Press Release

በመንግስት የፀጥታ ሃይሎች ከየቤታቸው ተይዘው ከተወሰዱ በኋላ ደብዛቸው የጠፉ የአዲስ አበባ ወጣቶች አድራሻና ደህንነት አሳስቦናል።

*ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ – ኢሕአፓ የተሰጠ መግለጫ*

በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ኢትዮጵያ ዜጎች በህግ ጥላ ስር የመጠበቅ መብታቸው ተጥሶ፣ ከየቤታቸው በፀጥታ አካላት ከተወሰዱ በኋላ ያሉበት ሳይታወቅ ደብዛቸው የመጥፋቱ አሳሳቢ ክስተት ቀጥሏል።

በተለይም ከአንድ አመት በፊት ከአዲስ አበባ ከተማ ተይዘው የተወሰዱ ወጣቶች እስካሁን ድረስ ያሉበት አድራሻና የደህንነት ሁኔታ አለመታወቁ ፓርቲያችንን እና መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ እጅግ አሳስቧል።

ከአንድ አመት በፊት በመንግስት የፀጥታ አካላት፣ ሰብዓዊ ክብርንና ህግን በሚጥስ መልኩ ከየቤታቸው ተይዘው ከተወሰዱት ውስጥ ገነት አራጌ፣ ሰብስቤ አለሙ፣ ሱራፌል፣ አማኑኤል እና ሌሎች በርካታ ወጣቶች ያሉበት ሁኔታ እስካሁን ድረስ ለቤተሰቦቻቸውም ሆነ ለህዝብ ግልፅ አይደለም።

ፓርቲያችን ኢሕአፓ፣ ዜጎች በወንጀል ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር የመዋል ሂደትን በራሱ አይቃወምም። ነገር ግን ማንኛውም በወንጀል የተጠረጠረ ዜጋ ከአያያዙ ጀምሮ፣ ምርመራ በሚደረግበት ወቅት ሰብዓዊ ክብሩና ደህንነቱ የመጠበቅ መብት እንዳለው በፅኑ ያምናል። ይህ መብት በሀገሪቱ ህግም በግልፅ ተደንግጓል።

ሆኖም ግን በብልፅግና አስተዳደር ስር እነዚህን መሰረታዊ መብቶች እንዲከበሩ መጠየቅ እንደ ቅንጦት መቆጠር ከጀመረ አመታት አልፈዋል፡፡

ዜጎችን አፍኖ ወስዶ፣ ለፍትሕ ተቋማት ሳያቀርቡ ከአመት በላይ ደብዛቸውን ማጥፋት ግልፅ ወንጀልና የህግ ልዕልናን መናቅ ነው።

ይህ ድርጊት ቤተሰቦቻቸውን ብቻ ሳይሆን ህግና ስርአት እንዲከበር የሚሻውን ዜጋ ሁሉ በእጅጉ የሚያስቆጣ ኢ-ሰብዓዊ ተግባርም ነው።

በመሆኑም፡

1. ደብዛቸው ከጠፋ አመት ያለፋቸው እነዚህ ዜጎች ያሉበት አድራሻና አጠቃላይ የደህንነት ሁኔታቸውን መንግስት በአስቸኳይ ለሕዝብና ለቤተሰቦቻቸው እንዲያሳውቅ፤

2. የታገቱት ወጣቶች የተጠረጠሩበት ጉዳይ ካለ፣ ጉዳያቸው በአስቸኳይ ተጣርቶ ወደ መደበኛ የፍትሕ ተቋማት እንዲቀርቡ፤

3. በማንነታቸው እና በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት በየእስር ቤቱ ታስረው የሚገኙ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የማህበረሰብ አንቂዎችና በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሀን ዜጎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ፤

4. መንግስት ዜጎችን በማንነታቸው እና በፖለቲካ አመለካከታቸው ለይቶ ማሳደዱን፣ ማፈኑን እና ማሰሩን እንዲሁም መሰል የመብት ጥሰቶችን መፈጸሙን እንዲያቆም ኢሕአፓ በጥብቅ ያሳስባል።

በመጨረሻም የኢትዮጵያ ሕዝብ የወጣቶቹ ደህንነት ታውቆ ፍትህ እስኪያገኙ ድረስ፣ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ድምፁን በአንድነት እንዲያሰማ ኢሕአፓ አበክሮ ይጠይቃል።

የዜጎችን ሰብአዊ መብት መጣስ ይብቃ!

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ  (ኢሕአፓ)

የካቲት 09 ቀን 2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *