Analysis

የመጨረሻው ደወል – አንዱ ዓለም ተፈራ

ረቡዕ፤ ግንቦት ፳ ፫ ቀን፣ ፳ ፻ ፲ ፫ ዓ. ም.

እየጠራ መጥቷል
ወለል ፍንትው ብሎ፣
የተሸከምነው ጉድ
ሊወድቅ ተንከባሎ።

ሥላሴ ገደሞ የተላከ ክርሰቲያን 1 1 1

አሁን ጉዳዩ፤ ኢትዮጵያን እናድናት፤ ወይንስ ሲያፈርሷት ዝም ብለን እጆቻችንን አጣጥፈን እንቀመጥ! ነው። ማንም ብቻውን ወይንም በቡድን ተከልሎ ነፃ የሚሆንባት ሀቅ የለም። አጥሩ ተከልሎ ወዲያና ወዲህ ተለይቷል! መንጠልጠል የለም፤ የአጥሩ እሾህ ይዋጋል! መቁነጥነት ኑሮ አይደለም! ጎርፉን መከተል ወይንም ጥሶ መውጣት ነው።

እንዲህ ነው

እያንዳንዱ የአስተዳደር ፖለቲካ ሂደት፤ የየራሱ የሆነ መስመር አለው። የራሱን መስመር ጥሶ ወደሌላ ሊገባ አይችልም፤ ማንነቱ አይፈቅድለትምና! ያን መስመር ከጣሰ፤ ማንነቱን ቀየረ ማለት ነው። በዚህ ሁኔታ ከሄደ፤ መጀመሪያ የታቀደለትን ግብ አይመታም። ዴሞክራሲን አቅፋለሁ ብሎ፤ ሌሎቹ ለኔ ወገን አገልጋይ መሆን አለባቸው! የሚባል ነገር የለም። አንድም ዴሞክራሲያዊ አሰራርን መቀበል ነው፤ አለያም አምባገነን መሆን ነው! ሁለቱንም አንዴ መሆን አይቻልም። በርግጥ ይህ በአንድ ግለሰብ ወይንም በቡድን ይተገበራል። አሁን በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ሂደት፤ ከተጀመረውና የኢትዮጵያ ሕዝብ የኔ ብሎ ተቀብሎ ከያዘው መስመር ወጥቷል። የመጨረሻው ደወል ተደውሏል። የኢትዮጵያ ሕዝብ የተዋደቀለት ለውጥ፤ ከሽፏል። የጎሳ ፖለቲካ ሥር ተክሏል። ሁሉም ፖለቲከኛ በየጎሳው ተሸጉጧል። መንግሥቱ ለይቶለት በአክራሪ ኦሮሞ ፅንፈኞች ተጠልፏል። በሰላም ለውጥ የማምጣቱ በር ተዘግቷል። ከዚህ የምንወጣው በምኞትና ዝም ብሎ በመጠበቅ ሳይሆን፤ ሁኔታው በሚፈቅደው መሠረት፤ ተደራጅቶና ታጥቆ፤ ለትግል በአንድነት በመነሳት ብቻ ነው።

ላብራራ!

የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባርን ከፋፋይና በጎሳ የተመሠረተ ፖለቲካ በቃኝ ብሎ፣ አትከፋፍሉን ብሎ፣ ይሄን ፀረ-ኢትዮጵያ ድርጅት ከመንበረ ሥልጣኑ አባረረው። ሕዝቡ እፎይታ አገኘን ብሎ፤ እኒያኑ የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ለውጥ አምጪ ብሎ ተቀብሎ፤ ለውጥ ይመጣል የሚለውን ተስፋ ተሸክሞ ቤቱ ገባ። አረንጓዴ ብጫና ቀይ ሰንደቅ ዓለማ እያውለበለቡ፣ ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ! እያሉ፣ የለውጥ ሳቅ እያሳዩ፣ ሥልጣኑን የጨበጡት ሹሞች፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ፤ ተስፋህን ብላ! ብለው፤ በአክራሪ ትግሬ ፋንታ አክራሪ ኦሮሞ ተክተው፤ መከፋፈሉን፣ ማዳላቱን፣ በሙስና መዘፈቁን፤ በከፋና በገለማ መንገድ ቀጠሉበት። መታወቅ ያለበት፤ በትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት፤ ሕዝቡ ለምን ትግሬ ገዛን! ብሎ አልተነሳም። የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ አንዱን ገዢ ወገን በማንነቱ ለይቶ ፍጹም አይመለከትም። ይሄን የሚያደርጉት ባለሥልጣናት ብቻ ናቸው። ዛሬም በሥልጣን የተቀመጡት አክራሪ የኦሮሞ ሹሞች፤ ኦሮሞዎችን ለሥልጣን ኮቻቸው መጠቀሚያ ያድርጓቸው እንጂ፤ የኦሮሞን ወይንም የማንንም ወገን ሳይሆን፤ ራሳቸውን እና አሳላጮቻቸውን ብቻ ነው የሚወክሉትና እየጠቀሙ ያሉት።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአማራ ሕዝብ ዐብይ ድክመት – መስፍን አረጋ

የኢትዮጵያ ሕዝብ ደሙን አፍስሶና ሀብት ንብረቱን አጥቶ፤ ይከተልልኛል ብሎ ተስፋ ያደረገው ለውጥ፤ ከሽፏል። አንድም ለውጥ የለም! በርግጥ ከሹሞቹ ቋንቋ በስተቀር። ይልቁንም የአሁኖቹ ተረኞች፤ የበለጠ እብሪተኛ፣ የበለጠ አረመኔ፣ የበለጠ ሙሰኛ፣ የበለጠ ቀማኛ፣ የበለጠ ጋጠወጥ ናቸው። አሁን ያለንበት ወቅት፤ አንድነቱ ቀርቶ፤ ከመቼውም የበለጠ የተከፋፈልንበት ሰዓት ነው። ንብረት ሁሉ በጣም ጥቂት በሆኑ ሹማምንት ቤት ገብቶ፤ ድሃው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር፤ በጣም ጨምሮ አድጓል። ልማት፤ በአደባባይ ጉራ ለመንዣ ካልሆነ በስተቀር፤ የደሃውን ሆድ አልሞላም። የኑሮው ውድነት በጣም ከፍቶ፤ የረሃብተኛው ሲቃ መንገድ ላይ ተዝረክርኳል። ጥቂቶች ሰማይ ጠቀስ ፎቆችን እየገነቡ፤ ማደሪያ ያጣው በጅብ ሲበላ፤ መገረሙና አዲስ ነገር መሆኑ፤ ከቀረ ቆይቷል። አገር ለቆ መሰደድ እንደ ታላቅ ዕድል፤ አሳዳጁ በዝቷል። በውጪ ያለው ኢትዮጵያዊ ቁጥር፤ ከመቼውም የበለጠ ከፍ ያለ ሆኗል።

ዋናው የለውጡ ማሽከርከሪያ የነበሩት፤ አትከፋፍሉን! የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ነን! አገራችን አንድ ናት! እያንዳንዳችን እኩል ኢትዮጵያዊ ነኝ! በኢትዮጵያዊ ማንነቴ የትም የኢትዮጵያ ክፍል ባለቤት ነኝ! የትም መኖር እችላለሁ! ሙስናና ወገንተኝነት ይጥፉ! እኒህ አገር አውዳሚዎች ናቸው! በትውልድ ቦታዬ፣ በቋንቋዬ፣ በሃይማኖቴ የተነሳ ልዩነት አይደረግብኝ! ሹሞች ሥልጣናቸውን ለግል ኪሳቸውና ቤተሰባቸውን ለማበልጠግ አይጠቀሙበት! ጦርነት ይቁምና በኢትዮጵያ ምድር፤ የትም ቦታ ሠርተን እንብላበት! ሕግና ደንብ ኖሮ፤ በሰላም እንደርበት! የመሳሰሉት ነበሩ።

አክራሪው የኦሮሞ ፅንፈኛ ገዢ ቡድን፤ ይሄን ሁሉ ወደጎን ጥሎ፤ በዚያው አስልጥኖ ባሳደገው የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ስርዓት፤ አሁንም አከርፍቶ ገፋበት። ጦርነት ያገራችን መታወቂያ ሆኗል። መተላለቅ ሃይማኖታችን ሆኗል። ድህነት መታወቂያችን መሆኑ ቀርቶ፤ ማንነታችን ሆኗል። ይባስ ብሎ፤ በያንዳንዱ መስሪያ ቤት፤ ከዘበኛ እስከ ዋና ባለሥልጣን ድረስ ኦሮሞ በመሾም፤ ኢትዮጵያ ጠፍታ የኦሮሞ አገር ብቻ እንድትሆን እተደረገ ነው። ይህ በጎሳ የተመሠረተ ፖለቲካ፤ በሚሰቀጥጥ መልኩ ሥር ሰዷል። ወደድንም ጠላንም፤ የጎሳ ፖለቲካ በቀላሉ የማይነቀልበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

“የኔ ጎሳ ከሆነ፤ ሁሉም ነገር ትክክል ነው! የአማራ ከሆነ ሁሉም ነገር ደግሞ ወንጀል ነው!” የአገራችን እስትንፋስ ሆኗል። ይሄ በጎሳ የተመሠረተው ፖለቲካ፤ ዜማው፤ “አማራ ጠላት ነው! ኦሮሞ ገዢ ነው! ኦሮሞን ገዥዬ ብለህ ካልተቀበልክ፤ ከዚህ ውጣ! ያንተ አገር አይደለም!” የሚል ነው። ቅኝቱ ከትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር የተወረሰ ቢሆንም፤ አሁን ጋጠወጥነት ተጨምሮበት፤ ከሰብዓዊነት ወጥቷል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ድንቄም ምርጫ! “ልመርጥ” ሄጄ ሳልመርጥ ተመለስኩ – ግርማ በላይ በፖለቲካው መድረክ ላይ ያለው ዝማሬ፤ “የኔ ጎሳ!” የሚል ነው። ከላይ እስከታች ድረስ፤ “ለኔ!” “ለኔ!” የሚል አታሞ እየተመታ ነው። ሁሉም ተቀባይ ሆኖ፤ አማራ ሠጪ እንዲሆን ታዟል። አማራ ምኑን ይሠጣል! ምንስ አለውና! መቼ ነበር አማራ በአማራነቱ ተጠቃሚ የሆነበት መንግሥት በኢትዮጵያ ሥልጣን ላይ የተቀመጠው! እስከመቼ ነው አማራ የሚቀጠቀጠው! አሁንስ በዛ! አማራ አማራነቱን ሊያስከብር፤ ተፈጥሯዊ ግዴታውን ተቀብሏል። አማራ ተነስቷል።

 

ብዙዎቻችን በኢትዮጵያዊነት ከፍተኛ መስዋዕትነትን ከፍለን፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለረጅም ጊዜ ታግለናል። ከዚያ አብዛኛዎቻችን አማራዎች፤ ከኢትዮጵያዊነት ወደ አማራ ኢትዮጵያዊነት ለመምጣት፤ ረጅም ጊዜ ፈጅቶብናል። አሁን ምርጫ የለንም። አማራን መታደግ፤ አገራዊ፣ ታሪካዊ፣ ትውልዳዊና አሁናዊ ግዴታ ነው። በአማራነት መታገል፤ ኢትዮጵያን ለማዳን የሚደረግ ትግል ነው። ጉራጌም ሆነ ሶማሊ፣ ሲዳማም ሆነ ወላይታ፣ አፋሬም ሆነ ጉምዝ፣ አዲስ አበቤም ሆነ አኙዋክ፤ የአማራው የዛሬ ዕጣ፤ ነገ የሱ ዕጣ መሆኑን ተረድቶ፤ ለራሱ ሲል ከአማራው ጎን መስለፍ አለበት። ኦሮሞ ሆኖ ኢትዮጵያን የሚወድና አሁን ያሉት አክራሪዎች የኔ መሪዎች አይደሉም ያለ፤ ከአማራው ጎን መሰለፍ አለበት። ትግሬ ሆኖ የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር የኔ አይደለም ያለ፤ ከአማራው ጎን መሰለፍ አለበት። ከአማራው ጎን መሰለፍ፤ በደልን መቃወም ነው። ከአማራው ጎን መሰለፍ፤ የነገዋን ኢትዮጵያ መታደግ ነው።

አማራው የሚታገለው፤ ራሱን ከኢትዮጵያ ነፃ ለማውጣት አይደለም። አማራው፤ ኢትዮጵያ ከጎሳ ፖለቲካና ከጦርነት አዙሪት እንትላቀቅ እየታገለ ነው። ምክንያቱም አማራ ነፃ የሚሆነው፤ እያንዳንዷ የኢትዮጵያ መሬት ነፃ ስትሆንና እኩልነት በአገራችን ሲሰፍን ብቻ ነው። ይህና ይህ ብቻ ነው፤ ኢትዮጵያን ሊያድናት የሚችለው። ለአንድ ጊዜና ለመጨረሻ ጊዜ ኢትዮጵያዊ ሆነን የምንድነውና የምንቀጥለው፤ ዛሬ ከአማራው ጎን ተሰልፈን ስንነሳ ብቻ ነው። አማራው የኢትዮጵያዊነት መጥፋትና መዳን ምልክት ተደርጎ፤ ተዘምቶበታል። አማራ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንና የኢትዮጵያ እስልምና ተከታይ፤ ወንጀለኛ! የጥፋት ዒላማ ከጀርባው ተለጥፎበታል። ሁሉም የአማራ ሃይማኖተኞች፤ በአማራነታቸው ወንጀለኞች ተብለዋል። ኢትዮጵያን ማዳን የምንፈልግ ሁሉ፤ ከአማራው ጎን መቆም አለብን። አማራው ለሕልውናው የሚያደርገው ትግል፤ ኢትዮጵያንም የማዳን ትግል ነው።

ውድ ኢትዮጵያዊያዊያን፤ ኢትዮጵያ ማለት፤ እያንዳንዳችን፤ ይሄን ቋንቋ እንናገር ወይንም ያንን፣ ከዚህ ቦታ እንወለድ ወይንም ከዚያ፣ የምንኖረው በኢትዮጵያዊነታችን ነው። እያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን ላይ የሚደርሰው ጥቃት፤ የያንዳንዳችን ጥቃት ነው። ያ ካልተሰማን፤ የውሸት ኢትዮጵያዊያን ነን። ዛሬ ሁሉም ለሆዱ ሩጫ እንዲይዝና ኢትዮጵያዊነቱን ትቶ፤ የዚህ ወይንም የዚያ ጎሳ ወገናዊ እንዲሆን የተደረገው፤ ለዓመታት የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባርና የኦነግ ነፃነት ግንባር በያዙት የኔ ባይነት ጎሳ ተኮር ሰበካና፤ ባራመዱት “እኛ የበላይ ነን!” ፖለቲካ ነው። አማራው የያዘው ትግል፤ እኔ የበላይ ልሁን ሳይሆን፤ እኔ መጠቃት የለብኝም! አማራነት ወንጀል አይደለም! እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ! የሚል ነው። ይህ የያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጩኸት መሆን አለበት። ለዚህ፤ ሁላችን በያለንብት መቆጠር አለብን።

Source: zehabesha

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *