ምክክር ተብየው
News

ከአብይ የምክክር ተብዬው ብዛት ያላቸው ተሳታፊዎች በተቃውሞ ራሳቸውን እያገለሉ በመውጣት ላይ መሆናቸው ተጋለጠ

ከምክክሩ ራሳቸውን ያገለሉት ተሳታፊዎች ያነሷቸው ቅሬታዎች

1ኛ) በሂደቱ ውስጥ በተደራጀ እና ስልታዊ በሆነ መንገድ የተፈጸሙ መዋቅራዊ ግድፈቶች የምክክር ሂደቱን ፍፁም አግላይ፣ ፍትሃዊነት የጎደላቸው እና አስቀድሞ የተወሰነን የገዢው ፓርቲ የፖለቲካ ፍላጎት ለማጽደቅ የተዘረጋ የይስሙላ መድረክ እንዳደረጉት አስተውለናል።

2ኛ) በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 አንቀጽ 14 እና በአለም አቀፍ የኮንሰንሰስ ምክክር መመሪያዎች የተደነገጉትን የአካታችነት (Inclusivity)፣ የገለልተኝነት (Neutrality) እና የጋራ መግባባት (Consensus-building) መርሆዎች በጽኑ የሚጥሱ መዋቅራዊ ክፍተቶች እንዳሉ በጥናት አረጋግጠናል። እነዚህን መዋቅራዊ ችግሮች አስመልክቶ የሰጠነው የቅድመ-ሁኔታ ማስተካከያ ጥያቄ እና የአስቸኳይ ስብሰባ ጥሪ በጽሁፍ ለኮሚሽኑ እና ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የገባ ቢሆንም፣ አስገዳጅ ማስተካከያ ሳይደረግበት ሂደቱ ወደ ውሳኔ አሰጣጥ ተጣድፏል።

3ኛ) ሂደት የህግ የበላይነትን እና ፍትሃዊነትን ያጣ በመሆኑ፣ እንዲሁም ለመጪው ትውልድ ህልውና ታሪካዊ ስብራት እንዳያመጣ ስጋት ፈጥሮብናል።

4ኛ) የገዢው ፓርቲ መዋቅራዊ ጠለፋ እንዳለም ተመለክተናል። መንግሥት እና ገዢው ፓርቲ በተለያዩ ስሞች እና ታክቲካዊ ሽፋኖች (በፌዴራል፣ በክልል፣ በከተማ አስተዳደሮች፣ በልዩ ልዩ የፍላጎት ቡድኖች፣ እንዲሁም በባህልና እምነት ተቋማት ስም) አብላጫ ተሳታፊ በመመደብ ሂደቱን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር እና አስቀድሞ የወሰናቸውን አጀንዳዎች ለማጽደቅ መድረኩን ጠልፈውታል።

5ኛ) የአማራን ሕዝብ እውነተኛ ውክልና ማደብዘዝ እና ስልታዊ ማግለል ተፈፅሟል። በመንግሥት መዋቅራዊ ተጽዕኖ አማካኝነት ከአማራ ክልል ስም የአማራን ሕዝብ ጥቅም የማይወክሉ እና ይልቁንም ከአማራ ሕዝብ ህልውና በተቃራኒ የተቀረጹ አናሳ ስብስቦችን በማብዛት፣ ሕዝባችንን በግንባር ቀደምትነት የሚወክሉ የፖለቲካ ኃይሎችን እና ሰፊውን የአማራ ድምፅ ወደ አናሳነት ለማውረድ በጥናት የተሰራ ሴራ ተተግብሯል። በተጨማሪም ከአማራ ክልል ውጭ የሚኖሩ ሚሊዮኖች ድምፅ አልባ እንዲሆኑ ተደርጓል።

6ኛ) የኤክስፐርቶችና የአወያዮች የሙያ፣ የአቅም እና የገለልተኝነት ክፍተትን አስተውለናል። በኮሚሽኑ የተመደቡ በርካታ ኤክስፐርቶችና አወያዮች የሀገሪቱን ውስብስብ ፖለቲካ በሙያዊ ብቃት የመተንተን አቅም የሌላቸው ከመሆኑም በላይ፣ በግልጽ ከገዢው ፓርቲና ከስልጣን መስመር ጋር ያደሉ፣ የገዢውን ፓርቲ ርዕዮተ-ዓለም የሚያንጸባርቁና የተለየ ሀሳብ ያላቸውን ተሳታፊዎች የሚያዳፍኑ ሆነው አግኝተናቸዋል።

7ኛ) የኮሚሽኑን ቀናነት ለሥልጣን ማጋበሻ ሆኗል ብለን እናምናለን። ሂደቱ የሀገር ችግር የሚፈታበት ከመሆን ይልቅ፣ የተወሰኑ የፖለቲካ ስብስቦች እና ገዢው ፓርቲ የኮሚሽኑን ግልጽነት እንደ ምቹ አጋጣሚ በመውሰድ የራሳቸውን ጠባብ ፍላጎት የሚያስፈጽሙበት፣ አጀንዳ የሚያሳኩበት እና የፖለቲካ ስልጣን ማጋበሻ መድረክ አድርገውታል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰናል።

8ኛ) የደህንነት አካላት ጣልቃ ገብነትና ነፃ ሀሳብን ማሸማቀቅ ተስተውሏል። በምክክር አዳራሾች ውስጥ የደህንነት እና የጸጥታ አካላትን እንደ ተሳታፊ በማስገባት፣ ተሳታፊዎች ያለምንም ፍርሃት የመሰላቸውን ሀሳብ በነጻነት እንዳያንሸራሽሩ የኃይልና የመሸማቀቅ መንፈስ እንዲነግስ ተደርጓል።

9ኛ),አጀንዳዎችን በጥላቻ እና በአድልዎ መቅረጽ ሂደቶችን ተመልክተናል። የውይይት አጀንዳዎች የተቀረጹበት መንገድ መሪ ጥያቄዎችን በመጠቀም፣ አማራውን የችግሮች ሁሉ ምንጭ አድርጎ ለመሳል እና ሌሎች ብሔረሰቦች በአማራው ላይ ቅሬታ እና ጥላቻ እንዲሰነዝሩ በሚያባብስ መልኩ የተነደፈ እንደሆነ በሂደቱ አስተውለናል።

10ኛ) የተደራጀ የሀሳብ ማስተጓጎል እና ማሸማቀቅ ተግባራት ተፈፅመውብናል። መብታቸውን፣ ማንነታቸውን እና ፍትሃዊ አቋማቸውን ለማንሳት የሚሞክሩ የአማራ ተወካዮች በተደራጀ መልኩ ጩኸት እንዲበዛባቸው፣ እንዲረበሹ እና ሀሳባቸውን ሳይጨርሱ እንዲቀጩ ይደረጋል።

11ኛ) ሀገራዊ ትርክቶችን ማጣመም ተግባራት ሆን ተብለው እየተፈፀሙ ነው። አገር ካለችበት ቀውስ የሚያወጡ ሁለንተናዊ እሴቶች (እንደ ዜግነት መብት) በሚነሱበት ወቅት፣ ሀሳቡን የሚያነሱ አካላትን በጅምላ “አሃዳዊና ጨቋኝ” በማለት የመፈረጅ እና በህዝቦች መካከል ጥላቻን የመዝራት አካሄድ ተስፋፍቷል።

12ኛ) ተመካክሮና ተከራክሮ ከመግባባት (Consensus) ይልቅ ወደ እጅ ብልጫ (Voting) መጣደፍ ተመልክተናል። ሀገራዊ ምክክር ማለት በምክንያት የሚደራደሩበት ሂደት እንጂ በድምፅ ብዛት የሚወሰንበት አይደለም። አጀንዳዎች በቂ ውይይት ሳይደረግባቸው፣ ገዢው ፓርቲ ባለው የውክልና ብልጫ በመጠቀም ሂደቱን በድምፅ አሰጣጥ ለማጽደቅ መጣደፉ የምክክሩን መሰረታዊ መንፈስ ያፈረሰ እንደሆነ እናምናለን።
በአጠቃላይ!

በበርካታ መዋቅራዊ ጥሰቶችና የፖለቲካ ሴራዎች ምክንያት፣ ሀገራዊ ምክክሩ ህጋዊ ቅቡልነቱን (Legitimacy) እያጣ ነው። በይስሙላ መድረክ ላይ ተሳስፎ ለገዢው ፓርቲ ውሳኔዎች ህጋዊነት መስጠት ለህዝብም ሆነ ለሀገር ህልውና የሚተርፍ ታሪካዊ ስብራት እንደሆነ እንገነዘባለን።
በእነዚህ ሂደቶች ምክንያት የገዢውን ፓርቲ ፍላጎት ህጋዊ ለማድረግ የተዘጋጀ የፖለቲካ ድራማ እንጅ ተሳታፊም ሆነ ህዝብ ውጤቱን ይቀበላል ብለን አናምንም። በዚህ መንገድ የሚተላለፍ ማንኛውም ውሳኔ በህዝብና በነፃ የፖለቲካ ኃይሎች ዘንድ ተቀባይነት እንደማይኖረው እና ሀገራዊ ሰላምን እንደማያመጣ ግልፅ ነው።

ምንጭ፡ ጌታቸው ሽፈራው ፌስቡክ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *