ethioAmerica
News Press Release

“አሜሪካ በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብታ ፖለቲካዊ መፍትሔ ያመጣችበት ታሪክ የለም” የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 18/2013 ዓ.ም (አሚኮ)
ስለአቢሲኒያ ኢትዮጵያ ማራኪና አስደናቂ ተፈጥሮ፣ አዝርዕት፣ እንስሳት፣ ባሕል፣ በዓላት፣ ወግ፣ ቁሳዊና መንፈሳዊ ቅርሶች፣ ልዩ የሆነውን የዘመን ቀመር፣ ታሪክ እና አየር ንብረት የሰሙት ምዕራባውያን ትኩረት የተሳበው ገና የዓለም ስልጣኔ ጎህ ሳይቀድ ነበር፡፡
የእንግሊዝ ዕለታዊ ጋዜጦች ተደጋጋሚ ሽፋን፣ የሳሙኤል ጆንሰን “ራሴላስ- የአበሻው መስፍን” እና የሜጀር ሀሪስ “የኢትዮጵያ ደጋማ ምድር” መጽሐፍት ልብ አንጠልጣይ ትረካ በምዕራባውያን ምድር ሁሉ ኢትዮጵያዊነትን ከአድማስ በላይ ከፍ አድርገው አጮኹት፡፡ ዝናዋ በዓለም አደባባይ ጎልቶ የናኘው የሀበሾች ምድር ኢትዮጵያ በምዕራባውያን ሀገራት ዘንድ የነበራት ክብር እና ሞገስ ከፍ ያለ እንደነበር ድርሳናት ያወሳሉ፡፡
ኢትዮጵያ መሪዎቿ መለኮታዊ ኅይል የተቸራቸው፣ ሕዝቦቿ ቀናዒ ተፈጥሮ ያላቸው እና ምድሯ የተቀደሰ እንደሆኑ ዛሬም ድረስ የሚያምኑ ሀገራት እና ሕዝቦች አሉ፡፡ ንጉሴ አየለ “ታላቁ ጥቁር” በሚለው መጽሐፋቸው የፕሬዚዳንት ቴዎዶር ሩዝቬልት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪ ሮቨርት ስኪነር አጼ ምኒልክን “በዓለም ላይ በሕይዎት የሚገኙ ታላቁ ጥቁር ሰው” ሲል እንደገለፃቸው አስነብበውናል፡፡
በዓለም ሀገራት የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ምስረታ ታሪክ ምዕራባውያኑ ወደ አፍሪካ አህጉር ፊታቸውን ሲያዞሩ ቀድማ የምትታያቸው ሀገር ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ ከእነዚህ ሀገራት መካከል ደግሞ አሜሪካ አንዷ እና ቀዳሚዋ ናት፡፡ በኢትዮጵያ እና አሜሪካ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መመስረት አስፈላጊ እንደሆነ ቀድማ ያመነችው ሀገር አሜሪካ ናት ይባላል፡፡
በንግድ፣ በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እና ነጥሮ በወጣ የነፃነት ታሪኳ ኢትዮጵያ በዓለም ሀገራት ውስጥ ዓይነ ግቡ እንድትሆን አድርጓታል፡፡
እንደ አሜሪካ ኢምባሲ ይፋዊ ድረ ገጽ መረጃ መሠረት በመንግሥት ደረጃ በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው በዳግማዊ አፄ ምኒልክ እና በአሜሪካው መልዕክተኛ ሮበርት ስኪነር አማካኝነት ታኅሣሥ 27/1903 (እ.አ.አ) ነበር፡፡ ላለፉት 120 ዓመታት እንደ አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ፍላጎት እና እንደ ኢትዮጵያውያኑ መሪዎች ብስለት ሁለቱ ሀገራት የሞቀ እና የቀዘቀዘ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችንም አሳልፈዋል፡፡
በተለይም በ1950 እና በ1960 አካባቢ የነበረው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት “ወርቃማ ዘመን” ይባል ነበር ያሉን በወሎ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዓለምአየሁ እርቂሁን (ዶ.ር) ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ የንጉሡ የአገዛዝ ዘመን አክትሞ ጊዜያዊ ወታደራዊ ደርግ ሲተካ የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት “የጨለማ ዘመንን” አስተናገደ፡፡ የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም አቀንቃኙ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥትም በአሜሪካ ጥርስ ውስጥ ገባ የሚሉት ዶክተር ዓለምአየሁ በጥብቅ የሚከታተሉት ምዕራባውያን የደርግ መንግሥትን የመቃብር ጉድጓድ በመማስ በኩል ስውር እጃቸው እንዳለበት ይታመናል ይላሉ፡፡
ዓለም በሁለት ጎራ በተከፈለችበት እና በተመሳሳይ ጎራ ያልቆሙ ሀገራት እንደጠላት በሚፈላለጉበት በዚያ ወቅት ሁለመናውን በሶቬት ኅብረታዊ ሶሻሊዝም ያጠመቀው ደርግ ከምዕራቡ ዓለም ሀገራት በተለይም ደግሞ ከአሜሪካ ጋር የከፋ ቅራኔ ውስጥ ገባ፡፡ የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትም ሳንካ ገጠመው ይላሉ ዶክተር ዓለምአየሁ፡፡
ከደርግ መውደቅ በኋላ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የመሸገውን ሽብርተኝነት በመከላከል በኩል ለአሜሪካ ስትራቴጅክ አጋር የሆነችው ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጥላሸታቸውን ገፈው ዳግም የሞቀ ግንኙነት ጀመሩ፡፡ አሜሪካ በቀጣናው ሽብርተኝነትን በመከላከል በኩል ከኢትዮጵያ የተሻለ ታማኝ አልነበራትምና ድጋፏ ቀላል እንዳልነበር አንስተዋል፡፡
ሽብርተኛው ትህነግም በሥልጣን ዘመኑ በቀላሉ የሚጠመዘዝ እና የሚታዘዝ እንደነበር ያመላክታል ነው ያሉት፡፡ በመሆኑም አሜሪካ ከሰሞኑ ከአሸባሪው ትህነግ ጋር እርቀ ሰላም፣ ይካሄድ፣ የአማራ ልዩ ኃይል አካባቢውን ይልቀቅ፣ በትግራይ የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነት ይኑር እና ዓለም አቀፍ የብዙኃን መገናኛ ተቋማት ይግቡ የሚሉት ጥያቄዎቿ “ከእናት በላይ ሞግዚት” አድርጓታል ይላሉ፡፡
የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መቀዛቀዝ የጀመረው በኢትዮጵያ ከታየው ለውጥ በኋላ እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር ዓለምአየሁ ይህም ከጀርባው ሕጋዊ ያልሆነ ጋብቻ እንደነበር አመላካች ነው ባይ ናቸው፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የውኃ ሙሌትን አስታከው ተደጋጋሚ ጫና ለመፍጠር ሲጥሩ የነበሩት ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግፊታቸው ከግል ፍላጎታቸው የመነጨ ነው የሚል የብዙ ኢትዮጵያዊያን እምነት ነበር፡፡ ነገር ግን ከድህረ ትራምፕ በኋላ ያለችው አሜሪካም ኢትዮጵያን በሚመለከት የምታራምደው ሃሳብ በቅራኔ የተሞላ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
አሜሪካ በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብታ ፖለቲካዊ መፍትሔ ያመጣችበት ታሪክ እንደሌለም የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ አንስተዋል፡፡ የውስጥ አንድነትን ማጠናከር፣ ከሌሎች ሀገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ማስፋት፣ ሌሎች ምጣኔ ሃብታዊ አማራጮችን መጠቀም እና የአፍሪካ ኅብረት አህጉራዊ ትስስርን ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡
ተጨማሪ መረጃ ምንጭ፡- የንጉሴ አየለ “ታላቁ ጥቁር” መጽሐፍ
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Source: https://www.amharaweb.com/

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *