Current

እስክንድር ነጋ ላይ ይካሄዳል ሰለተባለው ዘመቻ

Aklilu Wondaferewአክሊሉ ወንድአፈረው

 

በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይውት የቀጠፈውን የሰሞኑን የደብረ ኤልያስ ገዳም ዘመቻውን በመቀጠል መንግስት “እስክንድር ነጋን ለመያዝ ወይም ለመግደል እያሳደድኩ ነው” ብሏል፡፡

እስክንድር ከብልጽግና ጋር ግለፅ የፖለቲካ አመለካተት ልዩነት እንዳለው በግልጥ ይታወቃል፡፡ በዚህ አኳያም መንግስት የ እስክንድር ተቃውሞ ሁል ጊዜም እረፍት እንደነሳው በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ብልጽግና በእስክንድር ጉዳይ የሚሰማውን ክፍተኛ ስጋት ጠቅላዩ በአንድ ወቅት: እስክንድር ሰለአዲስ አበባ ባነሳው ጥያቄ የተነሳ “ ጦርነት እንገባለን” ማለታቸውን ማስታውስ ይህንኑ ያሳያል፡፡

ብልጽግና በአማራ ክልል ከእስክንድር መሰወር በፊትም ቢሆን በክልሉ ተቃውሞን በሀይል ለማጥፋት እንደተንቀሳቀሰ የሚታወቅ ነው፡፡

በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ እንዲሉ አሁኑ “እስክንድርን ለመያዝ” በክልሉ እየተጠናከረ ዘመቻ ለማካሄድ ገፊ የሆኑት ጉዳዮችም መንግስት እስክንድርን በተመለከት ለአመታት የተሸከመው ፍራቻና እያደገ የመጣውን የክልሉን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሁሉ በወታደራዊ ሀይል ለማንበርከክ የሚታየው ጥድፊያ እንደሆነ ያሳያል፡፡

ያም ሆኖ ግን ቀደም ሲል በክልሉ የተካሄዱ ወታደራዊ ዘማቻዎች ወጤት: በጥፋት ላይ ጥፋትን ማስከተል : በአካባቢው ከፍተኛ አለመረጋጋትን መጋበዝ እንጂ መንግስት የፈለገውን የተቃውሞ መክሰም አላስገኙም፡፡ ይህ የሚያሳየው ወታደራዊ የሀይል ዘመቻ የፖለቲከ ልዩነትን ለመፍታት ብቃት ያለው ዘዴ አለመሆኑን ነው፡፡

እስክንድር የረጅም ጊዜ የስላም ታጋይ እንደሆነ ይታወቃል::  አሁን ወዳለበት ሁኔታ የተገፋውም በተደጋጋሚ በሰበብ አስባቡ ለአመታት ሲታሰር እና ሲፈታ ከቆየ፣ በኳላ በተለይም በአማራ ማህበረስብ እና በአዲስ አበባ ላይ የሚካሄደው የመብት ረገጣ እየከፋ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ነው ብየ አስባለሁ፡፡

ሰለዚህም መፍትሄው የግለሰቡን ይህወት ማጥፋት ወይም ግለሰቡን ማሰር ላይ ያተኮረ ሳይሆን የሰላማዊ ታጋዮችን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ የሚገፋፋውን የሰላማዊ ትግል መድረክ መጣበብ፣ የህፍትህ መጥፋት እየሰፋ የመጣውን የመብት ረገጣ ጉዳይ መፍታት ወዘተ በሚቻልበት ራእይ እና አስራር ላይ ያተኮረ ሊሆን ይገባዋል፡፡

የአካባቢው ህዝብ እስክንድርን ቢያቅፍና ቢደግፈው ብሶቴን ያስተጋባል፣ የኔን ችግር ይኖራል ይካፈላልም ብሎ እንጂ ሌላ እንዳልሆነ ማስብ ያስፈልጋል፡፡

መንግስት አሁን በተያያዘው ወታደራዊ ዘመቻ ብዙ ህይወት አጥፍቶ ንብረትና ቅርስ አውድሞ አስክንድርን ሊይዘውም ሊገድለውም ይችላል፡፡ ይህ ግን በአካባቢው ሊፈጥረው የሚችለው ፖለቲካዊ ለውጥ ሰፊ ይሆናል መረጋጋትንም ያስከትላል ከማለት ሁኔታውን እጅግ ያወሳስበዋል ብየ እሰጋለሁ፡፡ ይህን ለማለት ያስደፈረኝ በጥቂቱ ላንሳ፡

1ኛ) ካሁን በፊት እንደታየውም እስክንድር በእስር በቆየበት ጊዜ ሁሉ በአማራ ክልል የታየው ተቃውሞ ጨመረ እንጂ እልቀነሰም ፡፡ አሁን አስክንድር ቢታሰር ወይም ቢገደል እንኳ በክልሉ የሚታየው የፖለቲካ አውድ እስካልተቀየረ እጅግ ብዙ እስክንድሮች እንደሚፈጠሩ መጠራጠር አያሻም፡፡ይህ በተደጋጋሚ በተከሰቱት እውነቶች የተመሰከረ ነው፡፡

2ኛ) ሌላው ጉዳይ በክልሉ የሚካሄደው ተቃውሞ እጅግ የተማከለ በአንድ ሰው (ማለትም እስክንድር) ብቻ የሚመራ እለመሆኑ ከውጭ ለምናየውና የትግል እድገቱን ቅደም ተከተል ለሚከታተል ግልጽ ነው፡፡ ይህም ሰለሆነ እስክንድርን በማሰርም ሆነ በመግደል በተወስነ ቦታ ጊዜያዊ ድል ይገኝ ይሆናል እንጂ የተቃውሞ እንቅስቃሴው ከእስክንድር ቀጥጥር ወጭ ሲካሄድ የቆየና አሁንም የቀጠለ በመሆኑ በእርሱ ላይ በሚወሰድ እርምጃ ተቃውሞውን በከፍተኛ ደረጃ ማደከም አይቻልም፡፡

መፍትሄው እስክንድርንና ተከታዮቹን ማሳደድና ማሰር ወይም መግደል አይሆንም፡፡ መፍትሄው እስክንድርን እና ደጋፊዎቹን እንዲሁም በአካባቢው ፖለቲካ ላይ ድርሻ ያላቸውን ሁሉ ያሳተፈ ሰላማዊ የፖለቲከ ድርድር፣ ማድረግ እና የጋራ መፍትሄ መፈለግ ነው፡፡

መፍትሄው በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን (ጠንከር ብለው የተደራጁትንም ይሁን ሌሎች ስብስቦች) በጠላትነት ፈርጆ ለማጥፋት ከመባከን በሰላማዊ መንገድ በቅን ልቦና የመፍትሄው አካል እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡

መፍትሄው በመንግስት በኩል ቀደም ሲል ለክልሉ ህዝብ የገባውን ቃል መፈጸም፣ የክልሉን ህዝብ ከቀን ወደ ቀን ወደ ከፋ ብሶት እየከተተው የሚገኘውን የአድልኦ፣ የጥቃት የማፈናቀል ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ የመከልከል ወዘተ ፖሊሲን መቀየር ነው፡፡ መፍትሄው በመላ ሀገሪቱ ለአመታት ተነቅሰው የወጡ መሰረታዊ ሀገ መንግስትዊ መዋቅራዊና ተቋማዊ ችግሮችን በሁሉም ባለድርሻዎች ተሳትፎ መፍታት ነው፡፡

ይህ ደግሞ ግለሰቦችንም ይሁን ቡድንን በመደለል የብልጽግናን አቋም እንዲቀበሉ ለማድረግ መጣር ውይም መሸወድ (ኮንቪንስም ኮንቪውስ ማድረግ) ሳይሆን የክልሉን የህዝብ ብሶት እና የፖለቲካ ለዩነትን እንጥሮ በማውጣት በንጹህ ልቦና በቅንነት በድርድር ለመፋታት መጣር ማለት ነው፡፡ ይህ ሂደት ሳይዘገይ አሁኑኑ ሊጀመር ይገባዋል፡

ጦርነት ይቁም ፣ ለፖለቲካ ችግራችን ሀቀና ፖለቲካዊ መፍትሄ አሁኑኑ፡፡

ይህ ሀገሩንና ህዝቡን የሚወድ የአንድ ግለሰብ አስተያየት ነው ፡፡ እርስዎስ ምን ይላሉ ከወደዱት ሽር ያድርጉ

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *