ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ
News

የቀጣዩ ምርጫ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 6 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀጣዩ ሃገራዊ ምርጫ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ በዛሬው እለት ይፋ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ነሃሴ 10 ቀን 2012 ዓ.ም የድምጽ መስጫ ቀን እንዲሆን ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።

የቀጣዩ ሃገራዊ ምርጫ የባለድርሻ አካላት ስብሰባ በጁፒተር ሆቴል ተካሂዷል።

በስብሰባው የመጭው ሃገራዊ ምርጫ አጠቃላይ የትግበራ መርሃ ግብር ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ሲሆን፥ የጊዜ ሰሌዳው ህገ መንግስቱን መሰረት ባደረገ መልኩ ምርጫውን ለማስፈጸም ታቅዶ መዘጋጀቱ ተገልጿል።

በዚህም ከታህሳስ 22 እስከ መጋቢት 2 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ የምርጫ ክልል ቢሮዎችን ማደራጃ፣ የካቲት 24 የምርጫ ክልል ካርታ ይፋ ማድረጊያ፣ ከመጋቢት 29 እስከ ሚያዚያ 28 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ የመራጮች ምዝገባ እንዲካሄድ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ ቀርቧል።

ከዚህ ባለፈም የመወዳደሪያ ምልክት ማቅረቢያና መወሰኛ ጊዜ ከመጋቢት 29 እስከ ሚያዚያ 8 ቀን 2012 ዓ.ም፣ የዕጩ ምዝገባ ጊዜ ከሚያዚያ 13 እስከ ሚያዚያ 26 ቀን 2012 ዓ.ም፣ የምረጡኝ ዘመቻ ከሚያዚያ 27 እስከ ነሃሴ 5 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲሁም የዕጩዎች ዝርዝር ይፋ ማድረጊያ ሰኔ 7 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲሆን ረቂቅ ቀርቦ ምክክር እየተደረገበት ነው።

የድምጽ መስጫ ቀን እና ውጤት ሂደትን አስመልክቶ ለመራጮች መረጃ የሚሰጥበት ጊዜ ከሰኔ 24 እስከ ነሃሴ 19 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ፣ ዘመቻ የሚከለከልበት ጊዜ ከነሃሴ 6 እስከ ነሃሴ 9 ቀን 2012 ዓ.ም፣ የድምጽ መስጫ ቀን ነሃሴ 10 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲሁም የምርጫ ውጤት በምርጫ ጣቢያዎች ይፋ የሚደረግበት ቀን ነሃሴ 10 እና 11 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲሆን በቀረበው ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ ላይ ባለድርሻ አካላት ምክክር እያደረጉበት ይገኛል።

ከዚህ ባለፈም በምርጫ ክልል ደረጃ ውጤት ይፋ የሚሆንበት ጊዜ ከነሃሴ 11 እስከ ነሃሴ 15 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲሁም የቦርዱ የተረገጋጠ ውጤት ማሳወቂያ ጊዜ ከነሃሴ 11 እስከ ነሃሴ 20 ቀን 2012 ዓ.ም ሆኖ ቀርቧል።

ሙሉውን ለማንበብ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *