለማግኘት አልቻልኩም። አማራው ድልድይና በነጻነቱ የሚኮራ ሕዝብ መሆኑን ከተማሪው እንቅስቃሴ ጀምሬ ስደግፍ ቆይቻለሁ። ግን ብዙም ስኬት አላየሁም።

የወደፊቱን ሁኔታ ለማሰብ የምቸገረው ኢትዮጵያ ያለ ዐማራው ሕዝብ፤ የዐማራው ሕዝብ ያለ ኢትዮጵያ ፋይዳ ቢስ ስለሆኑ ነው። በመርህ ደረጃ ስመለከተው የዐማራው፤ የጉራጌው፤ የሶማሌው፤ የአፋሩና ሌላው ኢትዮጵያዊ ሕዝብና ዜጋ በማንኛውም የኢትዮጵያ አካል በሆነ ምድር ያለ ምንም ስጋትና ፍርሃት ለመኖር ካልቻለ ለምንና ለማን ዓላማ ነው ጥምር ኃይሉ ለሁለት ዓመታት ደሙን
አፍስሶ፤ አጥንቱን ከስክሶ ህወሓትን፤ የውጭና የውስጥ አጋሮቹን የተዋጋቸው? የፕሪቶሪያውና የናይሮቢው ድርድርና ስምምነት ትርጉምና ፋይዳስ ምን ሊሆን ይችላል?

እነዚህን ጥያቆዎች መመለስ ያለባቸው አገሪቱን በበላይነት የሚመሩት ባለሥልጣናት መሆናቸው አያጠራጥርም። ጭና ማድረግ ያለብን ባለሥልጣናቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መልስ እንዲሰጡ ነው።

ኢትዮጵያ ህወሓትን አስወግዳ በሌላ ህወሓት ልትፈራርስ መፍቀድ ለኢትዮጵያም ሆነ ለማንም ባለሥልጣን ሊያዋጣ አይችልም። ምክንያቱም፤ ይህች አገር ልትፈራርስ ትችላለች።

በኦሮምያ/ወለጋ፤ በደራ፤ በአዲስ አበባ ዙሪያ ወዘተ የሚካሄደው አረመናዊ ዐማራ ተኮር ጭካኔ ከህወሕት ጭካኔ፤ ግፍና በደል አቻ ወይንም የባሰ መሆኑ በተደጋጋሚ ይታያል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በጋራ ሆኖ ህወሓትን በጥምር ኃይሉ ጀብድ ለማንበርከክ ተችሏል። ኦነግን ሸኔን በሚመለከት ግን፤ በኦሮምያ መንግሥትና በፌደራሉ መንግሥት ተቋማት ውስጥ ተሰስገው የሚገኙትን ግብረ አበሮቹን
ማንም ደፍሮ ሊነሳባቸው አልቻለም።

የፌደራሉ መንግሥት ሚና ምንድን ነው?
ልክ እንደ ሌሎች መንግሥታት የፌደራሉ መንግሥት መሰረታዊ ሚና የንጹህ ዜጎችን ደህንነት መንከባከብና ማስከበር ነው። የዐማራው ህዝብ ግን የዚህ መርህ ተጠቃሚ አለመሆኑ በተደጋጋሚ ታይቷል። ጥያቄው ለምን? የሚለው ነው።

የውስጥ ተመልካቾችና ታዛቢዎች እንደሚሉት ከሆነና እኔም እንደ ታዘብኩት፤ በተራው የአማራና የኦሮሞ፤ በተራው የአማራና የትግራይ፤ በተራው የአፋሩና የትግራይ ወዘተ ህዝብ መካከከል ጥላቻና ግጭት የለም። ግጭቱን ለፖለቲካ ትርፍ የሚጠቀሙበትና በሳቱ ላይ ቤንዚን የሚረጩት የጠባብ ብሄርተኛና ጽንፈኛ የፖለቲካና የማህበረሰባዊ ኢኮኖሚ ልሂቃን (Elites) ናቸው።

በወለጋ የሚካሄደውን የሚዘገንን የዐማራ-ተኮር እልቂት በአዲስ አበባ ከተማ “የኦሮሞ ሰንደቅ አላማና የኦሮሞ ቋንቋ የሕግ እውቅና የተሰጣቸውን ይተኩ” ከሚለው የጦፈ ትግልና እምቢተኛነትና አመፅ ለይቸ ለማየት እቸገራለሁ። ህገ ወጥነት ነግሷል የምለው ለዚህ ነው።

የአሁኑ ሕግ መንግሥት አንቀጽ 5 ቁጥር 2 “የፌደራሉ መንግሥት የስራ ቋንቋ አማርኛ ነው” ይላል። የአዲስ አበባም ከተማ የስራ ቋንቋ አማርኛ መሆኑን ያንጸባርቃል። ስለሆነም፤ በቋንቋ ምክንያት ግጭቱን ከጀርባ ሆኖ የሚያስተጋባው ማነውና ለምን? ብለን መጠየቅ አግባብ አለው። በተመሳሳይ፤ ሕግ የሚከበር ከሆነ በሰንደቅ አላማውም ላይ ተመሳሳይ ግንዛቤ መያዝ አግባብ አለው። ይለወጥም
ከተባለ በውይይትና በህግ እንጅ በኃይል ወይንም በጉልበት ሊሆን አይችልም። ህወሓት በወልቃይት ላይ ያደረገውን ህገወጥ ድርጊት በአዲስ አበባ እንዲደገም መፍቀድ የኢትዮጵያ ዘላቂነት ሊያናጋው ይችላል።

ኢትዮጵያ ወያኔን በሕዝባዊ አመጽና በቅርቡ ደግሞ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት አማካይነት ጦሩነቱ እንዲዲቆም፤ እርቅና ሰላም እንዲሰፍን፤ ሰብአዊ አገልግሎት በጦርነት ለተጎዱት በአፋር፤ በዐማራና በትግራይ ክልሎች ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እንዲደርስ ሲነገር የተሰማኝ ደስታና ተስፋ ከፍ ያለ ነበር።

እርቅና ሰላም አገር አቀፍ መሆን አለበት።
የትግራይ ተራ ሕዝብ አባላት እፎይ ሲሉና ሰብአዊ አገልግሎት ፈሰስ ሲጀመር፤ ለምን በዐማራው ሕዝብ ለይ የተቀነባበረ የዘውግ ማጥፋት (Amhara genocide) ዘመቻ ተባባሰ? ማን አባባሰው? ማን በሃላፊነት ይጠየቅ? ለያንዳንዱ ለህሊናው ለሚገዛ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለማቅረብ የምፈልገው ጥያቄ በንጹህ ዐማራዎች ላይ ያለ ገደብ የሚፈጸመው አሳፋሪና ዘግናኝ ጭፍጨፋ ከቀጠለ ለኢትዮጵያ ምን
አደጋ ሊያስከትል ይችላል? የሚለውን ነው።

1. መጀመሪያ አማራው በአንድ ድምጽ ለጋራ የህልውና መስተጋብር ለመስራት ይሞክር። የአማራው ሕዝብ በጎጥ፤ በመንደር፤ በክልልና በጥቅም ሳያከፋፈል ራሱን ከእልቂት አደጋ ለመከላከል ከብረት የጠነከረ የዓላማ አንድነት እንዲኖረውና ድርጅቲዊ አቅሙን በስልት እንዲያዋቅር እመክራለሁ

በተመሳሳይ፤ በውጭ የሚኖረው የተበታተነውና በግሉ ብቻ የሚፍጨረጨረው የአማራ ህብረተሰብ በአንድ ድምጽ፤ ለአንድ አላማ እንዲተባበር አደራ እላለሁ።

የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት አማራው ራሱን ከእልቂት ለማዳን የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በልዩ ልዩ ሰበብ–ፋኖ፤ ነፍጠኛ–በሚል ትችትና መሰናክል መፍጠር የለበትም። በወለጋና በሌሎች የጥቃት አካባቢዎች ለሚኖረው የአማራው ህዝብ የፌደራሉ መከላከያ ኃይል በአስቸኳይና አስተማማኝ በሆነ ደረጃ ድጋፍ ቢሰጠው ይመረጣል። ይህ ካልሆነ ግን፤ ሁለተኛው አማራጭ የአማራዊ ነዋሪ ህዝብ ራሱን ከጥቃት እንዲከላከል የፊደራሉ መንግሥት ባለሥልጣናትና ተቋማት የቁሳቁስ ድጋፍ የመስጠት ግዴታቸውን እንዲወጡ አሳስባለሁ።

ሶስተኛው አማራጭ የተባበሩት መንግሥታት ወይንም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የሰላም አገልግሎት ኃይል (UN or AU Peacekeeping contingent) ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ሰላም አስክባሪ ይሁን የሚለውን አማራጭ በበኩሌ አልቀበለውም። ይህ አማራጭ ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ፈርሳለች፤ መንግሥትም የለም ወደሚል ድምዳሜ እንደሚወስድ እሰጋለሁ። ይህ እንዳይሆን ስለምመኝ
የፌደራሉ መንግሥት አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ አለበት እላለሁ።

2. በወለጋ፤ በደራ፤ በአዲስ አበባ ዙሪያ የተከሰቱት እልቂቶች፤ አፈናዎች ወዘተ የተለየ የመንግሥት ትኩረት ካልተሰጣቸው፤ የእርስ በእርስ ጦርነት የሚከሰትበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል የሚለውን አመለካከት እኔም አስተናግዳለሁ።

ኢትዮጵያ የብዙ ሽህ ዓመታት ታሪክ ያላት አገር መሆኗ አያጠራጥርም። የአማርኛ ቋንቋ ብቻ አንድ ሽህ አመት ታሪክ አለው። ቋንቋውን ኦፊሻላዊ ያደረጉት ደግሞ አጼ ዮሃነስ ናቸው። መሆኑም አግባብ አለው። ይህ ቋንቋ የልዩ ልዩ ሃሳቦችና ቋንቋዎች ቅይጥ እንጅ የአማራ ብሄር ቋንቋ ውጤት አለመሆኑን ምሁራን ይናገራሉ።

በተመሳሳይ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ አንዱ ከሌላው የተዋለደና የተዛመደ ሕዝብ ነው። የሚያሳፍረው ግን፤ በህያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝብ ልክ እንደ ባእዳን የሚጋራው እሴት ተሽርሽሯል። ኢትዮጵያ የምትባል አገርንና ኢትዮጵያዊ የዜግነት
መለያን የተቀበለው ማነው ብለን እራሳችንን እንጠይቅ?

በኔ እምነት የኢትዮጵያ ህዝብ አብሮና ተቻችሎ ከመኖር ውጭ ሌላ አማራጭ የለውውም። ተተኪነትን የምተቸው ለዚህ ነው።

3. ህወሃት በመወገድ ሂደት ላይ ቢሆንም እንኳን በምትኩ ኦነጋዊያን በአንድ ድምጽ በሚባል ደረጃ በአዲስ አበባ፤ በሰሜን ሸዋና በወለጋ የሚያካሂዱት አደገኛ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን እያናጋት ነው። ይህ ሁኔታ ኢላማ ያደረገው አማራውን ነው።

በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ህዝብ ለአደጋ እንዲጋለጡ ያደረገው ማነው? የሚለው ጥያቄ በማያሻማ ደረጃ መልስ ነበረው። ይህም አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተጋራው መልስ ህወሃትና ግብረ አበሮቹ ናቸው የሚል ነው። በተነፃፃሪነት ሲገመገም ግን በወለጋ፤ በሰሜን ሸውና በአዲስ አበባ የሚካሄደውን አማራ ተኮር ግፍና በደል ስንመራመር የማያሻማ መልስ ለመስጠት እንቆጠባለን። ለምን ይሆን? ወደ የት እየተጓዝን ይሆን?
በኔ ግምገማና እምነት ግን፤ ወንጀሉን ማንም ኃይል ይፈጽመው ለአማራው ሕዝብ እልቂትና ለቅሶ ተጠያቆዎቹ የሚከተሉት ናቸው፤
1. የፌደራሉ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፤ የኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይልና ፌደራል ፖሊስ፤
2. የኦሮምያ መንግሥት ባለሥልጣናትና የኦሮሞ ልዩ ኃይልና ፖሊስ፤
3. የአማራውን ህዝብ እወክላለሁ ብሎ የሚናገረው የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር።
ባጭሩ፤ ባልታጠቀውና በማንም ህዝብ ላይ ጥፋትና ጥቃት ባላካሄደው የአማራ ሕዝብ ላይ በተካሄደውና አሁንም በሚካሄደው እልቂት ላይ የማሻማና ቆራጥ እርምጃ መውሰድ የነበረባቸው ከላይ በአንድና በሁለት ያስቀመጥኳቸው ባለሥልጣናት ናቸው።

በተዛማጅ ደግሞ በማያሻማ አንደበትና ደፋርነት ይህ የአማራ እልቂት ያስጥይቃል፤ መፍትሄ ካላገኘ ወደ የእርስ በእርስ ጦርነት ያመራል ብለው ድምጽና አቤቱታ ሳይሰለቹ ማሰማት ያለባቸው ደግሞ የአማራ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት ናቸው።

ስለሆነም፤ ሶስቱም በስልጣን ላይ የሚገኙ አካላት ከተጠያቂነትና ከሃላፊነት ሊሸሹ አይችሉም።
በመጨረሻ፤ በውጭ የሚኖረው ግዙፍ የአማራ ሕዝብ ለአማራው ብሶትና እልቂት በአንድነት ሆኖ ሊሰራ አለመቻሉ የአደባባይ ምስጢር ነው።

•   ድርጂት ከመፈልፈል ውጭ የአማራው ምሁር፤ ልሂቃን፤ ጋዜጠኛ፤ አስተማሪ፤ የግል ባለ ኃብትና ሌላ ባለሞያ በአንድ ላይ ሆኖ፤ በዝግ ችሎት ሆነ ሌላ እኛ የምናየው ክፍተት ምንድን ነው? ከህወሓት ሆነ ከኦነግ ምን ለመማር እንችላለን? ብሎ መፍትሄ የሚፈልግበት ወቅት ዛሬ ነው።

•   በግል ደረጃ ሲታይ፤ አማራው ስኬታማ ነው ለማለት ይቻላል። በጋራ ሆኖ ለጋራ ዓላማ ግን ለመቆም አልቻለም። ይህ ሁኔታ በአስቸኳይ መለወጥ አለበት።

•   የአስተሳሰብ ለውጥ ካላደረግንና በጋራ ለመስራት ካልቻልን ለአማራው ጠበቃ ለመሆን አንችልም።

December 12, 2022

 

 

 

መንግሥት የችግሩ ወይስ የመፍትሄው አካል?

Source: Zehabesha.com

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *