የአማራ ሕዝብ እና ሀገራችን ከገጠሟቸው ፈተናዎች ለመውጣት ዘላቂው መፍትሄ ሁሉንም ሕዝብ እና አካላት ባለቤት የሚያደርግ፣ ሀገራዊ መከራንም በጋራ መቀልበስ የሚያስችል ሥርዓትና ስሪት ማቆም መሆኑን ሳናሰልስ ተናግረናል፤ አስገንዝበናል፤ ወትውተናል።
የፍትህና እኩልነት ሥርዓት ስለማቆም ሳያሰልሱ መወትወትና መታገሉ በመሠረታዊነት አንዳችም ስህተት የሌለበት ቢሆንም ሀገራዊ ፕሮጀክቱ አማራውን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ከሚሠሩ የጥላቻ ኃይሎች ጋር በመሆን ማሳካት እንደማይቻል ግለፅ እየሆነ የመጣ እውነታ ሆኗል።
ሁሉን አቀፍ በጎ ውጥኖች በተግባር እስኪተረጎሙና የጥፋት ኃይሎችም ልቦና ገዝተው በባለቤትነት ስሜት ጭምር የየራሳቸውን አዎንታዊ አበርክቶ መወጣት ሊጀምሩ ይችላሉ ከሚለው እሳቤ በፊት የሕዝባችን ህልውና የሚቀድም መሆኑን በመረዳት አሳዳጅና ገዳዮቻችን ክላሽ፣ ሜንጫና ቀስታቸውን ጥለው እስኪመጡ ድረስ ለሽግግር የሚሆን የተቀናጀ እርምጃ እንዲወሰድ ዛሬም ለማሳሰብ እንወዳለን።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የመላው አማራ ሕዝብ ወኪል መሆኑን ማረጋገጥ ያለበት ወቅት መሆኑን በመረዳት በትሕነግ ላይ የወሰደውን ዓይነት ህልውናን የማስከበር ታሪካዊ ቁርጥ ውሳኔ በማሳለፍ በመተከል እየተፈፀመ ያለውን የዘር ፍጅት ለማስቆም ተግባራዊ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል። በዚህ ረገድ አብን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለማድረግ ያለንን ቁርጠኝነትም መግለጽ እንወዳለን።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት በዜጎቻችን ላይ ለሚፈፀመው ጭፍጨፋ ቀዳሚ ተጠያቂ ከመሆኑም በላይ በጭፍጨፋው የተሳተፉ ከክልል እስከ ቀበሌ የሚገኙ አመራሮችን በቸልታ በማለፍ የጥቃቱ ተባባሪ ሆኖ ይገኛል።
የፌደራል መንግሥትም ኦሮሚያንና ቤንሻንጉል ጉሙዝን ጨምሮ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመውን ሰፊ የዘር ማጥፋት ወንጀል ማስቆም ካለመቻሉም በላይ ወንጀሉን በስሙ ባለመጥራት በዜጎቻችን ላይ ለሚፈፀመው ጅምላ ፍጅት ተባባሪ በመሆኑ ከተጠያቂነት እያመልጥም።
በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለውን የማያባራ የዘር ፍጅት መላው ኢትዮጵያውያን እንድታወግዙና የአማራ ሕዝብ ህልውናውን ለማስቀጠል ከሚያደርገው ትግል ጎን እንድትቆሙም ንቅናቄያችን በአክብሮት ይጠይቃል። ንቅናቄያችን በመተከል በአማራ ወገኖቻችን ላይ የሚፈፀመውን የማያባራ የዘር ፍጅት በጽኑ እያወገዘ፤ ለዘር ፍጅት ሰለባ ቤተሰቦችና ለመላው የአማራ ሕዝብም መጽናናትን ይመኛል።
አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፥ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
ታኅሣሥ 15 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ሸዋ፥ ኢትዮጵያ!