Liya Tadesse
Africa Health News

የኮሮናቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱ ተረጋገጠ

የኮሮናቫይረስ ያለበት አንድ ጃፓናዊ ኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱን የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ።

ሚኒስትሯ ዛሬ ከሰዓት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት የካቲት 25 2012 ዓ.ም ከቡርኪናፋሶ ወደ ኢትዮጵያ የመጣ ጃፓናዊ የኮሮናቫይረስ ተገኝቶበታል

የጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ እንዳሉት ጃፓናዊ ትኩሳትና ማሳልን የመሳሰሉ የቫይረሱ ምልክቶችን የሚያሳይ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በለይቶ ማቆያ ውስጥ ይገኛል።

የጤንነቱ ሁኔታም መጥፎ የሚባል አንዳልሆነ ጨምረው ገልፀዋል።

ከጃፓናዊው ጋር ንክኪ የነበራቸው ከ25 በላይ ሰዎች ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑ በመግለጫው ላይ ተነግሯል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መግለጫ ከመስጠቱ ጥቂት ቀደም ብሎም የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ የሆኑት ኢንጂነር ታከለ ኡማ በትዊተር ገፃቸው ላይ አንድ ጃፓናዊ የኮሮናቫይረስ ተገኝቶበታል ሲሉ አስታውቀው ነበር።

ከንቲባው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች መውሰድ ያለባቸውን ጥንቃቄ በመልዕክታቸው ላይ ጨምረው አስፍረዋል።

በቅርቡ ኢትዮጵያ የነበረና ወደ አሜሪካ የተመለሰ አንድ አሜሪካዊ የኮሮናቫይረስ እንደተገኘበት ተገልጾ እንደነበር ይታወቃል።

በጣሊያን አገር በበሽታው ህይወቱ እንዳለፈ ስለተነገረ አንድ “ኢትዮጵያዊ” በሰጡት ምላሽ እስካሁን በውጪ አገር በበሽታው ተይዘዋል ስለተባሉ ኢትዮጵያዊያን የሚያውቁት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ብቻ እንደሆነና ስለጣሊያኑ መረጃ የለንም ብለዋል።

ዶ/ር ሊያ ግለሰቡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከየካቲት 9 እስከ የካቲት 13 2012 ዓ.ም እንደቆየና በሽታው ይዞታል ተብሎ ሆስፒታል የገባው የካቲት 30 2012 ዓ.ም እንደሆነ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ሳለ ከግለሰቡ ጋር ንክኪ አድርገዋል የተባሉ ሰዎች እንደተመረመሩና እስካሁን ምንም እንዳልተገኘባቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን ድረስ ለዜጎች አስፈላጊውን የጥንቃቄ መልዕክት ከማስተላለፍ በዘለለ ምን ዓይነት እርምጃ ለመውሰድ እንዳልተዘጋጀ በመግለጫው ላይ ተጠቁሟል።

ሕብረተሰቡ ከመንግሥት የሚሰጡ መረጃዎችን እየሰማ ተግባራዊ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል።

ቫይረሱን ለመከላከል አለመጨባበጥ፣ ከቫይረሱ ከተጠቁ አገራት የመጡ እንግዶችን ማሳወቅ፣ ሳል ወይንም ትኩሳት ካለው ግለሰብ መራቅ፣ እጅን በአግባቡ መታጠብ፣ አይንና አፍንጫን አለመንካት እና ሌሎች መልዕክቶች ተላልፈዋል።

ከንቲባ ታከለ ኡማ በትዊተር መልዕክታቸው ላይ “…ሁላችንም ከእጅ ንክኪና ከአላስፈላጊ ስብሰባዎች አንቆጠብ ለማለት እፈልጋለሁ” በማለት የጥንቃቄ መልዕክታቸውን ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች አስተላልፈዋል።

መንግሥት ለቫይረሱ መከላከል ከ300 ሚሊየን ብር በላይ መድቦ እየሰራ መሆኑን ዶ/ር ሊያ ጨምረው ተናግረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *