Analysis Opinion

‹‹መቼም የትም እንዳይደገም›› ከስም ባሻገር ለእኔ ትውልድ ሰዎች

20 December 2020

በተስፋዬ ወልደ ዮሐንስ

‹‹የቀረ ሰው አለ››

‹‹አምና የተነሳ መንገድ የጀመረ

ካሰበበት ሊደርስ ወገቡን ያሰረ

ትናንት የነበረ ዛሬ ግን የሌለ ሰው አለ የቀረ

እኛስ ተገኝተናል ዘመን ተሻግረናል

በለቅሶ ሸለቆ ሰንጥቀን አልፈናል

እንደ ሻማ ቀልጦ እዚህ ያደረሰን አለ ሰው የቀረ

አጥንቱ እንደ ጀልባ ደሙ ባህር ሆኖ እኛን ያሻገረ፡፡››

ዳዲሞስ

‹‹መቼም የትም እንዳይደገም ››  ከስም ባሻገር ለእኔ ትውልድ ሰዎች

ሁነቱ ከተፈጸመ ወደ አምስት አሥርት ዓመታት መጠጋቱን ተያይዞታል፡፡ ብዙዎች ለነፃነት፣ ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ያካሂዱት የነበረውን ተጋድሎ ለማስቆም የተደረገ የኃይል ዕርምጃ መሆኑን ጠቅሰው ከታሪኮቻችን አንዱ አካል አድርገው አስፍረውታል፡፡ ይህንን ጨካኝ ጊዜ በአዲስ አበባ የሚገኘው የቀይ ሽብር ሰማዕታት መታሰቢያ ሙዚየም መግቢያ በር ላይ ‹‹መቼም የትም እንዳይደገም›› ከሚለው ሐውልት ጎን ለጎን፣ ‹‹በአንድ ሌሊት የወለድኳቸው ይመስል በአንድ ሌሊት ጨረሷቸው›› የሚለው አራት ልጆቻቸውን በአንድ ሌሊት ያጡት እናት ወ/ሮ ከበቡሽ አድማሱ ቃል ድርጊቱን፣ ስሜቱን፣ ብሶቱንና ሥቃዩን በብዙ ብዙ ገላጭ ይመስለኛል፡፡

በሟቾች ቁጥር በማይስማሙበት ወገኖች መሀል የወደቁ ለአገራቸው የሞቱ፣ ለፍትሕ፣ ለእኩልነት፣ ለነፃነታቸው ነፍሳቸውን ከሥጋቸው በኃይል እንዳትለይ የተደረጉ ወገኖቻችን ከቁጥርነት ባሻገር ለሰውነት፣ ለከንቱ ሳይሆን ለአገራቸው የነበራቸውን ፍቅር ስለመሆኑ ለማሰብ ጊዜና ዕውቀት ጠይቆናል፡፡ ቀይ ሽብር ለእኔ ትውልድ እንደሆነ ዕድለኛ የሆነ ሰው ካላችሁም ጥቂት ማጣቀሻ ንባብ አግኝቷል፡፡ አብዛኛው ግን የእኔ ትውልድ ቀይ ሽብርን ከሰው ሞት ይልቅ የሚያውቀው ሲኖትራክ ስለሚባል በሕገወጥ መንገድ መንጃ ፈቃድ በማውጣት ማሽከርከርን ተከትሎ፣ በተደጋጋሚ አደጋ በማድረስ ለሚታወቅ ቻይና ሠራሽ መኪና በተሰጠ መጠሪያ ስያሜ ነው፡፡

ከዚህ ባለፈ ለምን በደንብ ሳይወራ፣ በደንብ ሳይነገር፣ ከታሪካችን አንዱ አካል ያልሆነ ያህል ተተወ? የሁልጊዜውም ጥያቄ ሆኖ ይሰማኛል፡፡ ያንን ጨካኝ ጊዜ በአዲስ አበባ የሚገኘው የቀይ ሽብር ሰማዕታት መታሰቢያ ሙዚየም መግቢያ በር ላይ ‹‹መቼም የትም እንዳይደገም›› ከሚለው ሐውልት ውጪ ብዙም ሳይባል ለዛሬው የመተራረድ፣ የመቆሳሰል፣ የመፈነቃቀል ጊዜ ዳረገን ብሎ ተመልሶ መጠየቅ ትክክል መስሎ ይሰማኛል፡፡ ጠባሳችንን መካድ እርግጥ ነው ያ ዘመን ከባድ ነበር፡፡ አብዮተኞቹ ‹‹ያለ ምንም ደም. . .›› የተባው ለውጥ ምናልባም ወርቃማ ከሚባሉ ዘመናት የሚመደቡ ዕንቁ የአገር ልጆች አሳጥቶናል፡፡ ከአጠገቡ ወንድሙን፣ እህቱን፣ እናቱን፣ አባቱን፣ ይህንን እንኳ አላየሁም ቢል የትምህርት ቤትና የሠፈር ጓደኞቻቸውን፣ ዕልፍ ሲል ጎረቤቱንና ቢከፋ ዘመዱን ያላጣ ሰው የለም፡፡

ሲከፋ ደግሞ በራስም ላይ ከግርፋት እስር እስከ ሞት ማምለጥ ድረስ በሕይወቱ ውስጥ፣ በአንድም ይሁን በሌላም በኩል ያላገኘው የእዚያን ትውልድ ሰው በጣም ጥቂት ይመስለኛል፡፡ ያንን ዘመን ከባድ የሆነብን ጉዳይ አሁን አድገን ቤተሰብ መሥርተን ለራሳችንም ሆነ ለቤተሰባችን ያለመንገር ጠባሳችንን መካድ የመረጥን ብዙ ነን፡፡ አንድ አሜሪካ የሚገኝ ወዳጄ 70 ዓመቱን ሲያከብር ልጆቼ ደርሰዋል ሲል ስላለፈበት የአሲምባ ምድር ትግልና ታጋይነት ለማስረዳት ሞክሮ፣ የደረሰበትን ከባድ ችግር ለመወጣት የሄደበት መንገድ ቀላል አልነበረም፡፡ እዚህም አገር ውስጥ ቢሆን በርካቶች ለልጆቻቸው ስለዘመኑ ቀርቶ ስለራሳቸውም የሕይወት ታሪክ ለልጆቻቸው አይነግሩንም፡፡

አንድም ጠባሳውን ካለመነካካት በሌላ በኩል ደግሞ ችግሩ ዛሬም አለ ብሎ ከማሰብ የመነጨ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ አንዲት ወዳጄ ከቀናት በፊት፣ ‹‹ስለእስር ቤት ታሪኬ ለልጆቼ እንድነግር ባለቤቴ ቢጨቀጭቀኝም ምንም ላለማለት ወስኛለሁ፡፡ ምክንያቱም እናታችንም ለካ አብዮተኛ ነበረች ብለው በእኔ ይለፍ ያልኩትን ትግል፣ በአሁኗ የኢትዮጵያ ዝብርቅርቅ የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ ውስጥ ተነክረው በአርዓያነት ላለመታየት በማሰብ ነው?›› ስትል አጫውታኛለች፡፡ ግን እነዚህ ታሪኮች ቀይ ሽብርን ከማሳወቅና ስለነበረው እሳት ለማስረዳትና ለመቆም ከመሮጥ ይልቅ፣ ዛሬም ሌላ ደም መፋሰስ የታሪካችን አካል ከማድረግ ወደ ኋላ አላደረገውም፡፡

ያውም ከዚያኛው ትውልድ በባሰ በአደባባይ ሰውን እስከ መስቀል አሻገረን አንጂ፡፡ የቀይ ሽብር ጠባሳ ለሦስት አሥር ዓመታት ለሚቆጠር ጊዜ ሰዎች ለመብታቸው፣ ለነፃነታቸውና ለፍትሕ ከመቆም ይልቅ ከአገራዊ ጉዳዮች ከፖለቲካው እንዲርቁ ትልቁን ሚና ተጫውቷል፡፡ ‹‹ፖለቲካና ኮረንቲን በሩቁ ነው፣ የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም›› የሚሉ አባባሎች ጎላ ብለው እንዲሰሙ ዕድሉን አመቻችቷል፡፡ ግን አሁንም የኢትዮጵያ ዜጎች ላይ አስተዳደሩ ይሁን የፖለቲካ ፓርቲዎቹና ምኅዳሩ ለሃምሳ ዓመታት ያልተመለሱ የፍትሕና የነፃነት እኩልነት ጥያቄ ይዘው፣ ከግለሰብ ግድያ እስከ ዘር ማጥፋት ዘመቻ ድረስ ሆይ ሆይ ማለትን ተያይዘውታል፡፡ አደጋው ለአሁን ብቻም ሳይሆን ወደ ነገም የሚጓዝ አድርገውብናል፡፡

ከዚህም አልፎ ኢትዮጵያ ሲባል በምንም ነገር እርግጠኛ አለመሆን የሚል ስሜት ፈጥረውብናል፡፡ ‹‹ያልታደልሽ እንደምን አደርሽ?›› አባባል ይህንን ዓይነቱ ሁኔታ ይገልጸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ቀይ ሽብር ዛሬና ነገ ያ ዘመን ያለፈበት መንገድ በአግባቡ፣ በትክክል፣ በሚመጥንና በታሪክ መልክ ብዙ አልተነገረም፡፡ ለዚህኛውም ትውልድ አልተላለፈም፡፡ የታሪካችን አንዱ አካል ከመሆንም አልተፋቀም፣ አይፋቅም፡፡ ለእዚያ ትውልድ መጋደል ዓይነተኛ ምክንያቱ ‹‹ቸ›› እና ‹‹ሸ›› የሚባሉ ፊደሎች ናቸው የሚል ትርክት ሁሉ እስከ መነገር ደርሷል፡፡ በደንብ ያልተጻፈና ያልተነገረ ታሪክ ውጤቱ ይህ ነው፡፡ የአሉ አሉና የአፈ ታሪክ ጉዳይ ይሆንብኛል፡፡ ዛሬም ነገም የትም እዳይደገም ስላልን ብቻ ከመድገም ወደ ኋላ የምንል አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ሕመሙን እንድናውቀውና እንዲሰማን፣ ብሎም አይሆንም እንድንል የሚያስችል ከፍታ ላይ አስቀምጦን ባለማየቴ ነው፡፡

ዛሬን ሆነ ነገንም እንድፈራው የሚያደርገኝ በየዕለቱ ያለው ሥራችንም ጭምር ነው፡፡ ቀይ ሽብር ለዚህኛው ለእኔ ትውልድ ስለሰው ዋጋነት ብዙም አላስተማረውም ብዬ አምናለሁ፡፡ መሪዎቻችንም ቅርፅና የስም ለውጥ አደረጉበት አንጂ የሰው ልጅ ሞት  ከእንስሳት እኩል የሆነባት አገር እንድትፈጠር ትልቁን ሚና ተጫውተውባታል፡፡ በቅርብ ጊዜ ታሪካችን ውስጥ ግጭቶቻችንን የምንፈታባቸውን መንገዶች ሳስብ፣ የታሪክ አሰናነዳችንና የትምህርት ሥርዓታችን ትልቁ የውድቀታችን ማሳያ ይመስለኛል፡፡ ትምህርት በአስተሳሰባችን ላይ ከጥይት፣ ከጉልበትና ዱላ ዕልፍ ብሎ መሠረታዊ ለውጥ አላመጣም፡፡ በትናንት ታሪካችን ባንስማማ እንኳ የነገውን በጋራ መጻፍ እንደምንችል አምናለሁ፡፡ ዛሬ አስወጣውና ግደለው ባይ በእያንዳንዱ የደሃ ሞት፣ በእያንዳንዱ የሰው ሕይወት ማለፍ ውስጥ የገዳዩን ያህል ድርሻ እንዳለውም አምናለሁ፡፡ ስለመንግሥት ስናወራና ስንወቅስ ሩቅ ስለሆነ አይሰማንም፡፡ አጠገባችን ግን ያለውን በደል፣ ግድያና ግፍ አናወራውም፡፡ ምክንያቱም በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ እኛ የዚህ ታሪክ አንድ አካል ስለሆንን ነው፡፡

ጨቋኝና ተጨቋኝ፣ ገዳይና ተገዳይ ቤታችን፣ በሠፈራችንና በአካባቢያችን ነው ያለው፡፡ ስለዚህ እንዳይደገም ስንል ከራሳችን የአዕምሮ ሰላም ጋር ታርቀን መሆን አለበት፡፡ ስንፀየፍ ከቤታችን መጀመርን ግድ ይለናል፡፡ አለበለዚያ ግን አሁንም በብዙ እጥፍ እንደግመዋለን፣ እንደጋግመዋለን፡፡

‹‹ከማዶ ተራራ፣ እዚህኛው ተራራ

የቸገረን ጊዜ እንድንጠራራ

እስኪ ስም አውጡለት ለያዘን መከራ፡፡››

ከአዘጋጁ፡– ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው twoldeyohanes@gamil.com ማግኘት ይቻላል፡፡

Source: http://www.ethiopanorama.com/

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *