ግንቦት 7,2017 ዓ.ም.
ለሚመለከተው ሁሉ፣ በአስቸኳይ ይሰራጭ፤
ጉዳዩ፤ የኢትዮጵያ ዶክተሮችና የጤና ሙያተኞች ንቅናቄን ስለመደገፍ፤
የኢትዮጵያ ዶክተሮችና የጤና ባለሙያዎች እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ፣ የሚሰጣቸው ደሞዝ ኢትዮጵያ ዛሬ በምትግኝበት ኢኮኖሚያዊና የኑሮ ሁኔታ በበቂ ሊያኖራቸው የማይችል መሆኑን፣ የጤና መድህን (ኢንሹራንስ) እንደሌላቸውና እንደሚያስፈልጋቸው፣ የሚሠሩባቸው ሁኔታዎችም ምቹ እንዳልሆኑ በመግለጽ ጉዳያቸው በሰላማዊ መንገድ መፍትሄ እንዲሰጠው ለሚመለከተ የመንግስት አካል ከአንድ ወር በፊት ማቅረባቸው ይታወሳል። ሆኖም ግን፣ የእነዚህን የጤና ባለሙያዎች ጥያቄ የሚገባውን መልስ በወቅቱ ባለመስጠታቸው እነሆ ዛሬ የጤና ባለሙያዎቹ በከፊል የሥራ ማቆም
አድማ እንዲያደርጉ ተገደዋል። በዚህ በተፈጠረው ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግሥት ዶ/ር ዮናታን ዳኝው፣ የኢትዮጵያ የጤና ሙያተኞች ማህበር ሊቀመንበርና ሌሎች ከፍተኛ ችሎታ ያላቸውን ዶክተሮች በማሰርና በማስፈራራት ላይ ይገኛል። የኢትዮጵያውያን የትብብር ንቅናቄ፣ በእነዚህ ዶክተሮችና የጤና ባለሙያዎች ላይ የሚያደርሰውን ህገ ወጥ ማዋከብና ማሰር መንግሥት በአስቸኳይ እንዲያቆምና ለጥያቄያቸው አስፈላጊውና ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ የኢትዮጵያውያን የትብብር ንቅናቄ አጥብቀን እንጠይቃለን።
የኢትዮጵያውያን የትብብር ንቅናቄ ከሶስት ወራት በፊት በውጭ አገር የምንኖር ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆንን ግለሰቦች፣ ማኅበሮችና ድርጅቶች፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ አሁን የምትገኝበትን አሳሳቢ ሁኔታ በመገንዘብ፣ በመሀከላችን ያሉትን የፓለቲካና የአስተሳሰብ ልዩነቶች ወደ ጎን በመተው፣ በጋራ በመስራት አገራችንን ለማዳን ጉልኅ አስተዋጽኦ ሊያደርግ የሚችል ትልቅ ኅብረት፣ የትብብር፣ የቅንብርና የመተጋገዣ አካል በመፍጠር ነው።
ትብብሩ በአሁኑ ወቅት ስምንት መስራች ድርጅቶችና ሁለት ተባባሪ ድርጅቶች አሉት። እነዚህም፦ ፩)ኢትዮጵያዊነት፣ ፪)የኢትዮጵያ አሜሪካውያን ዜጎች ምክር ቤት፣ ፫)ኢትዮጵያን እናድን መድረክ፣ ፬) የአሜሪካን ኢትዮጰያዊያን የሕዝብ ጉዳይ ኮሚቴ (ኤፓክ)(ተባባሪ)፣ ፭) ኒውዮርክ ትራይ ስቴት፣ ተስፋ ለኢትዮጵያ፣ ፮)የሶማሌ ዲሞክራሲያዊ ካውንስል፣ ፯)የኢህአፓ ድጋፍ ኮሚቴ፣ ፰)የኅብረ፡ኢትዮጵያ ግብረ ሀይል ሲሆኑ፣ በተባባሪነት፣ ፩)ግሎባል የአማራ ዲያስፖራ መድረክና ፪)ቪዥን ኢትዮጵያ ናቸው።
በአሁኑ ወቅት ትብብሩ የውስጥ ደንቦችን በማዘጋጀት፣ የተለያዩ ግብረ ኃይሎችን በማቋቋምና የሥራ ክፍፍል በማድረግ፣ እንዲሁም የድርጅቱን የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ በማውጣት ወደ ሥራ ገብቷል። ከዚህ በተጨማሪ፣ ትብብሩን ለማሳደግ ለሌሎች ድርጅቶችና ተዋቂ ግለሰቦች እንዲቀላቀሉት ጥሪ እናደርጋለን።
በትብብር ትግላችን ኢትዮጵያ ታሸንፋለች!!!
አለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን ትብብር ንቅናቄ።
ዶር ባደገ ቢሻው፤ ሊቀ መንበር፤
የኢትዮጵያውያን ትብብር ንቅናቄ፤
መግለጫውን ለማንበብ፡ የኢትዮጵያውያን የትብብር ንቅናቄ የድጋፍ መግለጫ፤