ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኃላፊነት በጎደላቸውና በላዔሰባዊ-ዝማሜ በተጫናቸው ‹አክቲቪስቶች› እና ፖለቲከኞች አዲስ አበባ ወደ መከራ-ቋትነት እየተገፋች ነው። ለእንዲህ አይነቱ ችግር በቀዳሚነት አቶ ጃዋር መሐመድ ይጠቀሳል። ከዚህ ቀደም ያስተላለፈውን አጥፊ የክተት ጥሪ ወደጎን ብንለው እንኳ፣ ሰሞነኛውን የእልቂት ‹ጽንሱ›ን ሳልጠቅስ ማለፍ አይቻለኝም። የሰውየውን ጭካኔና የነጠፈ ሰብዓዊነት የሚያስረግጠው ለህልፈታቸው ምክንያት የሆናቸው ወጣቶች በረገፉበት ቀውጢ ሰዓት እንኳ በርካታ የሚዲያ ካሜራዎች ፊት ቢቀርብም፣ ስለራሱ ከመደስኮር ባለፈ ቅንጣት ሀዘኔታ እንደተሰማው ለማሳየት አለመፍቀዱ ነው። ሌላው ነገር ቦሌ ተቀምጦ፣ ጉለሌና ባሌን ‹ቦስንያ› የማድረግ ‹ፕሮጀክት› አእላፍ ‹ጂኒ›ዎችን የመቀስቀሱ እውነታ ነው። ማን ያውቃል? አንዱ በቆፈሩት ጉድጓድ የሚከት ይሆናል?
በዶ/ር ዐቢይ አህመድ እና አቶ ለማ መገርሳ መሀል የተፈጠረው ስንጥቃትም ለሴራ ፖለቲካ አመችቷል። ኢትዮጵያዊነትን አቅል-ከሚያስት የሀሽሽ ሱስ ጋር ያነፃፅር የነበረ ሰው ‹ተገፋሁ› በሚል የግል-ጉዳይ ወደኋላ ዞሯል ሲባል ያስደነግጣል። አልፎ-ተርፎም የዜጎች እልቂት በሚመራበት ጥቁር መስመር ላይ ሲቆም፣ ‹ኦፍ ሳይድ› ብሎ ብቻ ማለፍ ይቸግራል። መቼም በግላጭ የለቀቁትን ‹መሰላል› በሸፍጥ ለመሳብ መሞከር፣ ‹የላይኛውን ብቻ አፍርጦ አለመስከኑን መረዳት የፖለቲካ ሀሁ ነው።
ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ፣ አዲስ አበባ ዋንኛ የፀብ ሜዳ ሆናለች። ሰገነቱን የሞሉት አክራሪ-ብሔርተኞች ‹በአገሪቱ ሁለት መንግሥት ነው ያለው፤ የቄሮና የዐቢይ› እስከማለት ከመድፈር በዘለለ፣ የከተማውን ነዋሪ ህልውና የካዱ ድርጊቶችን ደጋግመው ፈፅመዋል። በጥቂቶች የሚታጀብ ተቃውሞ ሰልፍ በሚከለከልበት መዲና፣ ገጀራና ቆንጨራ ለታጠቁ ወጣቶች፣ ያውም ፀረ-ሕዝብ ሰልፍ ማካሄድ ሙዝ የመላጥ ያህል አቅልለዋል። በአንድ ወቅት የከተማውን ወጣቶች ሰላማዊ ጥያቄ ማፈን ዒላማ ያደረገው የ‹አደገኛ ቦዘኔ ሕግ› ዛሬም በ‹ህይወት› መኖሩ የድራማው አስቂኝ ክፍል እንደሆነ ለተከበረው ዐቃቢ-ሕግ ማስታወስ እወዳለሁ። ከ1997 ዓ.ም በፊት ተጠሪነቱ ለፌደራል ፖሊስ የነበረው የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ በድኀረ-ምርጫ ወደ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ የዞረ ሲሆን፣ ዶ/ር ዐቢይ አህመድም ባላየ አልፈውታል።
የሆነው ሆኖ መሬት የረገጡ እውነታዎች የሚነግሩን ከዚህ በኋላም በተደራጁ ቡድኖች ከሚሰነዘር ጥቃት ‹የሚታደግ አለ› ብሎ መዘናጋቱ ለማይታረም ስህተት መዳረጉን ነው። እየመከርኩህ ያለው ጉዳይ ‹የመንግሥትን ኃላፊነት ተወጥቼ፣ ራሴን ከጥቃት እከላከላለሁ› ወደሚል መደምደሚያ እንድታዘነብል አይደለም። እንዲህ አይነቱ ግብረ-ምላሽ አደገኛ አደጋ ያስከትላል። ይህ ከፍርሃት ጋር አይያያዝም፤ አርቆ አሳቢነት እንጂ። በተረፈ የአዲስ አበባን ልጆች ቁርጠኝነትና ጀብደኝነት የተጠራጠረ የኢሕአፓን የከተማ ውስጥ የትጥቅ ትግል ታሪክ መለስ ብሉ ቢቃኝ መልካም ነው።
የኢሕአፓ አብዛኛው አመራር ከተለያየ የአገሪቱ አካባቢ እንደመጣ ባይካድም፣ ከሰለጠነና እስከ አፍንጫው ከታጠቀ የመንግሥት ሠራዊት ጋር ፊት-ለፊት ተጋፍጠው፣ በሸገር ጎዳና ተጋድሎ ከፈፀሙት እጅግ የሚበዙት የእኛ ልጆች ናቸው። እናም ‹ከተማዋ የሁሉም ኢትዮጵያዊ መኖሪያ እንጂ፣ መደባደቢ እንድትሆን አንፈቅድም› ወደሚሉበት ትዕግስት አስጨራሽ ትንኮሳ ከመግፋት መታቀብ ይመከራል። በነገራችን ላይ የሸገር የወል መስተጋብር የትኛውንም ብሔር አይወክልም። ዛሬ የያዘውን ቅርፅ የሰጠውም የባህል መመሳሰል አይደለም። ከእድርና ዕቁብ ጀምሮ የተለያዩ የጋራ ግንኙነቶች ክዋኔ ባዋለዱት ማኀበራዊ ሕይወት ላይ መመስረቱ እንጂ።
በዚህ ዐውድ የቀረበው ብቸኛ መፍትሔ አዲስ አበባን ለማያውቋት ካድሬዎች መቀለጃ፣ ለሕገ-ወጦች መፈንጪያ የዳረጋትን የፌደራል መንግሥት፣ በከተማው ላይ የያዘውን ሥልጣን አስጥሎ ሕገ-መንግሥቱን ማስከበር ነው። ይህንን ለማሳካት በተደራጀና በተቀናጀ ትግል አስተዳደራዊ መዋቅሩን እንደ ከዚህ ቀደሙ ክልላዊ ማድረግ ይጠይቃል። ይህ አይነቱ መንገድ የፌደራሉን ወመኔነት ከማስቀረቱም በላይ፣ ከጠርዘኛ የመሬት ቀበኛ ኢምፔሪያሊስቶች ይታደጋል። ለዚህ ደግሞ በሽግግር መንግሥቱ ዘመን ክልሎች የተዋቀሩበት አዋጅ (7/1984)፣ የሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 47 እና 49 ይደግፍሀል። ከ1989 እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ የተሻሻሉ ቻርተሮች የነዋሪውን ራስን-በራስ የማስተዳደር ሙሉ ስልጣን አለመካዳቸውም በማስረጃነት ይቆጠራሉ።
ሚዲያ ላይ ቀርበው ‹ሕገ-መንግሥቱ የአዲስ አበባን ሕዝብ አያውቀውም› ለሚሉ ወንድሞቻችንን እያዘንን፣ ከዚያው ሰነድ የሚመለከተንን እንምዘዝ። ክልል ለማዋቀር በአንቀጽ 47 ቁጥር 3 የተቀመጡት አምስቱ መስፈርቶች የሚከተሉት ናቸው፡-
‹‹ሀ- የክልል መመሥረት ጥያቄው በብሔሩ፣ በብሔረሰቡ ወይም በሕዝቡ ምክር ቤት 2/3ኛ ድምፅ ተቀባይነት ማግኘቱ ሲረጋገጥ ጥያቄው በጽሑፍ ለክልሉ ምክር ቤት ሲቀርብ፣
ለ- ጥያቄው የቀረበለት የክልል ምክር ቤት ጥያቄው በደረሰው በአንድ ዓመት ውስጥ ለጠየቀው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ሕዝበ ውሳኔ ሲያደራጅ፣
ሐ- ክልል የመመሠረት ጥያቄ በብሔሩ፣ በብሔረሰቡ ወይም ሕዝቡ ሕዝበ ውሳኔ በአብላጫ ድምፅ ሲደገፍ፣
መ- የክልል ምክር ቤት ሥልጣኑን ለጠየቀው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ሲያስረክብ
ሠ- በሕዝበ ውሳኔ የሚፈጠረው አዲስ ክልል ጥያቄ ማቅረብ ሳያስፈልገው በቀጥታ የኢትዮጵያ ፌደራል ዴሞክራሲዊ ሪፐብሊክ አባል ሲሆን ነው።››
እነዚህን ማረጋገጫዎች ይዘን ሁለት አንጓዎችን እናንሳ፤ የመጀመሪያው በአምስቱም ነጥብ ላይ ስለ መብቱ ተጠቃሚዎች የተገለፀው ‹‹በብሔሩ፣ በብሔረሰቡ ወይም በሕዝቡ›› የሚል አማራጭ በመስጠት የአዲስ አበባ ሕዝብንም ማካተቱ ነው። ሁለተኛው፣ ስለእነዚህ ሦስት አካላት ማንነት በአንቀጽ 39 ቁጥር 5 ከሰጠው ብያኔ ነው፡-
‹‹በዚህ ሕገ መንግሥት ውስጥ ‹ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ› ማለት ከዚህ ቀጥሎ የተገለፀውን ባህርይ የሚያሳይ ማኀበረሰብ ነው።
ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንፀባርቅ ባሕል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች ያላቸው፣ ሊግባቡበት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልውና አለን ብለው የሚያምኑ፣ የሥነ ልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖሩ ናቸው፤›› ከ5 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የሚኖርባት አዲስ አበባ፣ ክልል ለመመስረት በቅድመ ሁኔታ የተጠቀሱትን ሁሉንም መስፈርቶች ታሟላለች። ነጣጥለን እንያቸው፤ ‹የጋራ ባሕል ወይም ተመሳሳይ ልማዶች› ለተባለው በግርድፉ ‹ከተሜነት› የሚል ምላሽ አስቀምጦ ማለፉ ያስማማል፤ (ወደፊት በአዲሱ ፓርቲ ይዘረዘራል።) ለሁለተኛው እንኳ ‹ሊግባቡበት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ› እንጂ፣ የአፍ መፍቻ አለማለቱን ካስታወስን በቂ ነው። የሕልውናችን ተዛምዶም ማብራሪያ የሚፈልግ አይመስለኝም። አራተኛ ላይ ላለው ‹የሥነ ልቦና አንድነት›፣ በአጭሩ የዜግነት ፖለቲካ ማቀንቀናችን መለዮ ይሆነዋል። አምስተኛውን እናንተው ጨርሱት።
አዲስ አበባ እንደ ነዋሪዎቿ ከተሜ አስተደደር ያስፈልጋታል። እየሸራረፉት ካለው የህልውና ስጋት በአስተማማኝ መልኩ መታደግ የሚቻለውም ሆነ የፖለቲካ ተሳትፎና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚረጋገጠው መሰረታዊ የመዋቅር ለውጥ ሲመጣ ብቻ ነው። ይህንን አጀንዳ ውህድ-ፓርቲው ይፈታዋል ብሎ መዘናጋት ካሳለፍናቸው ስህተቶች አለመማር ነው። ‹ይሁን› ቢባል እንኳ ዛሬ ሥልጣን የጨበጠ፣ ነገ የመልቀቁን አይቀሬነት አንዘነጋም። የእንዲህ አይነቱ ጉዳይ ዋስትና ተቋማዊ በሆነ መንገድ መቋጨቱ ብቻ ነው። ለአንዳንድ አጨቃጫቂ ጉዳዮች የዐለም አቀፍ ተሞክሮዎችን መጠቀም ይቻላል።
የአዲስ አበባ ክልላዊ መንግሥት?
ከተማይቱን በክልል ደረጃ ለማዋቀር ብርቱ ትግልን ይጠይቃል። ሰፊ የማንቃት ሥራ መፈለጉና በአስቸጋሪ ፈተናዎች የማለፉ አይቀሬነትም ተገማች ነው። የድሉን ዕድሜ ለማሳጠር እንደ ‹ባልደራስ› ያሉ ‹ፎረሞች›ን በብዛት መመስረት ወሣኝ ነው። እነዚህን መሰል ድርጅቶች ጥናታዊ ጽሑፎችን በገፍ እያሰናዱ በአጀንዳው ላይ ብዥታ የሚፈጥሩ ጉዳዮችን ለማጥራት መስራታቸው መንገዱን ያቀልለዋል። መንግሥት ሳይናጋ፣ ሰላም ሳይደፈርስ፣ የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት ውይይቶችን ማካሄድ፣ በዙሪያው ካሉ የኦሮሞ ተወላጆች ጋር ስለ ወል ተጠቃሚነት መደራደር፣ መግባባት፣ መስማማት ቀዳሚ የቤት ሥራ ነው። በአካባቢው ያሉ የገጠር ነዋሪዎች ህይወት ሊቀየር የሚችለው የግንኙነት መስተጋብሩ ከአዲስ አበባ ጋር ሲጠብቅ እንደሆነ መተማመን ያስፈልጋል። በተለይ፣ ከእነሱ የኢኮኖሚ ባህል አኳያ ግብርና-መር ኢንዱስትሪያላይዜሽን እንዲስፋፋና ተመጋጋቢ ዕድገት እንዲኖር የሚያስችል ዕቅድ የሰጥቶ-መቀበሉ አካል ማድረግ ለቅቡልነት ያግዛል።
የብሔረሰቡ ባህልና ቋንቋ እንዲዳብር መደገፍ እና ኢንቨስትመንት ማበረታታት ላይ አተኩሮ መስራትም ነጥብ ያሰጣል። የሕዝቡን ፍላጎትና ውሳኔ ባከበረ መልኩም አስተዳደራዊ መዋቅሩን ለመዘርጋት መስማማት ግድ ይላል። ባህልን ከማኀበራዊ ሕይወት ነጥሎ የሚያየው ከተሜ፣ በአቻቻይ ፖለቲካ ለሁሉም ችግሮቹ እንደ ባሕሪያቸው መፍትሔ መቀመሩ አይነሳውም። በነገራችን ላይ አዲስ አበባን እና ኦሮሚያን የሚያጋጨው የከተማዋ እየተለጠጠች መሄድ፣ ወደ ክልልነት ስትቀየር ስለሚቆም ዘላቂ መፍትሄ ማምጣቱንም ከግምት መግባት አለበት። ከተማ እንጂ ክልል አይስፋፋም።
በመጨረሻም፣ በቀጣዩ ምርጫ በሸገር የሚወዳደሩ ፓርቲዎች ይህንን ጥያቄ በፕሮግራማቸው ቢያካትቱት አንድ እግርን ወደ መዘጋጃው ጽ/ቤት የማስገባት ያህል እንደሆነ በትህትና አስረዳለሁ። አሊያም ደግሞ አዲስ አበባን ክልል የማድረግ አጀንዳ የቀረፀ አዲስ ፓርቲ አቋቁሞ አራዳ ላይ ለመንገሥ ቀላሉ መንገድ ይህ ነው። በድምጽም በትግልም ሚሊዮኖችን ማሰለፍ ያስችላልና። ከተማይቷን የፖለቲካ ‹ሙት መሬት› ያደረገውን ሕገ-መንግሥት መገፍተሪያው ጊዜ ደርሷል። ጎሳን ጥለን፣ ከተሜነትን አንጠልጥለን መደራጀት ብቸኛ አማራጭ ሆኗል። በአዲስ አበባ ጉዳይ የማረቆ ወይም የኢሮብ ካድሬ የሚወስንበት የረገጣ-አገዛዝን በዚህ መንገድ አሰናብተን፣ ሳናንቀላፋ የምንጠብቀውን አስተዳደር እንተክላለን።
መደመደሚያ
የአዲስ አበባ ክልላዊ መንግሥት›
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ