ከ2010 ዓ.ም. ለውጥ ማግሥት ወደ ኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ በጉልህ ብቅ ካሉ ፖለቲከኞች አንዱ የሆኑት አቶ ሙስጠፋ ሞሐመድ ዑመር ወይም ብዙዎች እንደሚጠሯቸው ‘ሙስጠፌ’ ራሳቸውን ጭምር በግል፣ እንዲሁም በቤተሰብ ደረጃ ሰለባ ያደረጋቸውና ለበርካታ ዓመታት የስደት ሕይወት የዳረጋቸው የሶማሌ ክልል የፖለቲካ ከባቢ በተጨባጭ መሻሻል እንዲያሳይ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ የአመራር ሚና የተጫወቱ ስለመሆናቸው ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል፡፡
አቶ ሙስጠፌ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ በኋላም ፕሬዚዳንት ሆነው ከተሰየሙበት ጊዜ ጀምሮ በክልሉ ይስተዋሉ የነበሩ የክልሉ ተወላጆች ያልሆኑ ነዋሪዎችን አብዝቶ የመግፋት አዝማሚያዎችን፣ እንዲሁም ለሃይማኖት ብዝኃነት ተፃራሪ የሆኑ በርካታ እንቅስቃሴዎችን በመግታት ረገድ ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻላቸው ይወሳል፡፡
በተጨማሪም የክልሉን ፖለቲካ በአገር አቀፉ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ንቁ ተሳታፊነቱ እንዲጨምር በማድረግ ረገድ የማይናቁ ተግባራትን ማከናወናቸው ይጠቀስላቸዋል፡፡
የተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በብርቱ የፀጥታ ችግር ውስጥ በሚገኙበት በዚህ ጊዜም እሳቸው የሚመሩት የሶማሌ ክልልን፣ በአንፃራዊነት የዜጎች ደኅንነት የሚጠበቅበትና የተሻለ ሰላምና ፀጥታ ካላቸው ክልሎች አንዱ ለማድረግ ችለዋል፡፡
ሪፖርተር፡- እስከ የ2010 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ ድረስ በስደት ላይ ነበሩ፡፡ አገር ውስጥ ከነበረው የለውጥ ኃይል ጋር ግንኙነት ነበረዎት ወይስ ወደ አገር ቤት ከተመለሱ በኋላ ነው የተዋወቃችሁት?
አቶ ሙስጠፌ፡- ለ11 ዓመታት በስደት ነበርኩ፡፡ አካሌ ውጭ ቢሆንም በመንፈስ ግን አገሬ ነበርኩ፡፡ በስደት እያለሁም በኢትዮጵያ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለዓለም ለማሳወቅ እየሠራሁ ነበር፡፡ ከዚያም የ2010 ዓ.ም. ለውጥ ሲከሰት ወደ አገር ቤት ተመልሼ የለውጥ ኃይሉን ተቀላቀልኩ፡፡
ሪፖርተር፡- የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ሆነው እንደተሾሙ በክልሉ ይስተዋሉ የነበሩ የብሔር ጥላቻ መሰል ግጭቶችን በማስቆም ሰላም አስፍነዋል፡፡ እርስዎ ከክልሉ ኃላፊነት ቢነሱ ሰላሙ ይቀጥላል? ይህንንስ የሚያስቀጥል ተቋም ተገንብቷል?
አቶ ሙስጠፌ፡- በትክክል፡፡ ያ ለውጥ በአንድ ሰው ጥረት ብቻ አልተገኘም፡፡ ነገር ግን በብዙ ሰዎች ጥረት እንጂ፡፡ እኔ ባልኖርም ለውጡ ይቀጥላል፡፡ ለውጡ ከላይ ጀምሮ በተደረገ የመንግሥትና የፓርቲ ድጋፍ ነው የተገኘው፡፡
ሪፖርተር፡- በአንድ ወቅት ‹‹ከብሔር ግጭት ነፃ የሆነች ኢትዮጵያን መፍጠር አለብን›› ብለው ነበር፡፡ ፓርቲዎ በዚህ ተሳክቶለታል?
አቶ ሙስጠፌ፡- ብልፅግና በወሰዳቸው ዕርምጃዎች ካለፉት አምስት ዓመታት ብዙ ለውጦች መጥተዋል፡፡ ከብሔር ጥላቻ እየተላቀቅን ነው፡፡ ብዝኃነት እንዳለ ሆኖ በአንድ አገራዊ ማንነት የማመን ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በሁለቱ የአገራችን ፅንፍ የረገጡ የፖለቲካ አመለካከቶች፣ ማለትም በብሔር ፖለቲካና በማዕከላዊ አገረ መንግሥትነት ዙሪያም የመግባባት ፖለቲካ እየመጣ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ፡፡ በቅርቡ በብልፅግና የተሰጡ ሥልጠናዎችም ላይ ተንፀባርቋል፡፡ እስካሁን ያሉት ለውጦች ጥሩና አበረታች ናቸው፡፡ ይሁንና ለውጡ ተግዳሮቶች እየገጠሙት መሆኑ ዕሙን ነው፡፡ በተለይ ለውጡን በበጎ የማይቀበሉ ኃይሎች በሚጋርጡዋቸው ተግዳሮቶች፡፡
ሪፖርተር፡- በ2010 ዓ.ም. ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ነበር፡፡ ነገር ግን ከለውጡ በኋላ አገሪቱ ወደ የማያባራ ግጭትና ጦርነት ውስጥ ገብታለች፡፡ ምክንያቱ ምንድነው?
አቶ ሙስጠፌ፡- ከለውጡ ወዲህ ለተፈጠሩት ግጭቶች የአገሪቱ የተበላሸ የፖለቲካ ባህል አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በእርግጥ በለውጥ ጊዜ ግጭቶች መፈጠራቸው ያልተለመደ አይደለም፡፡ በለውጡ ሥልጣን ያጡ ኃይሎች ተግዳሮት መደቀናቸውና አዲሱ ገዥ ፓርቲ እንዳይረጋጋ ማድረጋቸው ያልተደበቀ ሀቅ ነው፡፡ ለእነዚህ ግጭቶች ዋናው ምክንያት የቀድሞው ገዥ ኃይሎች በፈቃደኝነት ሥልጣን እስከ ወዲያኛው ለማስረከብና አዲሱ የለውጥ ኃይል ሥልጣኑን እንዳያደላድል አለመፈለጋቸው ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በብልፅግና ውስጥ ያሉ ኃይሎች ሕወሓትን ለመታገል (ለማሸነፍ) ተባብረው ነበር፡፡ ሕወሓት በጦርነት ከተሸነፈ በኋላ ግን ብልፅግና ውስጥ መፈረካከስ ተፈጥሯል የሚሉ የፖለቲካ ታዛቢዎች አሉ፡፡
አቶ ሙስጠፌ፡- ብልፅግናን የፈጠሩት አካላት ዛሬም ትብብራቸው የጠነከረ ነው፡፡ ከሕወሓት በስተቀር ነባሮቹ ሦስት ፓርቲዎችና የክልል ኃይሎች አንድ ሆነው አንድ ፓርቲ የሆነውን ብልፅግናን ፈጠሩ፡፡ ብልፅግና ውስጥ መፈረካከስ አልተፈጠረም፡፡ በግለሰቦች ደረጃ ሥልጣን መልቀቅና ሽግሽጎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ብልፅግና በተፈጠረ የመጀመሪያውና ሁለተኛው ዓመት ድረስ ከፓርቲው የወጡ ግለሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን አንተ ባልከው ደረጃ ውስጣዊ መፈረካከስ የለም፡፡
ሪፖርተር፡- ሕወሓት ብልፅግና ውስጥ ቢካተት ኖሮ የሰሜኑ ጦርነት ይከሰት ነበር? ጦርነቱን ለማስወገድ ለምን አልተቻለም?
አቶ ሙስጠፌ፡- ካለፈ በኋላ ማውራቱ ቀላል ሊሆን ይችላል፡፡ ግን በወቅቱ የነበረው አስተሳሰብና በወቅቱ የነበሩ የታጠቁ ኃይሎች ጦርነቱን ለማስቀረት መንግሥት ያደረገውን ጥረት ውጤታማ እንዳይሆን አድርገዋል፡፡ የነበሩት የትጥቅ እንቅስቃሴዎች ጦርነቱን አይቀሬ አድርገዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በሰሜኑ ጦርነት ወቅት የአልሸባብን ጥቃት ሲመክት የነበረው የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ነበር፡፡ አሁንስ ሥጋቱ ምን ያህል ነው?
አቶ ሙስጠፌ፡- በጎረቤታችን ደካማ አገረ መንግሥት እስካለ ድረስ የአልሸባብ የጥቃት አደጋ ሁሌ እንዳንዣበበ ነው፡፡ ፅንፈኛ ኃይሉ ሁሌም ኢትዮጵያን ለማተራመስ እንደተዘጋጀ ነው፡፡ እኛም ለመመከት ሁሌም ዝግጁ ነን፡፡
ሪፖርተር፡- የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ በሶማሊያ (አሚሶም) ወታደሮችን በአንድ ዓመት ውስጥ ከሶማሊያ እንደሚያስወጣ አስታውቋል፡፡ ይህ ክፍተት ለኢትዮጵያ ምን ያህል አደጋ አለው?
አቶ ሙስጠፌ፡- የሰላም አስከባሪው መውጣት አልሸባብ የሚያደርሰውን አደጋ ከፍ ያደርጋል፡፡ ለዚያም መዘጋጀት አለብን፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ያላት ግንኙነት ዋናዋን ሶማሊያ ያስከፋል ብለው ያስባሉ?
አቶ ሙስጠፌ፡- የኢትዮጵያ ፍላጎት ከተባበረች ሶማሊያ ጋር ጥሩ ግንኙነት መፍጠር ነው፡፡ ከሶማሌላንድ ጋር ያለን ግንኙነት ሶማሊያን ሊያስከፋት ይችላል፣ እኛ ላይ ግን ተፅዕኖ አያመጣም፡፡
ሪፖርተር፡- በኢሕአዴግ ጊዜ የሶማሌ ክልልና ሌሎች ታዳጊ የሚባሉ ክልሎች ወደ ዳር ተገፍተው ነበር፡፡ አሁን የተወሰኑ የሶማሌ ክልል ተወላጆች በፌዴራል መንግሥት ውስጥ ሥልጣን ስላገኙ ብቻ ሶማሌ ክልል ወደ መሀል መጥቷል ማለት ይቻላል?
አቶ ሙስጠፌ፡- አይቻልም፣ ሶማሌ አሁንም ወደ መሀል አልመጣም፡፡ ግን በፌዴራል ደረጃ ውክልና ማግኘት ራሱ ጥሩ ጅምር ነው፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት በሰላም፣ በመናገር ነፃነት፣ በሰብዓዊ መብትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ወሳኝ ለውጦች ታይተዋል፡፡ አሁን በግልጽ የተቀመጠው አቅጣጫ ሶማሌና ሁሉም ክልሎች በማዕከላዊው ሥልጣን ውስጥ ተሳታፊ መሆን እንደሚገባቸው ነው፡፡ ግን ሙሉ ለሙሉ ከማዕከላዊ ሥልጣን ጋር ለመዋሀድ፣ በፀጥታና በኢኮኖሚ ዘርፎችም በብሔራዊ ደረጃ መዋሀድ አለብን፡፡
ሪፖርተር፡- ወደ ሥልጣን ሲመጡ ለሁሉም ብሔሮች የምትመች የሶማሌ ክልል እንደሚፈጥሩ ተናግረው ነበር፡፡ ተሳክቷል ይላሉ?
አቶ ሙስጠፌ፡- እኔ ወደ ሥልጣን ስመጣ በሶማሌ ክልል ውስጥ ያሉ ሶማሌ ያልሆኑ ብሔሮች ላይ የፖለቲካ የሚመስል ጥቃት ነበር፡፡ አሁን ሁሉም ሰው በሶማሌ ክልል እኩል ነው፡፡ የሶማሌ ክልልን አካታች ዴሞክራሲያዊ ልምምድ በፌዴራል ደረጃም መተግበር አለብን፡፡
ሪፖርተር፡- ገዥው ፓርቲ የድጋፍ መሠረቱን እያጣ ነው የሚሉ ተንታኞች ስላሉ እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ ሙስጠፌ፡- የትኛው ጥናት ነው ይህን ያረጋገጠው? በእኔ አመለካከት ኢትዮጵያ ሁሌም በተቃርኖዎች መሀል ናት፡፡ ብልፅግና የድጋፍ መሠረቱን እያጣ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ይኼን ለማረጋጥ ግን ቀጣዩ ምርጫ አለ፣ እሱ ወሳኝ ነው፡፡ እስከዚያ ብዙ ንግግሮችና ትንተናዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ግን በሚዲያ ትንተና ላይ ብቻ ተንተርሰን ማጠቃለል አንችልም፡፡ በሱማሌ ክልል በተለይ ብልፅግና ትልልቅ ለውጦች በማምጣቱ ትልቅ ድጋፍ አለው፡፡ የብልፅግና ድጋፉ እያደገ ነው፡፡
ሪፖርተር፡– ደርግ የሠራተኛው መደብ ሳይፈጠር የሠራተኛው መደብ ተወካይ ነኝ አለ፡፡ ብልፅግናም ባለከፍተኛ ገቢ እርከን ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ሳይፈጠር የብልፅግና ማኅበረሰብ ተወካይ ነኝ ብሏል፡፡ የብልፅግና የድጋፍ መደብ የትኛው ማኅበረሰብ ነው?
አቶ ሙስጠፌ፡- የብልፅግና ደጋፊ መደብ ባለመካከለኛውና ባለከፍተኛው ገቢ ማኅበረሰብ ብቻ አይደለም፡፡ ከገበሬ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ባለሙያ ሁሉም የብልፅግና መሠረት ናቸው፡፡ የብልፅግና መሠረት ከኢሕአዴግም የተለየ ሲሆን፣ ዋና ሐሳቡም በአንድ አስተሳሰብ ብቻ ያለ መታጠር መርህ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ገዥው ፓርቲ የትጥቅ ትግል ከሚያደርጉ አካላት ጋር ተደራድሮ ሰላም ለማስፈን ፍላጎት የለውም ይባላል፡፡
አቶ ሙስጠፌ፡– በአገራችን ታሪክ መንግሥት ከታጠቁ አካላት ጋር ተደራድሮ መፍትሔ ያመጣበት የፕሪቶሪያው ስምምነት ነው፡፡ መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋርም ለመደራደር እስከ ታንዛኒያ ድረስ ሄዷል፡፡ መንግሥት ኤርትራ ውስጥ የነበሩ ተቃዋሚ ኃይሎች ወደ አገር ቤት በሰላም እንዲመለሱ አድርጓል፡፡ መንግሥት ለሰላማዊ መፍትሔና ድርድር ሁሌም ዝግጁ ነው፡፡
ሪፖርተር፡– የታጠቁ ኃይሎች በተለይ ገጠራማ አካባቢ ቦታዎችን እየተቆጣጠሩ ነው የሚሉ ሪፖርቶች አሉ፡፡
አቶ ሙስጠፌ፡- በአሁኑ ጊዜ ለፌዴራል መንግሥት ሥጋት የሚፈጥር የታጠቀ ኃይል የለም፡፡ እዚያም እዚህም ግጭቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ለመንግሥት ሥጋት አይደሉም ሲባል ጉዳት አያደርሱም ማለት አይደለም፡፡ እነዚህን ግጭቶች መፍታት የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ የሕግ የበላይነትን ማስከበርና ትክክለኛ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር መንግሥት እየሠራ ነው፡፡ ብሔራዊ የምክክር መድረኩ አንዱ ትልቅ ዕድል ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ መሆናቸውን ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡ መንግሥት ለምን ማስቆም አልቻለም?
አቶ ሙስጠፌ፡- በአገሪቱ ያለፉት የ50 ዓመታት ታሪክ ግጭት ያልነበረበት ጊዜ የለም፡፡ ዛሬ ማኅበራዊ ሚዲያው ግጭቶች የበለጠ ጎልተው እንዲታዩ ስላደረገ ብቻ ጥሰቶች በርክተዋል ማለት አይቻልም፡፡ ለምሳሌ በኢሕአዴግ ዘመን ሶማሌ ክልልን የሚያህል የአገሪቱ ሲሶ በግጭት ይታመስ ነበር፡፡ ማንም ግን ሶማሌ ክልል ገሃነም ሆኖ ነበር አይልም፡፡ ዛሬ ግን ማኅበራዊ ሚዲያው እያንዳንዷን ግጭት እያጎላ ነው፡፡ ግን እውነታው ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ከተፈጠሩት ግጭቶች የተለየ ነገር የለም፡፡ እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶችን ከዚህ ቀደም ያልነበሩ ዓይነት አድርጎ ማቅረብ ትክክል አይደለም፡፡ ግን ይኼ ማለት ለግጭቶቹ መፍትሔ ማፈላለግ አያስፈልግም ማለት አይደለም፡፡ ግጭት ጥሩ ነው እያልኩም አይደለም፡፡ ነገር ግን ንፅፅሩን ብቻ ለማሳየት እየሞከርኩ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- አንዳንዶች ሕገ መንግሥቱን መቀየር ኢትዮጵያ ላለችበት ችግር መፍትሔ ያመጣል ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ሕገ መንግሥቱን መንካት ችግሩን ያባብሳል ይላሉ፡፡ የእርስዎም አቋም ምንድነው?
አቶ ሙስጠፌ፡- የእኔ አቋም ከፓርቲዬ አቋም ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ሕገ መንግሥት መሻሻል አለበት፡፡ ምሁራን አዲስ ትውልድ በመጣ ቁጥር አዲስ ሕገ መንግሥት ማርቀቅ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ ብልፅግና ሕገ መንግሥት መሻሻል አለበት ብሎ ያምናል፡፡ ይህ ማለት ግን ቀደን እንጣለው ማለት አይደለም፡፡ በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ነባሩ ሕገ መንግሥት በጣም ጥሩ ነገሮች አሉት፡፡ ስለዚህ መሻሻል ያለበትን መለየት አለብን፡፡ ብሔራዊ የምክክር መድረኩ ለዚህ ጥሩ ዕድል ይፈጥራል፡፡ የማንስማማቸው ጉዳዮች ካሉም በሪፈረንደም መፍታት ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- ከሕገ መንግሥት ማሻሻል ዓውድ ውስጥ ብሔርተኝነትንና ብሔራዊነትን በተመለከተ የብልፅግና አቋም ምንድነው?
አቶ ሙስጠፌ፡- የብልፅግና አቋም መሀል መንገድ (Centrist) ነው፡፡ ብሔርተኝነትና ብሔራዊነት መመጣጠን አለባቸው፡፡ የግልና የቡድን መብቶች መመጣጠን አለባቸው፡፡ የብሔር መብቶች መከበር አለባቸው፡፡ ግን ደግሞ የጋራ ብሔራዊ ማንነትን መፍጠር ላይ መሥራት አለብን፡፡ ከዚህ ቀደም እንደነበረው አንድ ብሔር ብቻ የሚገንበት ሁኔታ መፈጠር የለበትም፡፡ የጋራ ትርክት ፈጥረን የብሔርና የሃይማኖት ልዩነቶችን ማጥበብ አለብን፡፡
ሪፖርተር፡- ወደ ብሔራዊ ምክክርና ሕገ መንግሥት ማሻሻል ከመሄድ በፊት ለተፈጠሩት ጥሰቶች ፍትሕ መሰጠት አለበት ይባላል፡፡ ያንን እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል?
አቶ ሙስጠፌ፡- የብዙ አገሮች የአገር ግንባታ ጥረት በግጭቶች ውስጥ ያለፈ ነው፡፡ ግን ላለፈው በደል ፍትሕ መንፈግ ስኬቱን ያስተጓጉላል፡፡ እኛም የጀመርነው የሽግግር ፍትሕ ለዚህ ጥሩ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን የተፈጸመውን በደል እንዳልተፈጸመ ማድረግ አይቻልም፡፡ ካለፈው ጠባሳ በመማር ላለመድገም መሥራት ግን ወሳኝ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የሽግግር ፍትሕ ከ2010 ዓ.ም.፣ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ ወይስ ከደርግ ጊዜ ነው መጀመር ያለበት?
አቶ ሙስጠፌ፡- እሱን ሕዝቡ ለሽግግር ፍትሕ ግብዓት ሲሰጥ የሚወስነው ይሆናል፡፡ ከዛሬ አንድ ሺሕ ዓመት፣ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን፣ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን፣ ከደርግ ወይም ከኢሕአዴግ ዘመን ይጀመር የሚሉም አሉ፡፡ በኢትዮጵያ የአገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ የተፈጠረውን ስህተት ለማረም መሄድ እስከቻልንበት ርቀት ድረስ ወደኋላ መሄድ መቻል አለብን፡፡ ግን ፍትሕን ለተጎጂዎች ከማረጋገጥ አንፃር በሕይወት ባሉት ላይ ማተኮር አለብን፡፡ የዛሬ 200 ዓመት ወይም 300 ዓመት ወንጀል የሠሩም የተሠራባቸውም ዛሬ በሕይወት የሉም፡፡ ስለዚህ ከሕግ አንፃር አሁን ባሉት ላይ መተኮር አለበት፡፡ ነገር ግን የሽግግር ፍትሕ ቡድኑ የሚበጀውን አካሄድ መርጦ እንደሚወስን እናምናለን፡፡
ሪፖርተር፡- እርስዎ ወደ ፌዴራል መንግሥት ሹመት አግኝተው ሊሄዱ ነው የሚሉ ወሬዎች አሉ፡፡
አቶ ሙስጠፌ፡- የግል ጉዳይ ስለሆነ እንለፈው፡፡
ሪፖርተር፡- ብዙ ነገሮች የተሳካልዎት የመሪነት ተሰጥኦ ስላለዎት ነው የሚሉ አሉ፡፡
አቶ ሙስጠፌ፡- መልስ የለኝም፣ እሱንም እንለፈው፡፡
ሪፖርተር፡- በሶማሌና በኦሮሚያ፣ እንዲሁም በሶማሌና በአፋር ወሰኖች ላይ በተደጋጋሚ ግጭቶች ይፈጠራሉ፡፡ ምክንያቱ ምንድነው?
አቶ ሙስጠፌ፡- ከኦሮሚያ ጋር ያለውን አብዛኛውን የድንበር ግጭት ፈተናል፡፡ ከሁለት ሺሕ ኪሎ ሜትር በላይ የጋራ ወሰን ስለምንጋራ ግጭት የሚጠበቅ ነው፡፡ አሁን በሶማሌና በኦሮሚያ ወሰንተኛ ሕዝቦች መካከል ሰላም ወርዷል፡፡ በሶማሌና በአፋር ወሰን መካከል ግን የቀጠሉ ችግሮች አሉ፡፡ በአፋር በኩል ከመሬቶቻቸው የተፈናቀሉ ብዙ ሶማሌዎች ስላሉ ወደ መሬታቸው መመለስ አለባቸው፡፡ ለመቶ ዓመታት የኖሩበት ቀዬአቸው መመለስ አለባቸው፡፡
ሪፖርተር፡- በሶማሌ ክልል ድርቅና ረሃብ በተደጋጋሚ ይከሰታል፡፡ የከርሰ ምድር ውኃን ለመጠቀም ለምን አልተሠራም?
አቶ ሙስጠፌ፡- በአየር ለውጥ ምክንያት ድርቅ እየበዛ ነው፡፡ የከርሰ ምድር ውኃን መጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን በነበሩት ግጭቶች ምክንያት በዚህ ልማት ላይ ማተኮር አልተቻለም ነበር፡፡ እስካሁን የገነባነው ድርቅን የመቋቋም አቅማችንን አዳብሯል፡፡ ለዚህም ነው በ100 ዓመታት ውስጥ ከባዱ የተባለው ድርቅ ቢያጋጥመንም ወደ ሰዎች ሞት ግን አላመራም፡፡ የከርሰ ምድር ውኃ በቂ ስላለን በቀጣይ እሱ ላይ መሥራት አለብን፡፡
ሪፖርተር፡- በሶማሌ ክልል የተገኘው የተፈጥሮ ጋዝ መቼ ወደ ምርት ይቀየራል?
አቶ ሙስጠፌ፡- በቂ መረጃ የለኝም፣ ግን የፌዴራል መንግሥት እየሠራበት ነው፡፡ መሠረተ ልማቱን ገንብቶ ወደ ምርት ለመግባትና በኢንዱስትሪ ደረጃ ለማምረት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋው ቢሳካም የአዋጭነት ጥናትና መሠረተ ልማት ግንባታን የመሰሉ ሥራዎች ይቀራሉ፡፡
ሪፖርተር፡- የሶማሌ ክልል ከፍተኛ የኮንትሮባንድ ዝውውር ማዕከል ነው፡፡ ችግሩን ለመፍታት ለምን አልተቻለም?
አቶ ሙስጠፌ፡- ኮንትሮባንድ ለረዥም ጊዜ የቆየ ችግር ነው፡፡ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ሆነን እየሠራን ነው፡፡ ሶማሌ ክልል ከጎረቤት አገር ጋር ከ1‚000 ኪሎ ሜትር በላይ ድንበር ይጋራል፡፡ ይኼን ሁሉ ድንበር መቆጣጠር ከባድ ነው፡፡ ኮንትሮባንድ መቆጣጠር የሚቻለው የየብስ፣ የአየርና የውኃ ትራንስፖርት መንገዶችን ዘግቶ በእያንዳንዱ ድንበር መግቢያ ላይ መቆጣጠሪያ ጣቢያ በማበጀት ነው፡፡ ይኼን ማድረግ ሳይቻል ኮንትሮባንድን መቆጣጠር አዳጋች ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርቡ የጫት ኤክስፖርት እየቀነሰ ሲሆን ክልሎች የሚጥሉት ቀረጥና የሶማሊያ መንግሥት ዕገዳዎች መንስዔ ናቸው ተብሏል፡፡ ትክክል ነው?
አቶ ሙስጠፌ፡- የጫት ወጪ ንግድ ቀንሷል፡፡ በፌዴራልና በክልል መንግሥታት መካከል ውይይቶች እየተደረጉ ነው፡፡ አላስፈላጊ ቀረጦችም ምርቱ ላይ እየተጣሉ ነው፡፡ ነገር ግን መፍትሔውን ለማወቅ መጀመርያ አጠቃላይ ምርመራ መካሄድ አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- በሶማሌ ክልል በሚዲያ ተቋማትና በጋዜጠኞች ላይ የክልሉ መንግሥት አላስፈላጊ ዕርምጃ እየወሰደ ነው የሚሉ ሪፖርቶች እየወጡ ነው፡፡ ለምንድነው ይኼ የሚደረገው?
አቶ ሙስጠፌ፡- የከለከልናቸው በሶማሌ ክልል ያልተመዘገቡትን ሚዲያዎች ነው፡፡ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ሄደው እንዲመዘገቡ ብንነግራቸውም ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ ከሚዲያ የተደበቀ የምንሠራው ሥራ የለንም፡፡ ሕጉን ተከትለው ከተመዘገቡ አሁንም መጥተው መሥራት ይችላሉ፡፡ በሐሳብ ብዝኃነትና በአተያይ ዙሪያ ሁልጊዜም ልዩነት አለ፡፡ ብዙ የሚዲያ ተቋማት በአገሪቱ ኖረው ሁሉም ግን አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ብቻ ሊያቀነቅኑ ይችላሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ሁለት ወይም ሦስት ሚዲያ ተቋማት ብቻ በአገሪቱ ኖረው ግን፣ ብዙ ዓይነት የአተያይ መንገዶችን ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ ከአተያይ አንፃር በሶማሌ ክልል የመናገር ነፃነት ሙሉ በሙሉ ተረጋግጧል፡፡ ጅግጅጋ ብትሄድ ቢቢሲ፣ ቪኦኤ፣ ማኅበራዊና ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ሁሉም አሉ፡፡ እንደሚታወቀው ማኅበራዊ ሚዲያው ዛሬ ዋናዎቹን የሚዲያ ተቋማት እየተካ ነው ያለው፡፡ በአጭሩ በእኛ በኩል የመናገር ነፃነትን የማፈን ፍላጎት የለንም፡፡ ግን ደግሞ ያልተመዘገቡ ሚዲያዎች እንዲሠሩ በመፍቀድ ቢጫ ጋዜጠኝነት (Yellow Journalism) እንዲፈጠር አንፈልግም፡፡ እንዲህ ዓይነት ሚዲያዎች የጎሳ ግጭቶችን በማጉላት አለመግባባት እንዲሰፍን ያደርጋሉ፡፡
ሪፖርተር፡- የሰሜኑ ጦርነት እንዳለቀ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓይብ አህመድ (ዶ/ር) የፀረ ሙስና ኮሚቴ በፌዴራልና ክልል ደረጃዎች ማቋቋማቸው ይታወሳል፡፡ ኮሚቴው ውጤታማ ሆኗል ማለት ይቻላል?
አቶ ሙስጠፌ፡- በጠቅላይ ሚኒስትር የተቋቋመው ፀረ ሙስና ኮሚቴ ብዙ ሥራ ሠርቶ ውጤታማ ሆኗል፡፡ ብዙ ነገሮችም እየተሠሩ ነው፡፡ የሕዝቡን ሞራል መገንባትና ተቋማትን መገንባት ወሳኝ ነው፡፡ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነትም ሙስናን ለመዋጋት አስፈላጊ ነው፡፡
Source: https://www.ethiopianreporter.com/