Dr.beyene
News

“የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች ውዝግብን ከመጫር ባሻገር የፈየዱልን አንዳችም ነገር የለም” ፕ/ር በየነ

የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች መምጣት አለመምጣት በአገራዊው የምርጫ ሂደት ላይ የሚያሳድረው አንዳችም ተጽዕኖ እንደሌለ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ)ፕሬዚዳንትና የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ አስታወቁ ።

ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፣ የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች መምጣት አለመምጣት በአገራዊው የምርጫ ሂደት ላይ የሚያሳድረው አንዳችም ተጽእኖ የለም፤ ምክንያቱም ታዛቢዎች ባሉበት ባለፉት ምርጫዎች ወቅትም ውዝግብን ከመጫር ባሻገር የፈየዱልን አንዳችም ነገር የለም።

በተለይም በ1997ቱ ምርጫ ወቅት የአውሮፓ ህብረት ታዘብኩ ብሎ ያወጣው መረጃ እንደ አገር ብዙ ዋጋ የከፈልንበት ብዙ ትርምስ የተፈጠረበት ከመሆኑ አንጻር አሁን ላይ አንመጣም ማለታቸው የሚያጎለው አንዳችም ነገር የለም፤ እኛም አንጠብቃቸውም ብለዋል።

ብዙ ምርጫን ከመሳተፌ አንጻርና ባለኝ ልምድ ከአውሮፓ ህብረት ምርጫ ታዛቢ እየተባሉ ቢመጡም የተጣለባቸው ኃላፊነት በአግባቡ ሲወጡ አይቼ አላውቅም ብለዋል ፕሮፌሰር በየነ ። እንደውም አንዳንድ ጊዜ ስራቸውን ሙሉ በሙሉ ዘንግተው እንደ አገር ጎብኚ ቱሪስት ሁሉ ሲያደርጋቸው እንደታዘቡም አመልክተዋል።

ከዚህ የተነሳም እነሱ እየታዘብን ነው በሚሏቸው አካባቢዎች ላይ እንኳን ችግር አለ ተመልከቱልን ሲባሉም ፍቃደኛ የማይሆኑበት ጊዜ ብዙ መሆኑን ገልጸዋል። ፕሮፌሰር በየነ የአውሮፓ ህብረት ታዛቢዎች መቅረታቸው እንደውም የውስጥ አቅማችንን ተጠቅመን ምርጫውን ተዓማኒ እንድናደርገው እድል የሚሰጥ ይመስለኛል ብለዋል። (ኢብኮ)

ምንጭ፤ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *