አቢይ
News

ህግ የበላይነትን በማስከበር የዜጎችን ህይወትና ንብረት መጠበቅ የመንግስት ቅድሚያ ሃላፊነት ነዉ! – ኤድመንተን ካናዳ የምንኖር ትዉልደ ኢትዮጵያዉያን

ሃምሌ 12, 2012 ዓ.ም

የተከበሩ ዶ/ር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ጠ/ሚንስቴር፣

ሎሬንዞ ትዕዛዝ መንገድ
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
ስልክ፦ 251 111 226 767
ፋክስ፦ 251 111 226 292
ኢ-ሜይል፦ info@pmo.gov.et
ፖ.ሣ.ቁ፦1031

በኤድመንተን ካናዳ ከሚኖሩ ትዉልደ ኢትዮጵያዉያን

በመጀመሪያ፣ በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ መገደል፣ ከዚያም ተያይዞ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል ዘር-ተኮር በሆነ አረመኒያዊ ግድያ ህይወታቸዉን ስላጡት 167 ንጹሃን ኢትዮጵያውያን የተሰማንን ከፍተኛ ሃዘን መግለጽ እንወዳለን። በተጨማሪም በእድሜ ዘመናቸዉ ጥረዉ ግረዉ ያፈሩት ሃብት በእብሪተኛ ቄሮዎች ለወደመባቸዉ ወገኖች፣ ምንም እንኳ ህይወት የማጣትን ያህል ባይሆን፣ በድሃ አገር ለሚኖር ዜጋ የሚያስከትለዉን የኑሮ መቃወስ ስለምንረዳ፣ የተሰማንን ቁጭት ማሳወቅ እንፈልጋለን።

ይህን እልቂትና ዉድመት ይበልጥ አሳዛኝ የሚያደርገዉ የዜጎችን ህይወትና ሁለንተናዊ ደህንነት የመጠበቅ ሃላፊነት ያለበት የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ሃላፊዎችና የጸጥታ ሃይሎች ያሳዩት ቸልተኝነት ሲሆን፣ እነዚህ ኃይሎች ከዚህ በፊትም ለነበሩት ዉድመቶችና የሰዉ ህይወት ጥፋት ጭምር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከተጠያቂነት ሊያመልጡ አይችሉም ብለን እናምናለን።

የአርቲስት ሃጫሉን ቀጥተኛ ገዳዮችና በማግስቱ የአርቲስቱን ግድያ እንደመሳሪያ ለመጠቀም፣ ከአርቲስቱ ቤተዘመድ ፈቃድና ፍላጎት ዉጭ አስከሬኑን ወደአዲስ አበባ በመመለስ በከተማዋ ዉስጥ መጠነ ሰፊ ቀዉስ ለመፍጠር፣ ቢቻልም የመንግስት ስልጣንን ለማብረክረክ አልመዉ የተንቀሳቀሱ ግለሰቦችንና ቡድኖች በቁጥጥር ስር በማዋል፣ ቆስቆሽ ሚዲያዎችን በመዝጋትና የኢንተርኔት አገልግሎት በማቋረጥ ሊፈጠር ይችል የነበረዉን የባሰ እልቂት ለማስቆም መንግስት የወሰደዉን ፈጣን እርምጃ እናደንቃለን። በኦሮሚያ ክልል የደረሱ ዘር ተኮር ግድያዎችና የንብረት ዉድመቶች ላይ የተሳተፉ ቄሮዎችን ብሎም በጥፋቱ የተሳተፉ ወይም በቸልተኝነት የተመለከቱ የአስተዳደርና የጸጥታ ሃላፊዎችን በህግ ቁጥጥር ስር ለማዋል የተወሰደዉን እርምጃ እንደግፋለን።

ዉድ ጠ/ሚ፦ ወደስልጣን ከመጡ ጀምሮ የህግን በትር ባጥፊዎች ላይ ፈጥኖ ላለማሳረፍ ያሳዩትን ትዕግስት ልብ እንላለን። እርስዎ በተደጋጋሚ እንዳሉት፣ በጭቆና እና ባፈና ስር ለአስርት አመታት ለኖረ ህዝብ የተወሰነ የህግ ታጋሽነት ማሳየቱ ተቀባይነት ሊኖረዉ እንደሚችል እናስባለን። ይሁንና ከእለት ወደእለት እየባሰ እንጂ እየተሻለዉ ያልመጣዉ የአገሪቱ አለመረጋጋትም ሆነ በየጊዜዉ እየፈሰሰ ያለዉ የንጹሃን ደምና የንብረት ዉድመት መንግስት ያሳየዉን ትዕግስት ዋጋ የሚያሳጣ እንጂ “ይበል” የሚያስብል እንዳልሆነ ማመን ያስፈልጋል። በተለይ ባለፈዉ ጥቅምት 2012 በተከሰተዉ ተመሳሳይ እልቂት ወቅት፣ መንግስትዎ የእልቂቱ ዋና ቀስቃሽ የሆኑ እብሪተኛና አክራሪ ብሄረተኞች ላይ ተገቢዉን እርምጃ በመዉሰድ ፋንታ፣ እነዚህን ወንጀለኞች ለማባበል የተሄደዉ እርቀት ለሰሞኑ እልቂትና ዉድመት ዋና አደፋፋሪ ምክንያት መሆኑን መቀበል የግድ ነዉ፤ ለዚህም እርስዎም ሆኑ መንግስትዎና የኦሮሚያ መስተዳድር የተወሰነ ሃላፊነት ሊሰማችሁ ይገባል ብለን እናምናለን።

ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ባሉባት አገር የሚደረግ የፖለቲካ ሽግግር አስቸጋሪ መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም። ከዚህ አንጻር፣ የእርስዎ አመራር ባለፉት ሁለት አመታት በተለይ በኢኮኖሚዉና በማህበራዊ መስኩ ያስመዘገቡትን ቀላል የማይባሉ ስኬቶችን እናደንቃለን። የፖለቲካ ሽግግሩ ግን ዛሬም ቅጡ ያለየለት፣ ሲበዛም

ወደኋላ የሚያፈገፍግ መሆኑ፣ ለዚህም ዋነኛዉ ምክንያት የአገሪቱን ሰላምና መረጋጋት በዘላቂነት መፍጠር አለመቻሉ መሆኑን ስናስብ ከፍተኛ ስጋት ይገባናል።

ከስልጣን የተወገዱ የህወሃት መሪዎችና ለስልጣን የሚቋምጡ አክራሪ ብሄረተኞች የተደላደለች የበለጸገች፣ አንድነቷ የጠነከረና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ላለማየት እንደተማማሉ በአደባባይ ያሳወቁት ጉዳይ ነዉ። እርስዎን ዋና ጠላት አድርገዉ የፈረጁበትም ምክንያት ግልጽ ነዉ። እነዚህ ኃይሎች ባለፉት ሁለት አመታት ያልፈነቀሉት ድንጋይ ያላደረጉት ቁስቆሳ የለም። በሌላ ጎን፣ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ተገዳዳሪ የሆነችዉ ግብጽ የአባይ ግድብ ሙላትን ለማስተጓጎል ማናኛዉንም ስትራቴጂ ከመጠቀም ወደኋላ እንደማትል፣ በአገር ዉስጥ የሚፈጠርን ክፈተትም ሆነ አለመረጋጋት ለማባባስና በጊዚያዊ ጥቅምና የስልጣን ፍላጎት የሚናዉዙትን ለመጠቀም ወደኋላ እንደማትል መገመት ቀላል ነዉ። በቅርቡ ለተፈጠረዉ አሳዛኝ እልቂትና ዉድመትም የእነዚህ ሶስት ኃይሎች የተናጥልና የተቀናጀ እንቅስቃሴ እንዳለበት ማመን አያስቸግርም።

ዉድ ጠ/ሚ፦ ያም ሆኖ ግን፣ አንድ መቀበል ያለብን ሌላ ወሳኝ እዉነት፣ አገሪቱን በቋንቋና በዘር ከልሎ፣ የብሄረሰቦችን የባህል፣ የቋንቋና ሎሎች እሴቶች የማሳደግ ሳይሆን፣ አንዱ ብሄረሰብ ከሌላዉ በአይነ ቁራኛ እንዲተያይ በማድረግ ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲያስችል ታቅዶ፣ ከ29 አመታት በፊት የተዘረጋዉ የፖለቲካ ስርአትና የክልል የጸጥታ ኃይሎች አወቃቀር በስራ ላይ እስካለ ድረስ የዉስጥም የዉጭም ጠላቶች የመጫወቻ ሜዳ ማግኘታቸዉና የሰሞኑ አይነት ዘር-ተኮር እልቂትና ዉድመት ለወደፊትም መፈጠሩ አይቀሬ መሆኑን ነዉ። ይህን እዉነት ለመቀበል ከአሁን የተሻለ ጊዜ አይኖርም ብለን እናምናለን።

ከዚህ በመነሳት እኛ ካናዳ፣ኤድመንተን ከተማ ዉስጥ የምንኖር ኢትዮጵያዊያንና ትዉልደ ኢትዮጵያዊያን፦

1. በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ላይ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ተሳታፊ የነበሩትንና በቀጣይም የአርቲስቱን አስከሬን በመጥለፍ በአዲስ አበባ ሁከት ለፈጠሩትና ለብዙዎች ሞት ምክንያት የሆኑትን ግለሰቦች በህግ ስር ዉለዉ አስፈላጊዉ ህጋዊ ፍርድ እንዲበየንባቸዉ፤ እርስዎ እንዳሉትም፣ ከእንግዲህ በወንጀለኞች ላይ የህግ ብይን እንጂ “አንተ ተዉ”; “አንተም ተዉ” የሚል የሽምግልና ሂደት ዉስጥ በመግባት መንግስት እጁን እንዳያስርና አገሪቱን ለሌላ እልቂትና ጥፋት እንዳያዘጋጅ ጥንቃቄ እንዲያደርግ፤

2. የአርቲስት ሃጫሉን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል በመቶዎች በሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን ላይ ለደረሰዉ አሰቃቂና አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ቀጥተኛ ተሳታፊ የሆኑ ግለሰቦችንና እልቂቱንና ዉድመቱን በቸልተኝነት የተመለከቱ ምናልባትም በተዘዋዋሪ የተባበሩ የመንግስት ባለስልጣናትና የጸጥታ ሃላፊዎች ላይ ለወደፊቱም ትምህርት የሚሆን ህጋዊ ፍርድ እንዲተላለፍባቸዉ፤

3. ከእንግዲህ ኢትዮጵያ ዉስጥ አንድም ዜጋ ቢሆን በፈለገዉ ቦታ የመንቀሳቀስ፣ የመስራት፣ የመነገድና ንብረት የማፍራት መብቱ ሙሉ በሙሉ እንደሚከበር፣ በማንነቱ ወይም በእምነቱ በህይወቱ፣ በደህንነቱ ወይም በንብረቱ ላይ ምንም አይነት ጥቃት እንዳይደርስበት የፌዴራልና የክልል መንግስታት ለኢትዮጵያ ህዝብ ቃል እንዲገቡ፣

4. በሰሞኑ በተፈጠረዉ እልቂት ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተሳተፉ ወይም እልቂቱን በቸልታ የተመለከቱ የአስተዳደርና የጸጥታ አካላት መኖራቸዉ የሚያረጋግጠዉ ሃቅ ቢኖር በአሁኑ ወቅት ያለዉ ክልላዊ የጸጥታና ደህንነት መዋቅር የዜጎችን ደህንነት በእኩልነት ሊያስጠብቅ እንደማይችል ነዉ። ስለዚህም በአሁኑ ወቅት በየክልሉ የሚገኙ የጸጥታና ደህንነት ሃይላት በፌዴራል መንግስት ስር ገብተዉ የክልል አመዳደባቸዉም ከሁሉም ብሄረሰብ በተዉጣጣ መልኩ እንዲሆን፤

5. መንግስት ከአርቲስት ሃጫሉ ግድያ ጋር ሆነ በቀጣይ ከተገደሉት ኢትዮጵያዉያንና ከደረሰዉ የንብረት ዉድመት ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸዉ፣ ህዝብን በማጋጨትም ሆነ ሰላምን በማደፍረስ የማይታሙ፣ ሰላማዊ ስብእናቸዉን በአስርት አመታት ዉስጥ ያስመሰከሩ ፖለቲከኞች በእስር ዉስጥ ማስገባቱን ልብ ብለናል። ምናልባትም ሁኔታዎች በተሳከሩበት ወቅት የተወሰደ እርምጃ ሊሆን ይችላል ብለን ስለምንገምት፣ አሁን ከተፈጠረዉ አንጻራዊ መረጋጋት አንጻር፣ ለራሱም ታአማኒነት ሲል መንግስት እነዚህን ግለሰቦች እንዲፈታ፣

6. መንግስት ቀጣዩን ትዉልድ በፍቅር፣ በአብሮነትና በመቻቻል መንፈስ እንዲያድጉና፣ በተለይ ባለፉት 30 አመታት የተዘራዉን የልዩነትና የጥላቻ ስሜት ለመንቀል ሰፊ የትምህርት ፕሮግራም እንዲቀረጽና እንዲተገብር፤

7. በዚህ ዘመን ያሉ የኢትዮጵያ ታዳጊ ወጣቶች አንድነታቸዉን ለማጠንክር ይችሉ ዘንድ አያቶቻቸዉና ቅድም አያቶቻቸዉ፣ ቋንቋ፣ ብሄረሰብ፣ ወይም ኃይማኖታዊ እምነት ሳይለያቸዉ በህብረት ተነስተዉ ያደረጉትን የፀረ ቅኝ ግዛት ተጋድሎና ያስገኙትን የነጻነትና አገራዊ ሉአላዊነት ታሪክ በትምህርት ቤት ከልጅነታቸው ጀምሮ እንዲማሩ እንዲደረግ፤

8. በመጨረሻም፣ መንግስት የአባይ ግድብን ሙሌት በተመለከተ በቅርቡ የወሰደዉን ቆራጥ እርምጃ እያደነቅንና ከእኛም የሚጠበቀዉን ለማድረግ ቃል እየገባን፣ በቀጣይ ከግብጽና ከሱዳን ጋር የሚያደረጉት ድርድሮች የኢትዮጵያን ዘላቂ ሉአላዊ ጥቅምና መብት ያለማወላዉል የሚያረጋግጡ እንዲሆን፤

ከመልካም ምኞት ጋር በአክብሮት እናሳስባለን።

ኢትዮጵያ በአንድነቷ ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!!

በኤድመንተን ካናዳ የምንኖር ትዉልደ ኢትዮጵያዉያን

 

ለተፈጠረው ችግር ሁሉ ተጠያቂውና ሃላፊነት መውሰድ ያለበት የኢትዮጵያ መንግስት ነው – በዳንኤል ብ. ተክሉ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *