እስኪ ተጠየቁ! – መስከረም አበራ፣ ከቃሊቲ ማጎሪያ ቤት
በአለም ላይ ያሉ መልካም ነገሮች ሁሉ የትግል ውጤቶች ናቸው፦ እኩልነት፣ ነጻነት፣ ሰብዓዊ ክብር፣ ከቅኝ-ግዛት ሰንሰለት መፈታት፣ ከዘር መድሎ መዋጀት፣ በወደዱት/በፈቀዱት መተዳደር ሁሉ የትግል ትሩፋቶች ናቸው። የአማራ ህዝብ ዛሬ እያደረገ ያለው የትግል ትሩፋት የሆኑ መልካም ነገሮች ሁሉ ለማግኘት የሚያስፈልገውን መራር ትግል ነው። በመራራው የጥላቻ ፖለቲካ ለበቆች ሁሉ ሲገረፍ ማንም ችግሩን ያልተረዳለት የአማራ ህዝብ በስተመጨረሻው የራሱን ትግል ለመታገል ቆርጦ ተነስቷል። ይህ ቻይ ህዝብ እዚህ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት የፍጡር በማይመስል ትዕግስት ታግሷል፣ የማይቻለውን ችሏል፣ የማይታለፈውን አልፏል፣ ለማይሰሙ ጆሮዎች በደሉን “አቤት” ብሏል። ሰሚ ግን አልነበረም።
አሁን ትግሉ ሲፋፋም ደግሞ መካሪ ዘካሪው በዝቷል፣ አድፋጩ ሁሉ የሰላም ሰባኪ ሆኗል። የአማራ ህዝብ በደሉን አበክሮ ሲነግረውና መፍትሄ እንዲያመጣለት ሲማጸነው የነበረው የብልጽግናውን መንግስት ነበር። ይህ መንግስት የአማራ ህዝብ በሲቃ እያማጠ ፍትህ ይወርድለት ዘንድ ሲማጸነው ሰምቶ ሊመልስ ቀርቶ “ምን ሆንክ እና ምን ላድርግልህ?” የሚል በአማራ ህዝብ ለቅሶ ላይ የሰርግ ድንኳን ለመጣል የሚቃጣው መልስ ሲሰጥ ኖሯል።
አሁን የተፌዘበት ህዝብ ቆርጦ ሲነሳ ደግሞ ይሄው መንግስት በተለመደ ማደናቆሩ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ ስለመሆኑ እያወራ ነው። በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተመርጦ ከሆነም ምርጫ አንድ መንግስት ወደ ስልጣን የሚመጣበትን መንገድ ያሳያል እንጅ ከተመረጠ በኋላ ህዝብ አምኖበት የሰጠውን ስልጣን መንግስት ተብየው እንዴት እየተጠቀመበት እንደሆነ አላሳየም። የብልጽግና መንግስት ደግሞ ተመረጥኩ ካለ በኋላ ስልጣኑን እንዴት እየተጠቀመበት እንደሆነ ሁሉም የሚያውቀው ነዉ።
በሀገራችን በሁሉም ክልሎች ተመረጥን ብለው ስልጣን ላይ የተቀመጡ የየክልሉ የብልጽግና መኳንንት አዲስ አበባ እንደተቀመጠው የመንግስታቸው ራስ ሁሉ በአማራ ህዝብ መከራና ሲቃ ላይ ሲያላግጡ ነበር። አሁን ህዝቡ በመሰለው መንገድ ከሲቃ የሚያወጣውን መንገድ ሲጀምር ካደፈጡበት ከሸፍጥ ዋሻ ብቅ ብቅ እያሉ ማሳሰቢያ አይሉት የማንገራገሪያ መግለጫ እያዥጎደጎዱ ነው። እንደ ጉንዳን መንገደኛ በአንድ አቅጣጫ ከመፈሰስ በስተቀር ግራ ቀኙን የማያዩ የብልጽግና ፓርቲ የክልል ጭፍራዎች የአማራ ህዝብ በኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች እንደቆሻሻ በጅምላ ሲቀበር፣ ለገዳዮቹ የዝምታ ፍቃድ ሲሰጡ ነበር።
የኦሮሚያ ክልልን የሚመራው ሰውዬ እንደውም “ስንገላቸው ያልቅሱ የምንሰጣቸው ነገር ቢኖር እንባቸውን ማበሻ ሶፍት ነው” ሲል በግልጽ ተናግሯል። አሁን በንዴት ጥርሱን እያፏጨ ያወጣው መግለጫ ደግሞ የቀደመ ፌዙን አይመስልም። ይህ የሚጠበቅ ነው- ህዝብም ሲያለቅስ አይኖርም፤ ህዝብ ለትግል መነሳቱ ተፈጥሯዊ ነው። የአማራ ህዝብ እያደረገ ያለውም ይህንኑ ተፈጥሯዊ ነገር ነው። ይህን ተፈጥሯዊ ነገር በመከተር የአማራን ህዝብ የበደል ዕድገት ያሳልጥ ዘንድ ትውልደ አማራነቱን ተጠቅሞ ስልጣን ላይ ተወዝቶ የነበረው የአማራ ብልጽግናም ወጉ እንዳይቀርበት ስለሰላም አስፈላጊነት ለአማራ ህዝብ እየሰበከ ነው። ለዚህ ስብስብ ሰላም ማለት ለገዳይ ካባ ማልበስ ነውና እንዲህ ባለ ራስን መናቅ አዘቅት ውስጥ ለተዘፈቀ ቡድን ቃላትን ማባከን የማይገባውን ክብር መስጠት ነው። በአጠቃላይ የብልጽግናው መንግስት የአማራ ህዝብ ለሶስት አመታት የደረሰበትን ዘር ተኮር ጭፍጨፋ በዝምታ ሲያሳልጥ፣ ወይም በቀጥታ ሲደግፍ የኖረ በመሆኑ የዘር ማጥፋት ወንጀለኛ መሆኑን ታሪክ በማይለቅ ቀለሙ የጻፈው ሀቅ እንደሆነ ሊያውቅ ይገባዋል። በታሪክ ገጽ በደም የተጻፈውን ይህን የብልጽግናውን መንግስት ወንጀል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የከባድ መሳሪያ ተኩስ መፋቅ አይቻልም።
የብልጽግናውን መንግስት የዘር ማጥፋት ወንጀል አብረው ሲያሳልጡ የነበሩት ‘ኢዜማ’ የተባለው ፓርቲ መኳንንትም የአማራ ህዝብ በየደቂቃው በጥይት አርር ሲያልቅ “በአማራ ህዝብ ላይ የደረሰ በደል የለም” ሲሉ ኖረዋል። ዛሬ ስልጣን ላይ ያሰፈራቸውን ወንጀለኛ መንግስት በአማራ ህዝብ ቁጣ መድረሻው ሲጠፋው በአንድ ሳምንት ሁለት መግለጫ አውጥተዋል። ሶስት አመታት ሙሉ በአማራ ህዝብ ላይ በደረሰው ወንጀል ሲያፌዝ የነበረው ይህ ፓርቲ በተለመደው ሀፍረተ-ቢስነቱ ዛሬ ላይ የአማራ ህዝብ የተለየ ማንነት ተኮር በደል በመድረሱ ይህ ህዝቡ ተማሮ ጠመንጃ እንዳነሳ መተንተን ጀምረዋል። ይህ አባባል ሶስት አመታት ሙሉ “አማራው በተለየ መንገድ አልተበደለም” ሲሉ ከኖሩት ቅጥፈት ጋር የሚጋጭ ብቻ ሳይሆን እነሱንም ከአሳዳሪያቸው የብልጽግና መንግስት የዘር ማጥፋት ወንጀለኝነት ተርታ የሚያሰልፍ የራስ ምስክርነት ነው።
በጣም የሚገርመው ደግሞ ይህ ፓርቲ በመግለጫው መንግስት የአማራን ህዝብ ጥያቄ ባለመመለሱ እየከሰሰ የዚሁ ፓርቲ መሪ የመንግስት ሚንስትሮች ምክር-ቤት አባል ሆኖ፣ የአማራ ህዝብ በከባድ መሳሪያ የሚያልቅበትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን አውጆ ደም መፍሰሱን እያሳለጠ መገኘቱ ነው። ማምታት ጊዜው አልፏል፣ ገዳይም አዳኝም፣ ወዳጅም ጠላትም መሆን አይቻልም! የህዝብ ልቦና ሁሉን ያውቃል፣ ታሪክ ሁሉንም ይመዘግባል። የታሪክ ፍርድ በሁሉም ሰው ፊት ነው። ሁሉም እንደየስራው በታሪክ ፊት ይቆማል።
በዚህ ሁሉ ውስጥ ጊዜው የደረሰው የአማራ እውነት ድል እንደሚያደርግ ቅንጣት ጥርጣሬ የለኝም። ከልጆቼ ተለይቼ በተከረቸምኩበት እስር-ቤት የምጽናናበት ትልቁ ጉልበቴ ይህ ነው። በጥላቻ ተደፍኖ፣ በጠመንጃ ታፍኖ የኖረው የአማራ ህዝብ እውነት፣ ጊዜው ደርሶ ከተቀበረበት ወጥቶ በድል ጎዳና ላይ እየተራመደ ነው። ከዚህ በላይ የሚያስደስተኝ ነገር የለም። በተረፈ የአማራን ህዝብ እውነት በጭካኔ ሲያዳፍን የኖረው ሁሉ ዛሬ ለአማራ ህዝብ ስለሀገር ጠቀሜታ፣ ስለሰላም አስፈላጊነት ሊሰብክ ሲመጣ ሳልወድ ሳቅ ይሞክረኛል። እነዚህ የአዞ እንባ አንቢዎች ለአማራ ህዝብ ስለሀገር አስፈላጊነት፣ ስለሰላም በጎነት ሲመክሩ ‘ቄሰ ገበዝን የሚገዝት የቆሎ ተማሪ’ ይመስሉኛል።
ዛሬ የአማራ ህዝብ ወደ ነጻነቱ፣ ወደ ሰብዓዊ ክብሩ የሚያደርሰውን የትግል መንገድ በቆራጥነት ሲይዝ ፍርሀት የሚያስለፈልፈው ሁሉ ለአማራ ህዝብ አስቦ እንዳልሆነ የሚታወቅ ነው። ለአማራ ህዝብ ያሰበ፣ ይህ ህዝብ በሞት ጥላ ስር በሄደባቸው በነዛ ክፉ ቀናት ከጎኑ ይቆም ነበር። ይህን ከፍታ የረገጠ ብቻ ስለ አማራ ህዝብ ትግል አስተያየት መስጠት ይችላል። በተረፈ በንጉስ ትዕዛዝ በየሚዲያው እየወጣ የሚለፈልፈው ሁሉ የአማራ ጠሉ ስርዓት የዘር ማጥፋት ወንጀል አስቀጣይ እንጅ ሌላ አይደለም። የአማራ ህዝብ ትግል አስበርግጓዋቸው ከሰሞኑ በየሚዲያው የአማራን ህዝብ ልምከር የሚሉ ህልቆ መሳፍርት ሀሰተኛ የሰላም ሰባኪያንን ሳይ እና ስሰማ እንደ አማራ ህዝብ በሞት ጥላ ስር የኖሩ እስራኤላዊያን የአለምን ህዝብ በትዝብት የሚሞግቱበት አባባል ትዝ ይለኛል። አባባሉም ይህ ነው፦ “በክፉ ቀናችን ከሚፈጁን፣ ከሚያቃጥሉን ወገን ካልነበራችሁ ገዳዮቻችንን ስታግዙ ወይም የራሳቸው ጉዳይ ብላችሁ በመከራችን ላይ ፊታችሁን አዙራችሁ ነበር።”
ዛሬ የአማራን ህዝብ ስለ ሰላም አስፈላጊነት፣ ስለ ሀገር ጥቅም፣ ወቅቱ መኸር በመሆኑ አርሶ መብላት እንዳለበት ልትመክሩ በየሚዲያው የምትሰየሙ፣ ‘የሰላም ሰዎች’ የአማራ ህዝብ ይህንን የእስራኤላዊያንን አባባል ወደ እናንንተ ቢያቀርበው መልስ ይኖራችሁ ይሆን? እስኪ ተጠየቁ!
Source : Abebe Gellaw facebook account