የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር
News

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከነጃዋር ምን አለው? – ነፃነት ዘለቀ

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከነጃዋር ምን አለው?

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር እንደማንኛውም የቀይ መስቀልና የቀይ ጨረቃ ሰብኣዊ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ሁሉ በዘር፣ በቀለምና በሃይማኖት አድልዖ የማያደርግ፣ የሰው ልጆችን በምንም መንገድ ሳያዳላ እኩል ለማገልገል የተቋቋመ ድርጅት ነው፤ ይህን ዓላማውን መተዳደሪያ ቻርተሩ በሚገባ ይጠቅሰዋል፡፡ ይህ የገለልተኝነት ተፈጥሮው በአንድ ወይ በሌላ መንገድ ከተጣሰ ድርጅቱ ጤናማ አይደለም ማለት ነው፡፡

ከዚህ አኳያ በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የሚስተዋለው አሳሳቢ ጉዳይ ቀይ መስቀልም እንደፖለቲካው ሁሉ እየተበላሸና ጎሣዊ ስሜት እየተጠናወተው መምጣቱን የሚጠቁም ነው፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከነጃዋር ምን አለው?

የጎሠኝነቱን ጉዳይ ለጊዜው አቆይተነው እጅግ አስገራሚ ስለሆነውና ፕሬዝደንቱ አቶ አበራ ቶላ ለድርጅታቸው ለቀይ መስቀል ማኅበር ዓላማና መርኆዎች ተገዢ ከመሆን ይልቅ በፖለቲከኞች መድረኮች በመገኘት ያላንዳች ሀፍረት ያልተገባ ተግባር እያከናወኑ ስለመገኘታቸው የሚከተሉትን ልንል ወደድን፡፡

እንደቀይ መስቀል ያለ የአንድ ገለልተኛ ማኅበር መሪ ፖለቲካዊ ወገንተኝነት ይኖረዋል ተብሎ ባይገመትም የተለያዩ የኦሮሞ ፓርቲዎች የጋራ ስምምነት በተፈራሙበት ሥነ ሥርዓት ላይ በግንባር ቀደምትነት ሥነ ሥርዓቱን ከሚመሩ ግለሰቦች መካከል አቶ አበራ ቶላ አንዱ ሆነው በግልጽ ታይተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ አቶ አበራ ቶላ  ያለባቸውን ትልቅ ኃላፊነት በመዘንጋት በአንድ አክቲቪስት ቤት ተገኝተው በግልጽ ድጋፍ መስጠት በሚመስል እንቅስቃሴ ተሣታፊ ሆነዋል፡፡

ይህ ክስተት አጉል ጀብደኝነት ወይም ሕዝብንና አገርን መናቅ ነው፡፡ ይህ ከአንድ የተማረ ሰው የማይጠበቅ ክስተት  ሀገርንና ሕዝብን ብቻ ሣይሆን እንደ አንድ የትልቅ ሀገራዊ ማኅበር መሪነታቸው እርሳቸው ራሳቸውንም በእጅጉ ሊያሣፍራቸው ይገባል፡፡

 

የአንድ ገለልተኛ ማኅበር መሪ ሆኖ ከአንድ ጎራ የአንድ ዓይነት ፖለቲካዊ አስተሳሰብና አመለካከት ተጋሪዎች ጋር መሰባሰብ ኢ-ፍትኃዊነትን ከማሳየቱም በላይ የቀይ መስቀል ማኅበሩ በምን ዓይነት እጆች ውስጥ እንደሚገኝም አመላካች ነው፡፡

ይህንን ህገ ወጥ ተግባር የሀገራችን የቀይ መስቀል ቻርተር የሚከለክል ሲሆን ማኅበሩ አባል በሆነባቸው ተመሣሣይ ዓለም አቀፍ ተቋማትም የተወገዘ ተግባር ነው፡፡ ተቋሙ የሀገር ተቋም በመሆኑም የሚመለከታቸው አካላትና መንግሥት ጉዳዩን በቸልታ ሊያልፉት አይገባም፡፡

ይህ ሁኔታ ከቀጠለ አድልዖው በዜጎች መካከል ሊያስከትለው ከሚችለው ሀገራዊ ጉዳት በተጨማሪ የሀገራችንን ዓለም አቀፋዊ ምስልም ያጎድፋል፡፡ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ የሚዲያ አውታሮችም ጉዳዩን ተከታትለው  ወቅታዊ እርምት ሊወሰድ የሚችልበትን አግባብ እንዲጠቁሙ በዚህ አጋጣሚ ልናስገነዝብ እንወዳለን፡፡

 

Source: ZeHabesha

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *