የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክረተርያት የሆኑት አቶ ንጉሡ ጥላሁን ዛሬ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ ቀደም ሲል ከነበሩት የሕክምና እና የለይቶ ማቆያ ማዕከላት በተጨማሪ 180 ያህል ለይቶ ማቆያዎች ተዘጋጅተዋል ብለዋል።
እነዚህ 180 ተቋማት ከ180 ሺህ በላይ ሰዎችን የማስተናገድ አቅም እንዲኖራቸው ተደርጎ የሰው ኃይልን በማጠናከር እንዲሁም አስፈላጊ የሚባሉ ቁሳቁሶችም ዝግጅት እየተጠናቀቀ ነው ብለዋል።
አቶ ንጉሡ አክለውም እነዚህ ስፍራዎች፣ ሕክምና ተቋማት፣ ሆቴሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ መሆናቸው ገልፀዋል።
ከባህር ማዶ ለሚመጡ ሰባት ሆቴሎች መዘጋጀታቸውን አስታውሰው፣ አጠቃላይ ስፍራዎቹ በፖሊስ ጠንካራ ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑን አስረድተዋል።
ከዚህ ቀደም ሕብረተሰቡ በሰጠው ጥቆማ መሰረት ሶስት ሰዎች ከለይቶ ማቆያ ውጪ ተገኝተው ወዲያውኑ ከሌሎች ጋር ሳይቀላቀሉ ወደ ማቆያ እንዲገቡ ተደርገዋል ብለዋል።
አቶ ንጉሡ አክለውም ባለፉት ሁለት ቀናት ብቻ 47 ሚሊየን ብር ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የገንዘብ ድጋፍ ተሰብስቧል ብለዋል።
ይህም ከዚህ ቀደም ከተገለፀው 150 ሚሊየን ውጪ መሆኑን ጠቅሰው በአጠቃላይ ወደ 197 ሚሊየን የገንዘብ ድጋፍ መሰብሰብ መቻሉንም ገልፀዋል።
እንደ አቶ ንጉሡ መግለጫ ከሆነ ኮሮናቫይረስን ለመመርመር በአዲስ አበባ ብቻ ሶስት ላብራቶሪዎች ተዘጋጅተዋል።
Source: BBC Amharic