EPRP Logo
Press Release

አስቻይ ሁኔታዎች ያልተሟሉለት ምርጫ አምባገነንነተን እንጂ ዲሞክራሲን አያዋልድም!!!

EPRP

አስቻይ ሁኔታዎች ያልተሟሉለት ምርጫ አምባገነንነተን እንጂ ዲሞክራሲን አያዋልድም!!!

*ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ – ኢሕአፓ የተሰጠ መግለጫ*

ኢሕአፓ የመንግስት ስልጣን ሽግግር በኢትዮጵያ ሕዝብ ፈቃድና ይሁንታ፣ማለትም ሕዝቡ በነፃነት በሚያደርገው፣ ርትዓዊ፣ ተዓማኒነት ባለው ምርጫ መምጣት አለበት ብሎ በጽኑ ያምናል፡፡ ነገር ግን ምርጫ ሊካሄድ የሚያስችል ሁኔታ ደብዛው በጠፋበትና አሁን ብልጽግና የራሱን የሥልጣን-ዕድሜ ለማራዘምያስችለኛል በሚል፣ ዜጎችን አፍኖ፣ አስገድዶ፣ አደናግሮ፣ለማካሄድየሚሯሯጥለትስመ-ምርጫ የማወናበጃ ትርዒት እንጂ በፍጹም ሀገራዊ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሊሆን አይችልም፡፡ ምርጫ በአንድ ጀምበር ድምጽንበመስጠትና የድምጽ ቆጠራውን በማካሄድ ይጠናቀቅ እንጂበርካታ ጉዳዮችንያቀፈ አንድ ትልቅ ዴሞክራሲያዊ ሂደት ነው፡፡ በዋነኛነት በሁለትየምርጫ ወቅቶች መሐልበአንድ ሀገር ውስጥ ያሉትን የሠለምና መረጋጋት መኖርን፣ ዜጎች ሃሳባቸውን በነፃነት ሊገልጡ የሚችሉበት ሁኔታ መኖርን፣ የፖለቲካ ሃይሎችም አማራጭ ሃሳቦችን ለመራጩ ህዝብ ሊያቀርቡ የሚችሉበት ሠፊ የፖለቲካ ምህዳር መኖርን፣ ምርጫን የሚያደራጀውና የሚመራው አካልም ነፃነትና ኖሮትና ተዓማኒንትም አግኝቶ የሚሠራበት ሁኔታ መኖርን፣ በጥቅሉ አስቻይ ሁኔታዎችመኖርን ያቀፈ ሂደት ጉዳይ ነው፡፡
ዛሬ ላይ ቆመን ስለምርጫ ከመነጋገራችን በፊት ስለ አሁናዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ በጥሞና ልንነጋገር ግድ ይለናል፡፡ ኢሕአፓ ከዚህ ቀደምበተለያዩወቅቶች በሀገራችን ውስጥ የለበጣ ሳይሆን ትክክለኛ ምርጫ ሊካሄድ ይችል ዘንድ፣ ከምርጫ በፊት እንዲሟሉ የጠየቃቸው አግባብ ያላቸው ቅድመ ሁኔታዎች ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለገዥዎችም በግልጽ የሚታወቁ ናቸው።እነዚህ ሁኔታዎች ቢሟሉ ኖሮ ኢሕአፓ ዐይኑን ሳያሽ በምርጫውተሳትፎ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከቀጣይ መከራና ዕልቂት ለመታደግ ኢትዮጵያንም ከተደቀነባት የመፍረስ አደጋ ለማዳን የበኩሉን አስተዋጽዖ ያበረክታል ሙሉ ዝግጅትም አድርጎ ነበር። ነገር ግን ገዥው ብልጽግና ፍላጎቱ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ ሳይሆን ዛሬም ከቻለ አታሎ፣ አጭበርብሮና ሸውዶ፣ አለዚያም አፍኖና ጨፍልቆ “ተመርጫለሁ ዕወቁልኝ” ለማለት ነው።

የብልፅግና መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ ባሉት ስምንት አመታት የእርስ በእርስ ጦርነቶችን በማቀጣጠል፣ ማንነት ተኮር እስር እና ግድያዎች፣ የዜጎች በፍረጃ መፈናቀልና ስደት፣ የተፈናቀሉትም በየማጎሪያዎች በርካቶች በችጋርና ረሃብ መቆላት፣ የሚሊዮኖችበድህነት አረቋ መዋጥና የኢትዮጵያ መልኮች ሆነዋል፡፡ ሰራተኞች በልቶ ማደር ቅንጦት ሆኖባቸዋል፡፡ ህጻናት ያለ ሃጢያታቸው ከትምህርት ገበታ መፈናቀላቸው ሳያንስ በጦርነት ወላጅ አልባ ሆነዋል፤ እነርሱም በረሃብ እና በመሳሪያ እየተደገሉ ነው፡፡ ዜጎች መርጠው ባልተወለዱበት ማንነት፤ መርጠው በተከተሉት ሀይማኖትም ተሳድደው እየተጨፈጨፉ ነው፡፡

ፓርቲያችን ኢሕአፓ በ7ኛው አገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ ወደ ሂደቱ ሲገባ ዕውነተኛ ምርጫ እንዲሆን መሟላት ያለባቸውን ቅድመሁኔታዎች አስቀምጦ ነበር። እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች የማይሟሉ ከሆነ በማንኛውም ጊዜ ተገቢ ነው ብሎ የሚያምንበትን ፖለቲካዊ እርምጃ እንደሚወስድ እና ሠላማዊ የፖለቲካ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡
ዛሬም እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ባልተሟሉበት ሁኔታ ገዥው ሃይልየምርጫ ስርኣቱን ተጠቅሞ የራሱን እድሜ ለማራዘም አጃቢዎቹን ሰብስቦ በምርጫ ስምትርዒት ከማሳየት ባለፈ አንዳችም ኢትዮጵያ ውስጥ የዴሞክራሲ ሥር ዓትን የሚያጎለብት አንዳችም ጠቀሜታ እንደማይኖረው እናምናለን። በተቃራኒው አሁን ያለው የአፈና ስርዓት የሚያስቀጥል እንደሚሆን እናምናለን፡፡

1. ብልጽግና ንጹሃን ዜጎችን በድሮን እና በከባድ መሳሪያ መግደሉን አቁሞ ለፖለቲካዊ ጥያቄዎች ፖለቲካዊ ምላሽ ባልሰጠበት እና ከእጃችሁን ስጡኝ ያለፈ ገለልተኛ እና ሁሉም ባለድርሻ አካላትና ኃይሎች የሚሳተፉበት አስተማማኝ ድርድር ለማካሄድ ፍቃደኛ ባልሆነበት
2. በማንነታቸው፣ በፖለቲካ አመለካከታቸው እና በሙያቸው ምክንያት የታሰሩ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ ንጹሃን ዜጎች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ከግፍ እስራት እንዲለቀቁ ቢጠየቅም ገዥው ሃይል ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ በስር እያማቀቃቸው ባለበት
3. የሚዲያ እና የዴሞክራሲ ተቋማትለሙያ እና ለእውነት መታመን ተግባራቸው ሊሆን ሲገባ በተቃራኒው በመንግሥት ጫና ውስጥ ገብተው የአንድ አካል አወዳሾችበሆኑበት፣ ምንም ገለልተኛ ሜዲያ እንዲኖር ባልተደረገበት
4. ዓለም ዓቀፍ ታዛቢዎች በሌሉበትና መንግሥታትም የሀገሪቱን ሁኔታዎች በአስጊነታቸው እያማረሩ ባሉበት፣
5. ብልጽግና በሰላማዊ መንገድ እየታገሉ ያሉ ሃቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና ግለሰቦች ላይ እያደረሰ ያለው ጫና ከዕለት ወደ ዕለት በጨመረበት ሁኔታ፣ ሰፋ ባሉ የሀገራችን ክፍሎች የሚኖሩት ዜጎች በጦርነቶች እየተቸፈጨፉና እየተዋከቡም ባሉበት የሚካሄድ ምርጫ በየትኛውም አይነት መመዘኛ ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃ፣ ፍትሃዊ እና ተ ዓማኒነት የሚኖረው ሊሆን አይችልም፡፡

በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚካሄድ ምርጫ ለስርኣቱ ንጹሃንን በጅምላ መግደልህን፣ ማሰደድህንና ማሳደድህን፣ ዜጎችን በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት በግፍ ማሰርህን ቀጥል ብሎ መፍቀድናየህዝቡንም ስቃይ ከማስቀጠል የዘለለ ትርጉም አይኖረውም፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ በሰራዊት ታጅቦ ምርጫ ለማድረግ መታቀዱም ብልጽግና ለቀጣይ አምስት አመታት በሃይል በስልጣን ላይ ለመቆየት ያለውን ፍላጎት የሚያስረግጥ ነው፡፡

የትግራይ ሕዝብ ለሁለተኛ ጊዜ የማይወከልበት፣ የአማራ ሕዝብ ብልጽግና በጀመረው ጦርነት ወላፈን እየተገረፈበሚገኝበት እና የማይወከልበት፣ በኦሮሚያ ክልል ውስጥም በርካታ አካባቢዎች ለአመታት በጦርነት እየተማገዱ ባሉበት እናፖለቲካዊ መፍትሔባልተቀመጠበት የሚካሄድ ምርጫ ትርጉሙ እጅግ አደገኛ እና የአገር አንድነት ከመሰረቱ እንዲናጋ የሚያደርግ ነው እንላለን፡፡
በመሆኑም የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ – ኢሕአፓ ምንም እንኳን የፖለቲካ ስልጣን ዝውውር በምርጫ መምጣት አለበት ብሎ ቢያምንም ከፍ ብለን በጠጠቀሳስናቸው ምክንያቶች፣ በተለይም ኢሕአፓ በምርጫ ለመሳተፍ ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ ዴሞክራሲያዊ፣ ነጻና ፍትሃዊ እንዲሁም ተዓማኒነት የሚኖረው ምርጫ ለማድረግ በዛሬቱ ኢትዮጵያ ውስጥ አስቻይ ሁኔታ አለ ብሎ አያምንም፡፡ የተጠቀሱት አስቻይ ሁኔታዎች ተሟልተው ፍትሃዊ ምርጫ እንዲደረግ ያለንን ፍላጎት እየገለጽን ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ሁሉ ይህንን ለማሳካት ከጎናችን እዲቆም ጥሪ እናቀርባለን፡፡
በመሆኑም የንጹሃንን ጭፍጨፋ እንዲቆም፣ የኑሮ ውድነቱን የዜጎችን ህይወት እያመሰቃቀለ ስለሆነ በአስቸኳይ ርምጃዎች እንዲገታ፣ የንጹሃን ዜጎችን እስር፣ ማንነት ተኮር እስሮች፣ ወከባዎችና ግድያዎች እንዲቆሙ፣ የዜጎች መፈናቀል፣ ከመኖሪቸው መፈናቀና መባረር እንዲቆም፣ ሙስና ድላዊነትና አግላይነት እንዲወገዱ፣ አምባገነንነት ከሕዝቡ ትከሻ ለማስወገድ የሚሻኢትዮጵያዊ በሙሉ ኢሕአፓ አርብ ሚያዚያ 30 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ፣ መቐለ፣ ባህርዳር፣ ጎንደር፣ ሀዋሳ፣ አዳማ እና አምቦ ከተሞች በጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ተገኝቶ በታላቅ መከራ ውስጥ እያለፈ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጎን እንደሚቆም በተግባር እንዲያሳይ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

ብልጽግና ንጹሃንን መግደል እና ማሳደዱን በአስቸኳይ ያቁም!
ሁሉን አቀፍ ሃቀኛ ድርድር ይደረግ!
የፖለቲካ እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ ይፈቱ!

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ – ኢሕአፓ
መጋቢት 30 ቀን 2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *