ቆንጅት ብርሃን
Politics

ኢህአፓ የራሱ አማራጭ የፌዴራሊዝም ሥርዓት አደረጃጀት አለው

ወይዘሮ ቆንጅት ብርሃን – የኢህአፓ ከፍተኛ አመራርና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል
July 5, 2019

በአሁኑ ጊዜ የኢህአፓ አመራር ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ የፓርቲው የማዕከላዊ ኮሚቴም አባል ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ በኢኮኖሚክስ ያገኙት ወይዘሮ ቆንጅት ብርሃን መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ባለሙያና ኃላፊ በመሆን ጭምር አገራቸውን አገልግለዋል፡፡
ከሰሩባቸው ድርጅቶች መካከል መንግሥት እርሻ ልማት ሚኒስቴር፣ ባህልና ስፖርት ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ፕሮፕራይድና ፋሚሊ ሂልዝ ኢንተርናሽናል ይገኙበታል፡፡ እንዲሁም የቦርድ አባልና አማካሪ በመሆንም በተለያዩ ድርጅቶች አገልግለዋል፡፡
በኢህአፓ ላይ ያተኮሩ ምርኮኛና ያላረፉ ድምጾች በሚል ርዕስ ሁለት መጽሐፍ ፅፈዋል፡፡ ከእኝህ ሴት ፖለቲከኛ ጋር በፓርቲያቸው እንቅስቃሴ፣ በአገራዊ ለውጡ ስጋትና ተስፋዎች ዙሪያ ቃለ ምልልስ አድርገናል፡፡ እንሆ፡-
አዲስ ዘመን፡–የፖለቲካ ተሳትፎዎ መቼ ጀመረ?
ወይዘሮ ቆንጅት፡– ከወጣትነት ዘመኔ ጀምሮ የኢህአፓ የወጣት ሊግ አባል ነበርኩ፡፡ በዚህ ምክንያት በደርግ ሥርዓት እስራትና ግርፋት ደርሶብኛል፡ ፡ በ1971 ዓ.ም ከእስር ከወጣሁ በኋላ ኢህአፓ የገጠሩ ትግል እንደቀጠለ ወሬዎች ቢሰሙም አዲስ አበባ ባለመኖሩ ወደ ግል ሕይወቴ ገባሁ፡፡ ሆኖም ኢህአፓ የሚንቀሳቀስ መሆኑን በትክክል ያወኩት በ2003 ዓ.ም ነው፡፡
በተለይ ምርኮኛን መጽሐፍ በጻፍኩ ጊዜ በአሜሪካ የሚገኙ የኢህአፓ አባላት አሜሪካ መጽሐፉን እንዳስመርቅ ጋበዙኝ፡፡ ኢህአፓ እየተቀሳቀሰ መሆኑን ያረጋገጥኩት ያን ጊዜ ነው:: ያኔም ቢሆን በግለሰብ እንጂ በድርጅት ደረጃ አላወኩትም፡፡ ግለሰቦቹን በሙሉ ግን አሜሪካ አግኝቻቸዋለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ኢህአፓን እንደ ድርጅት የተገናኘሁት ባለፈው ዓመት ዳላስ ላይ በተደረገው የስፖርት ውድድር ላይ ነው:: የቀድሞው ኢህአፓ ለሁለት ተከፍሏል፡፡ አንደኛው ኢህአፓ እኔ ያገኘሁት ሲሆን ሌላው ኢህአፓ አለ፡፡
እንደ ድርጅት ያገኘሁት እኔ አሁን አመራር የሆንኩበትን ኢህአፓ ነው፡፡ ስምንተኛው ጉባኤ ሲካሄድ እኔም እንደ እንግዳ ተገኝቼ ነበር፡፡ ከኢህአፓ ጋር እንደ ድርጅት መስራት የጀመርኩት እና አባል የሆንኩት ከዚህ በኋላ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አመራሮች መኖር ስላለባቸው ጥያቄውን ተቀብዬ አመራር አካሉ አባል ለመሆን በቃሁት፡፡ እንደ ግለሰብ ግን የእዚያንም ሆነ የእነዚህን ቡድን አባላት አውቃቸዋለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡–ፖለቲከኛ መሆን ሲመች የሚሳተፉበትሳይመች ትተውት የሚወጡት ነው?
ወይዘሮ ቆንጅት፡- እኔ የማስበው ሳይመቸኝ ከፖለቲካ ወጣሁ፤ ሲመቸኝ ደግሞ ፖለቲካ ገባሁ ብዬ አይደለም፡፡ ከ1971ዓ.ም እስከ ደርግ ውድቀት ድረስ የነበርነው ትኩስ የሥነ ልቦና ቀውስ ውስጥ ነበርን፡ ፡ በኃይል ሚዛን ተጨፍልቀን ዓላማችንና ሀሳባችን ብቻ ሳይሆን ጉልበታችንም የተዳፈነበት ጊዜ ነበር፡ ፡
ኢህአዴግ ከገባም በኋላ የምችለው መጻፍ ነበር፡ ፡ ስለዚህ ምርኮኛ የሚል መጽሐፍ አሳትሜያለሁ፡ ፡ ሌላም መጽሐፍም እንዲሁ ጸፌያለሁ፡፡ ፖለቲካ ውስጥ እንድትገባ የሚያደርግህ ዕድል አልነበረም፡፡ የተደራጀ ኃይል ስሌለ ምንም ለውጥ አልመጣም፡ ፡ የኢህአዴግ ተለጣፊ መሆን ደግሞ አልፈልግም፡፡
ከኢህአፓ ጋር ደግሞ ወደ ውጭ ያልሄድኩት ኢምፔሪያሊዝም ስቃወም የነበርኩ ወጣት ነኝ:: አሜሪካ መሄድ ለእኔ አማራጭ አይደለም፡፡ ነገር ግን ዓላማዬን ላለመተው የምችለውን ሁሉ ጥሬያለሁ፡ ፡ እውነት ለመናገር የሄዱትም ሰዎች ምርጫ ስለሌላቸው እንጂ የሄዱት ትክክለኛ አማራጭ ነው ብለው አምነውበት አይደለም፡፡
አሁን ለውጡ ሲመጣ ወደ ድርጅቱ የተቀላቀልኩት ይህን ዕድል ልጠቀም ብዬ ነው፡፡ ስለዚህ ስላልተመቸኝ አልተውኩትም፤ ስለተመቸኝ አልገባሁም፡፡ ተመልሼ ፖለቲካ ውስጥ የገባሁት በማይመች ሁኔታ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡– ኢህአፓ ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ የነበረውቢሆንም በሰራቸው ስህተቶች ውጤታማ ያልሆነ ድርጅትእንደሆነ ይጠቀሳል፡ ፡ አሁን ኢህአፓ ከስተቱ ተምሯልማለት ይቻላል?
ወይዘሮ ቆንጅት፡– ብዙ ስህተቶችን ስርቷል ለማለት ጥናት ይፈልጋል፡፡ እነዚህ ስህተቶች ከምንድነው የመነጩት የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ስህተት ሰርቷል የሚለው ውሳኔ በጥናት ላይ የተመረኮዘ ቢሆን ደስ ይለኛል:: ይህን ያልኩህ ግን ኢህአፓ ስህተት አልሰራም ብዬ ልክራከር ፈልጌ አይደለም፡፡ ሆኖም ባልተሰራ ጥናት ላይና በአፋዊ ትርክት ላይ ተመስርተን ስህተተኛ ድርጅት ነበር የሚለው ነገር እየተለመደ መጥቷል፡፡ ይህ መታረም አለበት፡፡ ግን እንደ ማንኛውም ድርጅት ሁሉ ኢህአፓ ስህተቶች ይሰራል፤ ሰርቷልም፡፡
ላለፉት ብዙ ዓመታት እኔ ከኢህአፓ ጋር አልነበርኩም፡፡ አሁን ኢህአፓን ከተቀላቀልኩ በኋላ ደግሞ ሙሉ ጊዜዬን የማውለው ኢህአፓ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕጋዊ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ እየሰራሁ ነው፡ ፡ እናም ያለፈ ነገሩን የመዳሰስ ዕድል አላገኘሁም፡፡ ነገር ግን እኔም ከባለፍ ገደም ከተወያየሁባቸው ነገሮች ብዙዎቹ ስህተቱ ውስጣዊ ናቸው፡፡
ኢህአፓ ዋና ዓላማው ላይ ችግር የለበትም፡፡ ዓላማው ኢትዮጵያና ሕዝቧን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማሻገር ነው፡ ፡ ይህን ዓላማውን ለማራመድና ለማሳካት ከመጡ ተቃራኒ ኃይሎች ጋር ሁሉ ታግሏል፡፡
በተለይ በአንኳርነት የታገለው ደርግና በደርግ ዙሪያ ከነበሩ ድርጅቶችና ከወያኔ ጋር ነው:: የ1966 ዓ.ም አብዮትን ሕዝቡ ያመጣው ቢሆንም የተደራጀ ኃይል ባለመኖሩ አብዮቱ ግቡን መትቶ ሕዝቡ የሚፈልገውን አላገኘም፡፡
ምክንያቱም ኢህአፓና መኢሶን በ1964 ዓ.ም ቢመሰረቱም እነዚህ ድርጅቶች ጎልብተው ትግሉን መምራት ያልቻሉበት ሂደት ነበር፡፡ ስለዚህ የደርግ ወታደራዊ መንግሥት በአቋራጭ ተጠቅሞ ሥልጣን ላይ ወጣ፡፡ ሕዝቡ የሚፈልገው የትግል ውጤት ባይሆንም ክፍተቱን ተጠቅሞ ሥልጣን ያዘ፡፡
ስለዚህ አብዮቱ የፈነዳው ኢህአፓ በተመሰረተ ከሁለት ዓመታት በኋላ ነው፡፡ ቢደራጅም በራሪ ወረቀቶችን ከመበተን ሌላ ያደረገው ነገር የለም፡ ፡ አብዮቱ ቀድሞ የፈነዳው ድርጅቱ ምንምባልሰራበት ሁኔታ ነው፡፡
የሕዝብ ትግል ሲቀለበስ ኢህአፓ የሕዝቡ ትግል ለምን ተቀለበሰና ግቡን አልመታም ብሎ መታገል ዋና ዓብይ ጉዳዩ ሆነ፡፡ በዚህ ምክንያት ከደርግ ጋር ተጋጨ፡፡ ደርግ ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ ሥልጣን መያዙን ኢህአፓ ከጅምሩ ጀምሮ ተቃውሟል፡ ፡ ከደርግ ጋር በተደረገው ግብግብና ትግል ውስጥ የተሰሩ ስህተቶች አሉ፡፡
አንደኛው ኢህአፓ ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ሞክሯል፡፡ ሰላማዊ ትግሉ አልሳካ ሲል ደግሞ ወደ ትጥቅ ትግል ገብቷል፡፡ የትጥቅ ትግሉ ሁለት ክፍል ነበረው፡፡ በገጠር ህዋሱን አሲንባ ላይ መስርቶ ነበር፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ደግሞ የከተማ ትጥቅ ትግልም ጀምሮ ነበር፡፡ የከተማው ትጥቅ ትግል ስህተቱ መነሻው ላይ አይደለም፡፡
ተጻራሪ አካላት ነገሮችን የሚያነሱት ሁሌም ራሳቸውን ነፃ ለማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ ኢህአፓ የመጀመሪያውን ጥይት ተኮሰ የሚለው አፋዊ ነው፡ ፡ በጥናት ላይ የተመሰረተና ማን ምን አደረገ ተብሎ በሀቅ የተሰራ ጥናት የለም፡፡ ኢህአፓ ግን ያንን የትጥቅ ትግል የጀመረው ራሱን ለመከላከል ነው፡፡
ምክንያቱም በ1969 ዓ.ም መስከረም ወር ደርግ ግልፅ ጦርነት በኢህአፓ ላይ በማወጁ የተነሳ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ኢህአፓ በሊቀመንበሩ ላይ የግድያ ሙከራ አድርጓል፡፡ እንዲሁም ትግሉን በሚያደናቅፉ በሌሎች አካላትም የግድያ ሙከራዎችንና ግድያዎችንም አካሂዷል፡፡ ይህ የወቅቱ የትግል ስልት ነው
«ያለደም ስርእየት የለም፤ አብዮት ልጇን ትበላለች» እንዲህ እንዲያ በሚሉ ትርክቶች የተሞሉ ትግል ይደረግ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ራስን ለመከላከል የተፈጠረ የከተማ ውስጥ ትጥቅ ትግል ነበር፡፡ ይህ ችግር አልነበረበትም፡፡ ነገር ግን ፓርቲው የከተማው የትጥቅ ትግል እየሰፋና እየተስፋፋ ሲሄድ የኃይል ሚዛኑን በመመልከት የሆነ ቦታ ላይ ሲደርስ ሚዛኑን አይቶ ትግሉን ማቆም፤ ማፈግፈግና ወደ ገጠሩ የትጥቅ ትግል መሄድ ነበረበት፤ ያን አላደረገም፡፡
በዚህ ምክንያት በርካታ ጥፋት ደርሷል፡፡ በርካታ ወጣት አላስፈላጊ መስዋእትነት ከፍሏል፡፡ የከተማውን የትጥቅ ትግል በጊዜና በሂደት አለማቆሙ አንደኛው ስህተት ነው፡፡ ምክንያቱም እስከ አፍንጫው ከታጠቀ መንግሥት ጋር በጥቂት ወጣቶችና መሣሪያ ባላቸው አነስተኛ ስኳዶች ስትታገል ኪሳራው ከፍተኛ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም፡፡
ሌላው ፓርቲው ብዙ ትኩረቱ የከተማው ትግል ላይ በመሆኑ የተነሳ ለገጠሩ ትግል የሚገባውን ያህል ድጋፍ ሳያደርግ ቀረ፡፡ለሠራዊቱም የሚገባውን ትኩረትና አቅም አልተሰጠም፡፡ ሁለቱ ተያያዥ ስህተቶች ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡– ኢህአፓ የደርግ ወታደራዊ መንግሥትአመራሮች ላይ የመግደል ሙከራ ያደረገውና የገደለውደርግን አሸንፋለሁ ብሎ ነው?
ወይዘሮ ቆንጅት፡– ኢህአፓ የከተማ ትጥቅ ትግሉን የጀመረው ጦርነት ከፍቶ ደርግን ሊያሸንፍ አልነበረም፡፡ ራሱን ለመከላከል ያደረገው እንቅስቃሴ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡– አሁን ኢህአፓ ከባለፈው ስህተቱ ተምሯልማለት ይቻላል?
ወይዘሮ ቆንጅት፡– ትናንትና ዛሬ በጣም የተለያዩ ቀናቶች ናቸው፡፡ ዛሬ ትጥቅ ትግል የለም፡ ፡ ያኔ የወቅቱ የትግል ስልት ያ ነበር፡፡ አብዮት ደግሞ በኢትዮጵያና በኢህአፓ ብቻ ሳይሆን መላው ዓለም ጭምር ምሥራቅና ምዕራብ በሚል የተከፈለበት ጊዜ ነበር፡፡ በተለይ የምሥራቁ ዓለም ብዙ አብዮቶችን አስተናግዶ አልፏል፡፡ ስለዚህ ዛሬና ትናንት በምንም መልኩ አይገናኝም:: የቀዝቃዛው ጦርነት ካከተመ በኋላ ዓለም ጎራም ከተቀየረ ቆየ፡፡ ስለዚህ ዛሬ ላይ ኢህአፓ መማሩ አይቀርም፡፡
በመጀመሪያ ኢህአፓ ከስህተቱ ከተማረ በጣም ቆይቷል፡፡ ድሮውንም ቢሆን እውነት ለመናገር ኢህአፓ ጦረኝነት ወዳድ ድርጅት አልነበረም:: ሁኔታዎች ሲገፉህ ጦረኛ ትሆናለህ፡፡ ኢህአፓ በከተማም በገጠርም መስዋዕትነትን የማይፈሩ ጀግና ልጆች ነበሩት፡፡ ሲጀምር ግን ሰላምን የማይወድ ድርጅት አልነበረም፡፡ ስለዚህ ሰላምን ይፈልጋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ መግባቱ ሰላማዊ ትግል ለማድረግ መለወጡን ያሳያል፡፡ ኢህአፓ ከኢህአዴግ (ህወሓት) ጋር ተስማምቶና ወዶት አያውቅም፡፡ ሲታገለው የቆየ ድርጅት ነው፡፡ በተለይ በጎንደር ከወያኔ ጋር በጣም ታግሏል፡፡ እኔ ባልኖርበትም ታሪኩ የሚያስረዳው ይህንን ነው፡፡ ልክ ለውጡን ተከትሎ በኢትዮጵያ ውስጥ የሰላም አየር አለ ብሎ መግባቱ የሚያሳያው ኢህአፓ መለወጡን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡– ኢህአፓ ከሰራው ስህተት አንጻር አሁንበኢትዮጵያ ተቀባይነት ይኖረው ይሆን?
ወይዘሮ ቆንጅት፡– ባለፉት 27ዓመታት ህወሓት ኢህአዴግ ከማንም በላይ በኢህአፓ ላይ አሉታዊ የቅስቀሳ ሥራ ሰርቷል፡፡ በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንኳ ሳይቀር ኢህአፓን የማጠልሸት ሥራ ከደርግ ባልተናነሰ እንዲያውም በበለጠ ሰርቷል፡፡ ስለዚህ ይህ ሥራ በኅብረተሰቡ ውስጥ ምንም ነገር ቢፈጥር አይገርምም፡፡ አዲስ አበባ የሚኖሩ የተወሰኑ ሰዎች በኢህአፓ ላይ የተፈጸመውን የስም ማጥፋት ዘመቻ ተከትሎ ፓርቲውን እንደ ጭራቅ የሚስሉት አሉ፡፡
እኔ ኢህአፓ ነኝ ስላቸው የሚደነግጡ ሰዎች አሉ፡፡ አሁንም ኢህአፓ ወደ ኢትዮጵያ መጣ ሲባል ጭራቅ እንደመጣ የሚያስቡ ሰዎች አሉ፡፡ ይህን ያመጣው ደግሞ የተሰራው የስም ማጥፋት ዘመቻ ነው፡፡ ፓርቲው ገና ስሙን የማንጻትና የማጸዳት ሥራ አልሰራም፡፡ መስራትም አይችልም ነበር፡ ፡ ምክንያቱም አገር ውስጥ መግባት አይችልም፡ ፡ አንዴ አሸባሪ ሌላ ጊዜ ሲአይኤ እየተባለ የቆየ ድርጅት ነው:: ስለዚህ በኢህአፓ ላይ ሕዝብ አሉታዊ አመለካከት ቢኖረው አይገርምም፡፡
በአሁኑ ጊዜ በየክልሎቹ ቢሮዎች እየከፈትን ነው፡፡ ጎንደርና ደሴ ላይ ቢሮ ከፍተናል፣ በደቡብ ክልልና በጎጃም ደግሞ ቢሮ ለመክፈት ዝግጅት ላይ ነን፡፡ በተለይ ሕዝቡ በጎጃምና ጎንደር ከኢህአፓ ጋር ሰላማዊ ትግል ማድረግ እንፈልጋለን ብሎ እየጠየቀ ነው፡፡
ሰከን ባለና በጥናት ላይ የተመሰረተ ነቀፋ ቢቀርብ ተመራጭ ነው የምንለው ለዚህ ነው፡፡ የጠለሸው ስሙ ሲጸዳ እኔንና እኔን የመሰሉ ወጣቶች የታገሉለትና የሞቱበት ድርጅት ስህተት ቢሰራም ምንም አያስደንቅም፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ነበር አላልኩም፡፡ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ ዴሞክራሲያዊ ነፃነትን ለማምጣት የሰራ መሆኑም መታወስ አለበት፡ ፡
አዲስ ዘመን፡– ኢህአፓ በምርጫ ቦርድ ምዝገባ አካሂዷል?
ወይዘሮ ቆንጅት፡- በምርጫ ቦርድ አልተመዘገብንም፡፡ ነገር ግን ኢህአፓ ወደ አገር ውስጥ የገባው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ መሠረት ነው፡፡ ከምርጫ ቦርድ ጋርም አብሮ ይሰራል፡፡ እንደ ፓርቲ ሕጋዊ እንድንሆን የሚያደርጉ ሥራዎችን እንድንሰራ ምርጫ ቦርድ ፈቃድ ሰጥቶናል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *