የአገራችን ኢትዮጵያ ህልውና በጥያቄ ውስጥ ሲገባ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም፡፡ የአሁኑን ለየት የሚያደርገው ግን የሕዝባችንንና የአገራችንን ታሪክ ፈጽሞ የካደ፣ ከውስጥ የበቀለ፣ ከውጭ ታሪካዊ ጠላት ጋር ያበረ የእናት ጡት ነካሽ የሆነው አሸባሪው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በሚባል ድርጅት የሚመራ መሆኑ ነው፡፡
የውጭ ጠላቶች፣ እንደ ግብጽ፣ ቱርክ፣ ጣሊያን ዓይነቶቹ ሲመጡ፣ ከቆዳ ቀለም አንስቶ፣ በቋንቋና ባህል ከሕዝባችን ፈጽሞ የተለየ ስለሆነ የውጭ ወራሪ መጣብህ በማለት ሕዝቡ እንዲከላከል ጥሪ ማድረግ ቀላል ነው፡፡ እንዲህም ስለሆነ ነው በአፄ ዮሃንስ ዘመን ግብጾች፣ ቱርኮች እንዲሁም ጣሊያኖች ኢትዮጵያን ለመውረር በቀይ ባሕር በኩል ሲመጡ፣ በጀግናው ራስ አሉላ አባ ነጋ ወታደራዊ አመራር አሸንፈን የአገራችንን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት እንዲሁም የሕዝባችንን አንድነት አስከብረን በውጭ ኃይሎች ያልተገዛች አገር አድርገን አገራችንን በክብር ማቆየት የቻልነው፡፡
ህወሓት/ወያኔ የሚባል የአሁኑ ጠላት የአገራችንን ታሪክ ከሃቅ የራቀ መልክ አስይዞ፣ ለበርካታ ሺህ ዓመታት ተጋብቶና ተዋልዶ፣ የአገሩን አንድነትም ለማስጠበቅ በጋራ ደሙን አፍስሶ፣ አጥንቱን ከስክሶ የኖረን ሕዝብ እንዲሁም አድዋ ላይ የፋሽሽት ጣሊያንን ወረራ በአንድነት ድባቅ በመምታታ ለጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ኩራት የሆነውን ሕዝባችንን በዘር በመለያየት እርስ በርስ እያጋደለ፣ አሁን ያለንበት ደረጃ በማድረስ የአገራችንን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት አደገኛ ሁኔታ ላይ በማድረስ መበታተን ደረጃ ላይ አድርሷታል፡፡