Analysis

አምስቱ የህወሀት ቀድመ ሁኔታዎች ሊሳኩ የሚችሉ ግቦች ወይስ ጦርነት መስቀጠያ መሳሪያዎች?

በባጤሮ በቀለ

የካቲት 15, 2014 (ፈበርዋሪ 21፣2022)

 

የህወሀቱ መሪ ዶክተር ደብረጽዮን ከሁለት ቀናት በፊት ጦርነቱን ለማስቆም ያቀረባቸውን ስጥቶ መቀበል በሚባል ነገር አይሸራረፉም ያላቸውን አምስት ቀድመ ሁኔታዎችን አስቀምጧል፡፡ አራቱ ከጦርነት በፊት በእጃቸው የነበሩና በራሳቸው ጥፋት ያጧቸው መሆናቸውን ተመለከትኩ፡፡ ወልቃይትን ልቀቁልኝ፣ ራያን ልቀቁልን፣ የኤርትራን ጦር  ከትግራይ ይውጣ : ውሀ ኤሌክትሪክ በጀት ልቀቁልን፣ ባንክ ይከፈትልኝ፣ ሰራዊቴን እንዳለ ይዤ መቀጠል አለብኝ  የሚሉት  ሁሉ ከጦርነቱ በፊት ሙሉ በሙሉ ተግባርዊ የሆኑ ጉዳዮች ነበሩ ። አምስተኛው በጦርነቱ ውስጥ ወንጀል የፈጸሙ ለፍርድ ይቅረቡ የሚል ነው፣ ይህ ደግሞ ራሱ ህወሀትንም የሚመለከት ስለሆነ “ብየ ነበር”  ለማለት ካልሆነ በስተቀር ብዙም ውሃ የሚቋጥር ጥያቄ እይደለም፡፡

የህወሀት ዋናው የድርድር ጥያቄ ይህ ከሆነ፣ ጦርነት ውስጥ ለምን ገባ? እነዚህን ሁሉ ከጦርነቱ በፊት ምንም ሳይሸራረፉ ለትግራይ የተሰጡ አልነበሩም  እንዴ? የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ይህ ድርጅት 300 ሽህ ወጣቶችን አስፈጅቶ፣ የትግራይን ህዝብ ጎረቤቱ ብቻ ሳይሆን ቤተሰቦቹም ከሆኑት  የአማራ፣ የአፋርና የኤርትራ ነዋሪዎች ጋር በደም አቃብቶ፣ ህዝቡንም በርሀብ በችጋር ውስጥ እንዲዘፈቅ ንብረቱም እንዲወድም አድርጎ   አሁን ለትግራይ ህዝብ ምን አስገኘሁ ማለት ይችላል? ብየ እጠይቃለሁ፡፡

እኔ ስመረምረው የህወሀት ነገር ሰዶ ማሳደድ ሆኗል፡፡ በትምክት ይዞት የተነሳው ሁሉንም ደምስሦ በሶስት ወር አዲስ አበባ ላይ መንግስት እንደገና የመመስረት እቅዱ ሲከሽፍ ግራ የተጋባና የሚፈልገውን በአግባቡ የተረዳ አለመሆኑ እየተጋለጠ ነው፡

ከዚህ በተጨማሪ  ደግሞ  የደረደረው ቅድመ ሁኔታ በምድር ላይ ያለው እውነታና የአጎራባች ክልሎችች ነዋሪዎችም ስነልቦና  ከጦርነቱ ወዲህ እጅግ የተቀየረ መሆኑን ህወሀት አሁንም የተገነዘበ አይመስልም፡፡

የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ህዝብ እንደገና በህወሀት አስተዳደር ስር ይግባ የሚለው ጥያቄ እንኳንስ በአካባቢው ነባር ነዋሪ ዘንድ ከዚያም ወጭ ባለው ህዝብ በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌለው  ነው፡፡

ህወሀት የትግራይን ህዝብን ያማከለ የስላም ፍላጎት ቢኖረው ተግባራዊ የማይሆን ቅድመ ሁኔታ ከመደርደር ይልቅ ለድርድርም ቢሆን የተሻለ አጀንዳን ማቅረብ ይችል ነበር ፣  በፍጹም የማይሆን ነገር እንደ ቅድመ ሁኔታ ሲደረድር ግን ይህን ለማስፈጸም ችሎታ የለውምና እቅዱ እውን ከማድረግ ይልቅ ወደ ቀጣይ የማያባራ ግጭት የሚቀርብ የትግራይንም ህዝብ ሰቆቃ እያራዘመ የሚሄድ እስትራተጂን እየተከተለ መሆኑን ያመላክታል፡፡

ሌላው አስቂኝ ነገር ዶክተር ደብረጽዮን በዚያው ንግግሩ ውስጥ ህወሀት አሁን ባለው “ ከበባ “ ስር መቆየት አንደማይችል ስለዚህም ያቀረበው ቅድመ ሁኔታ ሁሉ በአጭር ጊዜ ካልተፈጸመ በጉልበት ከበባውን እንደሚሰባብር መዛቱ  ነው፡፡

ሰሜታዊ ለሆነ የትግራይ ብሄረተኛ ይህ የደብረጽዮን ዛቻ በተግባር ሊተረጎም የሚችል ሊመስለው ይችላል፡፡ ረጋ ብሎ ለሚያስብ ሰው ግን  ይህ አባባል  ባዶ ፉከራ መሆኑ ግልጽ ነው፡፣

ህወሀት ወታደራዊ ጥቃቱን አሁንም በአፋር ሰሜን ወሎና የተወሰነ የጎንደር ክፍል ወስጥ ገድቦ የሚገኘው አቅም ሰላጣ ብቻ ነው፡፡ የዚህ ምስክሩ ደግሞ ቢችል ኖሮ ቢያንስ እስካሁን  ኤርትራን ከባድመ  ወይም አለ ከሚሉበት ሽራሮ አካባቢ ፣  በጉልበት ማስወጣት በቻለ ነበር፡፡ ወልቃይት፣ ጠገዴን ጠለምትንና ራያንም  እንዲሁ ሙሉ በሙሉ በተቆጣጠረ ነበር፡፡ አቅም ሰለሌለው ሳይሳካለት  ቀረ እንጂ  ወልቃይትን ይዞ ወደ ሱዳን የሚያስገባ ኮሪደር ለመክፈት 36 ሙከራ ማድረጉ የሚታወቅ ነው፡፡

ይህን ሁሉ ሰመለከት የህወሀት እካሄድ  እየተነሳሳ የሚገኘውን የትግራይ ህዝብ ቁጣ አዳፍኖ መቆየት አና ተጨማሪ ጊዜ ገዝቶ ለሌላ ጦርነት መዘጋጀትን እንጂ  ሰላምን ለማስፈን የመረጠ አይመስልም፡፡

በአካባቢው ሰላም እንዲመጣ ከተፈለገ ህወሀት መሰረታዊ የአስተሳስብ ለውጥ ሊያደርግ ይገባል፡፡ ቢያንስ ወልቃይት ጠገዴን ጠለምትና ራያን እንደገና ለመውስድ መሞከር ከቶውንም ከባድ ኪሳራን የሚያስከትል ግጭቱን የሚያስቀጥልና የትግራይንም ህዝብ አበሳ የሚያራዝም መሆኑን ተገንዝቦ ከዚህ ውጭ የትግራይ ህዝብ እንደማንኛውም ኢትዮጰያዊ ተጠቃሚ ሊሆን የሚችልበትን ሁኔታ መነጋገር የተሻለ ይሆናል፡፡

የህወሀት ሰራዊትንም በተመለከተም፣ በሀገረ መንግስቱ ላይ ጥቃት ከፈጸመ በኳላ እንደ ቅድመ ጦርነቱ  መቀጠል እንደማይችል መገንዘብ ይገባል፡፡ አሁን በሰራዊቱ ወስጥ የተሰለፉት ሁሉ ወደ መደባኛ ሰራቸው ( ገበሬው ወደ ግብርናው፣ ተማሪውም ወደ ትምርቱ፣ ወዘተ ) የሚመለሱበት  ሁኔታ መመቻቸት ይኖርበታል፡፡

ለትግራይ ክልል የፖሊስ ሰራ ደግሞ መደረግ በሚገባው ጉዳይ ላይ መነጋገርና መስማማት ይገባል፡፡ ባለ ታንክና ባለመድፍ ኮማንዶ ሳይሆን ትግራይ እንደክልል የሚያስፈልጋት እጅግ የተመጠነ ወንጀልን የሚከላከልና ህግና ደንብን የሚያስከብር  የፖሊስ ሀይል ነው፡፡ ከዚህ ውጭ መሄድ ሌላ ስህተትን መድገም ይሆናል፡፡

የትግራይ ህዝብ ደህንነት የሚጠበቀው እስከ አፍንጫው በታጠቀ ለአንድ ፖለቲካ ፓርቲ ታማኝና ታዛዥ በሆነ “ልዩ ሀይል” አለመሆኑን በተግባር ተመልክተናል፡፡

ይህን ጦርነት በመጀመርም ሆነ በማስቀጠል ረገድ ህወሀት የተከተለው ጀብደኛና እጅግ የተሳሳተ እስትራተጂ ለትግራይ ህዝብ ያተረፈው እልቂት የንብረት ውድመትንና አላሰፋልጊ ቂም በቀልን ነው፡፡ አለመታደል ሆኖ አሁንም በዶክተር ደብረጽዮን የቀረቡት እምስቱ ቀድመ ሁኔታዎች ይህንኑ ከማሰቀጠል ውጭ የስላም ብርሀን ወይንም ተስፋን የሚፈነጥቅ አይደለም፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *