ዛዲግ-አብርሃ
News

አቶ ዛዲግ አብርሃ ከተወረወረባቸው ቦንብ ለጥቂት መትረፋቸው ተሰማ!

የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕረዝዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ እና ሌሎች የፌደራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በሰሜን ወሎ ዞን ወልድያ ከተማ የቦንብ ጥቃት እንደተፈፀመባቸው የአማራ ድምፅ ሚዲያ የወሎ ዘጋቢዎች ለማረጋገጥ ችለዋል።

በጥቃቱ በባለስልጣናቱ አጃቢዎች ላይ መጠነኛ ጉዳት ከማስከተሉ በስተቀር በሰው ህይወት ላይ የደረሰ የከፋ ጉዳት አለመኖሩ የተረጋገጠ ሲሆን ነገር እነ ዛዲግ ሲንቀሳቀሱባቸው የነበሩትን ጨምሮ በርካታ ተሽከርካሪዎች መውደማቸው ታውቋል።

አቶ ዛዲግ አብርሃን ጨምሮ የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት የፓለቲካ ዘርፍ ኃላፊ እና የአማራ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ባሉበት ስፍራ ነው የቦንብ ጥቃቱ የተፈፀመው ተብሏል።

የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕረዝዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ፣ የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት የፓለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር ዘሪሁን ፍቅሩ፣ የአማራ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መንገሻ ፈንታው እና የሰሜን ወሎ ዞን ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም በዞኑ ስር የሁሉም ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች “ዘላቂ ሰላም በማፅናት እግር መትከል” በሚል መሪ ቃል ትናንት ግንቦት 26/2016 ዓ/ም በወልድያ ከተማ ስብሰባ አካሂደዋል።

አመራሮቹ ስብሰባውን ካካሄዱ በኋላ ለደህንነታቸው ሲባል ከፍተኛ ጥበቃ ባለበት የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ፅ/ቤት ህንፃ ውስጥ እንዲያርፉ የተደረገ ሲሆን በዚህ ስፍራ እንዳሉም የቦንብ ጥቃት እንደተፈፀመባቸው ነው የወሎ ግንባር ዘጋቢዎቻችን ለማረጋገጥ የቻሉት።

በቦንብ ጥቃቱ ባለስልጣናቱ ያረፉበትን የዞኑን ፅ/ቤት ሲጠብቁ የነበሩ የአድማ ብተና አባላት ላይ መጠነኛ ጉዳት ከማድረሱ በስተቀር በሰው ሕይወት ላይ የከፋ ጉዳት አላስከተለም የተባለ ሲሆን ባለስልጣናቱ ሲንቀሳቀሱባቸው የነብሩት ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውም ነው የታወቀው።

ጥቃቱ የተፈፀመው ምሽት 1:30 ገደማ ሲሆን ከጥቃቱ በኋላ በአከባቢው ከፍተኛ ውጥረት ነግሶ እንደነበርም ተገልጿል።

በከተማዋ የነበረው የሰሜን ምስራቅ ዕዝ ሰራዊት ፔምፔ የተባሉ ብረት ለበስ ታንኮችን ጨምሮ ዙ23 እና ሌሎች ከባባድና የቡድን መሣሪያዎችን ታጥቆ በከተማዋ ሲንቀሳቀስ ተስተውሏል ሲሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ለአማራ ድምፅ ገልፀዋል።

የቦንብ ጥቃቱ በሌሎች የከተማዋ አከባቢዎችም በመቀጠሉ አቶ ዛዲግ አብርሃን ጨምሮ ለክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ደህንነት ሲባል የነበሩበትን አከባቢ እንዲለቁ ተደርገው ከፍተኛ ቁጥር ባለው ወታደር ታጅበው ወደ ሼክ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲ ስታዲየም ተወስደው ማደራቸውንም ነው ጣቢያችን ለማረጋገጥ የቻለው።

ከፍተኛ የፌደራልና የክልል አመራሮቹ ከዞንና ወረዳ እንዲሁም ከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች ጋር “ዘላቂ ሰላም በማፅናት እግር መትከል” በሚል መሪ ቃል ስብሰባውን ያካሄዱት በወልድያ ዩኒቨርስቲ ቅጥር ጊቢ ውስጥ የተማሪዎች መመረቂያ አዳራሽ ላይ ሲሆን ለባለስልጣናቱ ደህንነት ሲባል የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች እንቅስቃሴ ተገድቦ መዋሉም ነው የታወቀው።

በስብሰባው ስለ ሰላም፣ ልማትና መልካም አስተደደር ጉዳዮች ተነስቶ በወፍ በረር ውይይት ተደርጎበታል የተባለ ሲሆን ሰፊውን ሰዓት የፈጀው ግን የፋኖ ኃይሎችን እንዴት እናጥፋ በሚል የተነሳው ሃሳብ ላይ ነው ሲሉ አንድ ስማቸው እና የስራ ኃላፊነታቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የስብሰባው ተሳታፊ ለአማራ ድምፅ ገልፀዋል።

አመራሮቹ ስብሰባውን ሲመሩ ውለው ወደ ተዘጋጀላቸው ማረፊያ ክፍል እንደደረሱ ነው የቦንብ ጥቃቱ የተፈፀመባቸው።

ምንጭ፡ የአማራ ድምፅ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *