News

በከባድ ፈተና ውስጥ እያለፈች ትገኛለች፡ አቡነ ማቲያስ

አቡነ ማቲያስ

የፎቶው ባለመብት,EOTC TV

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በከባድ ፈተና ውስጥ እያለፈች እንደምትገኝ ፓትሪያርኳ አቡነ ማቲያስ ዛሬ በተጀመረው ቅዱስ ሲኖዶስ መክፈቻ ላይ ተናገሩ።

ቅዱስ ፓትሪያርኩ የቤተክርስቲያኗ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ቤተክርስቲያኗ በአሁኑ ጊዜ ከውጭ እና ከውስጥ በከባድ ፈተና ውስጥ እያለፈች መሆኗን ገልጸዋል።

“የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ በከባድ ፈተና ውስጥ እያለፈች ትገኛለች፤ የውጭው ፈተና ባይቀርላትም ከእሱ በላይ ግን በውስጧ የሚነሡ ፈተናዎች ተልዕኮዋን በአግባቡ እንዳትወጣ ዕንቅፋት ሆነውባታል” ብለዋል።

አቡነ ማቲያስ አክለውም በቤተክርስቲያኗ ውስጥ የሹመት ፈላጊነት እና የገንዘብ ፍቅር መንገሱን፣ መለያየት እና መነቃቀፍ እየሰፉ መምጣቱን በማንሳት ኃላፊነት የጎደላቸው ንግግሮች “በበጎቻችን ዘንድ የነበረንን ተሰሚነት እና ተደማጭነት ሊቀንሱብን እየተንደረደሩ ነው” በማለት ገልጸዋል።

ራስን በራስ የመሾም ልምምድ በቤተክርስቲያኗ መታየቱን ያነሱት ፓትሪያርኩ የዚህ “ፈተና መንስኤ ውጫዊ ሳንካ ባይጠፋበትም የውስጣችን ሰዎች ለእሱ ምቹ ሆነው መገኘታቸው አልቀረም” በማለት በዚህ ሳቢያ ቤተ ክርስቲያኗ ከባድ ጉዳት እየደረሰባት ከመሆኑ ባሻገር ሰላሟ እና አንድነቷ ጥያቄ ላይ ወድቋል ብለዋል።

ከአንድ ዓመት በፊት የተወሰኑ የቤተክርስቲያኗ አባቶች ከአዲስ አበባ ውጪ ከሲኖዶሱ ዕውቅና ውጪ የጳጳሳት ሹመት መስጠታቸውን ተከትሎ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ለከባድ ቀውስ ተከስቶ እንደነበር ይታወሳል። በዚህም ሳቢያ መንግሥት በጉዳዩ ውስጥ ጣልቃ ገብቶ መግባባት እንዲፈጠር አድርጓል።

ነገር ግን ቅዱስ ፓትሪያርኩ በሲኖዶሱ ጉባኤ መጀመሪያ ላይ ባደረጉት አሁንም ቤተክርስቲያኗ ውስጣዊ እና ውጫዊ ፈተናዎች እየተጋፈጠች መሆኑን ተናግረዋል።

ፓትሪያርኩ በመልዕካታቸው ባለፉት ዓመታት አስከፊ በደል መፈጸሙን እና አሁንም እንዳልቆመ ጠቅሰው፤ ይህ በደል “ዛሬም አለ፤ ነገም የተለየ ነገር ይኖራል ተብሎ አይታሰብም” በማለት ጉባኤው ለዕርቅ እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል።

“በደልን በካሣ እና በዕርቅ፣ በይቅርታ እና በምሕረት መዝጋት፣ ተመሳሳይ በደል እንዳይፈጸም አስተማማኝ የሆነ ተቋማዊ ሥርዓትን ማበጀት መልካም ይሆናል፤ . . . ስለዚህ ይህ ቅዱስ ጉባኤ በዚህ ዙሪያ በስፋት እና በጥልቀት በመወያየት ሁሉንም ሊያስማማ በሚችል መልኩ ወደ ሰላም እና ዕርቅ የሚያደርስ ሥራ መሥራት ይኖርበታል” ብለዋል።

አቡነ ማቲያስ በተጨማሪም ችግር የገጠማት በቤተ ክርስቲያኗ ብቻ አለመሆኗን አንስተው፤ በአገር ደረጃ ያለው አለመግባባት ለጠቅላላ ሕዝቡ ፈተና ሆኖ ለቤተ ክርስቲያኗ ፈተና ምንጭ ከሆኑት አንዱ እና አመቺ ሁኔታ የፈጠረው በመላው አገሪቱ ያለው አለመግባባት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህም ሳቢያ “ገዳማውያን መነኮሳት፣ መምህራን፣ ካህናት፣ ምዕመናን እና አብያተ ክርስቲያናት ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ በሰላም ወጥቶ መግባትም አጠራጣሪ ሆኖአል፤ ይህንን ችግር ለመፍታት የሚደረግ ጥረትም ጎልቶ አይታይም።”

ባለፉት ዓመታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ በሚካሄዱ ግጭቶች እና በሚፈጸሙ ጥቃቶች አብያተ ክርስቲያናት፣ አገለግጋዮች እና ምዕመናን ኢላማ ተደርገው ጉዳት መድረሱን ቤተ ክርስቲያኗ ከዚህ በፊት ማስታወቋ ይታወሳል።

ይህ ዛሬ ረቡዕ ግንቦት 21/2016 ዓ.ም. የተጀመረው ዓመታዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በወሳን የቤተክርስቲያኗ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ያሳልፋል።

ፓትሪያርኩም ጉባኤው “ወሳኝ እና ወቅታዊ እንዲሁም ሐዋርያዊ እና ቀኖናዊ በሆኑ የቤተ ክርስቲያናችን ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ለቤተ ክርስቲያንና ለአገር የሚበጁ ነገሮችን በማየት ጠቃሚ ውሳኔዎችን እንዲያሳልፍ” አሳስበዋል።

Source: BBC amharic

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *