eprp
News

ኢትዮጵያ: የታላቁ ኅዳሴ ግድብ ጉዳይ ለሉአላዊነት የመቆም እና የአገርን ጥቅም የማስጠበቅ ጥያቄ ነው

ኢሕአፓ – EPRP

ኢትዮጵያ የበርካታ ወንዞች ባለቤት ብትሆንም በዘመኑ ስልጣኔ ተጠቅማ ወንዞቿን ለእድገት መሰረት ማድረግ ያልቻለች ሀገር ነች፡፡ ኢትዮጵያ ኣይደለም የዉሃ ሃብቷን ወደ እድገት ማማ መወጣጫ ማድረግ ቀርቶባት የህዝቧን የንፁህ ዉሃ ጥማት ማርካት ያልቻለች አገር ነች፡፡ ያም ሆኖ ታዲያ የዉሃ ጉዳይ በተነሳ ቁጥር ስሟ የሚነሳ ነች ኢትዮጵያ፡፡
ኢትዮጵያ ለበርካታ ዘመናት ከዓባይ ተፋሰስ ልታገኝ የሚገባትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሊያስገኝላት የሚችል ተግባር ባታከናዉንም ዓባይን የተመለከቱ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ትግል አቋርጣ አታዉቅም፡፡ ያም ሆነ ይህ የጥቁር ዓባይ መነሻዋ ኢትዮጵያ በዓባይና ገባሮቹ ዉሃ ለመጠቀም ሁኔታዎች ያልተመቻቹ በመሆናቸዉ በዓባይ ዉሃና በሚወስደዉ ለም አፈር ግብፅና ሱዳን ተጠቃሚ ሆነዉ ቆይተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኣቆጣጠር በ2003 ዓ.ም. በዓባይ ላይ የተጀመረዉ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ታዲያ ከጥንት ጀምሮ የዘለቀዉን የግብፅን ስጋት ወደ ከፍተኛ ደረጃ አሸጋገረዉ፡፡ በዚህም የተነሳ በሶስት የተፋሰሱ ሀገራት መካከል የተጀመረዉ ድርድር በርካታ ዓመታትን ቢያስቆጥርም፤ ዉይይቱ መቋጫ ሳያገኝ እነሆ ዛሬ ላይ ከተደረሰበት የዛቻና የማስፈራራት ዘመቻ ለመድረስ በቅቷል፡፡

የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ዓለም አቀፍ ህግ ባለበትና የጋራ መግባባት በተፈጠረበት በአሁኑ ወቅት፤ ኢትዮጵያ ወንዙ ከግዛቴ ስለሚፈስ ተፋሰሱን ለመቆጣጠር ያልተገደበ ሉኣላዊ ስልጣን አለኝ ባላላችበት ሁኔታ፤ የዓባይን ወንዝ እስከ 85% የምታበረክተዉ ኢትዮጵያ ከወንዙ ተመጣጣኝ የሆነ ጥቅም እንዳታገኝ የሚያደርግ ፍትሃዊ ያልሆነ መከራከሪያ ይዞ ዛቻ ዉስጥ መግባት የሚያዋጣ ያለመሆኑን ግብፅ ልትረዳ ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ በግዛቷ የሚነሳዉን ዓባይንና ሌሎች ገባር ወንዞች ከየትኛዉም መንግስት ፈቃድ ሳትጠይቅ ለዜጎቿ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግልጋሎት እንዲያስገኙ የማድረግ መብት ኣላት፡፡ ይህን ስታደርግ ዓባይ የአስራ አንዱም የተፋሰሱ ሃገሮች ተመጣጣኝ ግልጋሎት የማግኘት መበታቸዉን በማክበር ነዉ፡፡ የዓባይ ወንዝ የግብፅና የሱዳን የግል ንብረታቸዉ የሆነ ያህል በተናጠል የሚጠቀሙበትና የሚያስተዳድሩት ሳይሆን ሁሉም የተፋሰሱ ሀገሮች ፍትሃዊና ሚዛናዊ በሆነ መልኩ እንዲጠቀሙበት በሚፈቅድ የህግ ማእቀፍ መተዳደር የሚገባዉ የጋራ ሀብታቸዉ ነዉ፡፡

እ ኤ አ በ1997 ዓ.ም. የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን አጠቃቀም አስመልክቶ ባወጣዉ ኮንቬንሽን በአንቀፅ 5 ላይ ፍትሃዊና ሚዛናዊ ግልጋሎትን ሲደነግግ ወንዞችን ግልጋሎት ላይ ለማዋል የሌላኛውን ተጋሪ ሃገር መንግስት ፈቃድ መጠየቅ እንደማያስፈልጋቸዉ ያመለክታል፡፡

ዛሬ ኢትዮጵያ በጦር ሰበቃ የምታምን ሃገር አይደለችም፤ ሆኖም በሀገር ሉአላዊነትና ጥቅም ላይ ለመጣ ደግሞ መልስ መስጠት የምታውቅ ሃገር መሆኗን ታሪኳ የሚመሰክርላት ሃገር ነች፡፡ ልጆቿ አጥቂ ሲመጣ የዉስጥ ችግራቸዉን ወደጎን በማድረግ መሰባሰብን በተደጋገሚ ያስመሰከሩ ናቸዉ፡፡ በዉጭም በዉስጥም የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን፤ አሜሪካና የዓለም ባንክ ለምን ትእዛዛችን አልፈፀማችሁም ብለዉ የሚከለክሉንን የገንዘብ ዳረጎትና ብድር በጋራ ቆመን ለማዋጣትና ልክ ግድባችንን በራሳችን ጥረት እንደሰራነዉ የፍፃሜዉንም ሃላፊነት በጋራ ልንወጣዉ ይገባል፡፡

የጠ/ሚ አቢይ መንግስት ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበትንና ጥቅሟን የሚጎዳዉን ዉል አልፈርምም ማለት እንደሚገባ እያመንን አሁን በሂደት ላይ ያለውን እርምጃ እንደግፋለን፤ በሀገር ወዳድነት ከዓባይ ጋር በተያያዘ መንግስት የሚወስደዉን ርምጃ ሁላችንም በጋራ ልንደግፈዉ እንደሚገባና እንደ አንድ ሰዉ በህብረት እንድንቆም ኢህአፓ ያሳስባል፡፡ መንግስትም የሚወስዳቸዉን ርምጃዎች ሁሉ በዴሞክራሲያዊነትና በግልፅነት ከባለ ድርሻ ዜጎች ሁሉ ጋር እንዲመክር አበክረን እናሳስባለን፡፡

አንድ መቶ ሃያ አራተኛውን የአድዋን ድል ስናከብርም የውስጥ ፖለቲካዊ ልዩነቶቻችንን ወደጎን በማድረግ አገራችን ከገጠማት ችግር እንድትወጣ በአንድ ላይ እንድንቆም ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም በአንድነቷ ጸንታ ትኑር!!!
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)

Battle_of_Adwa

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *