covid-19
Health News

ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ በሙሉ በራሳቸው ወጪ ወደ ለይቶ ማቆያ ይገባሉ ተባለ

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ዛሬ አመሻሽ ላይ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በመግለጫቸው የኢኮኖሚ፣ የጸጥታ፣ የጤና እና የማህበራዊ ጉዳዮች ኮሚቴ ተቋቁሞ የኮሮናቫይረስ እድገት በኢትዮጵያ ሲከታተል መቆየቱን ተናግረዋል።

በዚህም መሠረት አዳዲስ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ተወስኗል ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ። ውሳኔዎቹም የሚከተሉት ናቸው።

1.ማንኛውም ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ ሰው ወደ ለይቶ ማቆያ ይወሰዳል

ማንኛውም ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ ሰው ለ14 ቀናት ወደ ለይቶ ማቆያ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አስታውቀዋል።

ወጪዉም በግለሰቡ ይሸፈናል በለዋል።

2. በረራ ይደረግባቸው የነበሩ ከ30 በላይ አገራት በረራ እንዲቋረጥ ተደርጓል

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ከ 30 በላይ አገራት የሚያደርገውን በረራ እንዲያቋርጥ መወሰኑን ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አየር መንገዱ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰበት ተናግረዋል።

“አየር መንገዱ 190 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ አጋጥሞታል። በዚህም ወደፊት ከፍተኛ ችግር ሊገጥመው እንደሚችል ይጠበቃል” ብለዋል።

3.የዕምነት ተቋማት

የአምልኮ ስርዓቱ እና ልምዱ ለበሽታው ተጋላጭ ያደርጋል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ ከኦርቶዶክስ ኃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህም “በእነሱ [ኦርቶዶክስ ኃይማኖት አባቶች] በኩል መልዕክት እንደሚተላለፍ ይጠበቃል” ያሉ ሲሆን፤ የኦርቶዶክስ አባቶች መግለጫ ዛሬ እንደሚወጣ ጠቁመዋል።

የፕሮቴስታንት መሪዎችም ቴክኖሎጂን በመታገዝ አገልግሎት እንዲሰጡ አማራጭ መቀመጡን ተናግረዋል።

በእስልምናም የሚደረጉ ሰላቶች ንክኪ ስለሚኖራቸው፤ የሃይማኖት መሪዎች እርምጃ እንደሚወስዱ እና መግለጫ እንዲሰጡ መንግሥት ጥሪ አስተላልፏል ብለዋል።

4.በማረሚያ ቤት የሚገኙ ታራሚዎች

በማረሚያ ቤቶች በሽታው ከገባ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል የተናገሩት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ታራሚዎችን ወደ ሌሎች ቦታዎች ወስዶ ዘርዘር ለማድረግ ተጨማሪ ቦታዎች ተዘጋጅቷል ብለዋል።

አዳዲስ ታራሚዎች ምረመራ ሳይደረግላቸው ወደ ማረሚያ ቤት አይገቡም ብለዋል።

አክለውም የቤተሰብ ጥየቃ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆም መደረጉን ጠቅሰዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ፤ ህጻናትን የያዙ፣ የአመክሮ ጊዜያቸው የደረሰ እና ቀለል ያለ ክስ ያለባቸው እንዲለቀቁ መወሰኑን ተናግረዋል።

5. በውጪ አገር ዜጎች ላይ ስለደረሰው ጥቃት

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ከሰሞኑ የወረርሽኙን ስርጭት ተከትሎ በአዲስ አበባ በውጪ አገር ዜጎች ላይ የደረሰው ጥቃት ‘‘ኢትዮጵያዊ ባህሪ የሌለው ነው’’ በማለት ጥቃቱን አውግዘዋል።

6. የበጎ አድራጎት ሥራዎች

ከሰሞኑ በርካታ ወጣቶች ሰዎችን እጅ ማስታጠብ ጨምሮ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ሲያከናውኑ ነበር። መንግሥት የበጎ አድራጎት ሥራዎቹን በአክብሮት የሚመለከተው ነው ካሉ በኋላ፤ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ሲሰሩ ተገቢውን ጥንቃቄ መውሰድ ተገቢ መሆኑን አሳስበዋል።

7. የሕክምና ባለሙያዎች ጥረት

ጠቅላይ ሚንስትሩ የእስካሁኑን የሕክምና ባለሙያዎችን ጥረት አድንቀዋል። የቫይረሱ ስርጭት የሚስፋፋ ከሆነም በሽታውን ለማሸነፍ ብዙ ጥረት ይጠበቅባችኋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

8. ወረርሽኙን ለመዋጋት የሚገኙ ድጋፎች

ከጃክ ማ፣ ከቢል ጊቴስ እና ከዓለም ባንክ በተገኙ ድጋፎች የዜጎች ሕይወት እንዳያልፍ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

9. የምሽት መዝናኛ ቤቶች ይዘጋሉ

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በአዲስ አበባ የሚገኙ የመሽት መዝናኛ ቤቶች ከዛሬ ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ዝግ ይሆናሉ ብለዋል።

በጠባብ ቦታ ላይ በርካታ ሰዎች ስለሚያስተናግዱ የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር ዝግ ይደረጋሉ ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ።

“በሽታውን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠራችንን እስክናረጋግጥ ድረስ የምሽት መዝናኛዎች እንዲዘጉ ተወስኗል” ብለዋል።

10. ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች

ጠቅላይ ሚንስትሩ የወረርሽኙን መከሰት ተከትሎ ያልተገባ ትርፍ ለማግኘት በሞከሩ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን አስታውሰው አሁንም ሕጋዊ የማስተካከያ እርምጃዎች መውሰድ ይቀጥላል ብለዋል።

11. ለክልሎች የሚደረገው ድጋፍ

በክልሎች የሚገኙ ዋና ዋና ሆስፒታሎች ምረመራ የማድረግ አቅማቸውን ለማሳደግ ስራዎች ሲከናወኑ እንደነበረ አስታወሰዋል።

ለዚህም የሚረዳ የምረመራ እና የማዳን ሥራ እንዲሰራ ተግባብተናል ብለዋል።

12. ምርጫ

ወረርሽኙ ከወራት በኋላ በሚካሄደው ምርጫ ላይ ስለሚኖረው ጫና ሲያስረዱ፤ “ምርጫ ቦርድ የራሱን ግምገማ እያካሄደ ነው፤ ግምገማውን መሰረት በማድረግ የመጨረሻው ውጤት ይፋ ይደረጋል” ብለዋል።

13. የመጠጥ ውሃ እጥረት

የመጠጥ ውሃ እጥረት ባለባቸው ቦታዎች በቦቴ የማቅረብ ሠራዎች እየተካሄደ እንደሆነ ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል።

በተለይ በከተማ አከባቢ ከፍተኛ የውሃ እጥረት መኖሩን አንስተዋል።

14. የኮሮናቫይረስ ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖ

ወረርሽኙ በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና ሊያሳድር እንደሚችል ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ተናግረዋል።

እንደ ምሳሌም አየር መንገዱ ብቻ 190 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ አጋጥሞታል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ በዚህም “አየር መንገዱ ከፍተኛ ችግር ሊገጥመው እንደሚችል ይጠበቃል” ብለዋል።

የአበባ እና የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎችም ከፍተኛ ኪሳራ እንዳጋጠማቸው ተናግረዋል።

“ይቅርታ”

ጠቅላይ ሚንሰትሩ በመግለጫቸው መጨረሻ ላይ “የብልጽግና ፓርቲ የገንዘብ መዋጮ ላይ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎችን እና የፖለቲካ ምሁሮችን በተመለከተ ባደረጉት ንግግር በርካቶች ማዘናቸውን ሰምቻለሁ” ብለዋል።

“ጉዳዩ የማይመለከታችሁ እና በንግግሬ እንድትታቀፉ የሆናችሁ፣ የተማራችሁ እና በተማራችሁበት ዘርፍ አገራችሁን በቅንንተ የምታገለግሉ ውጤትም ያመጣችሁ ሰዎች ጉዳዩ እናንተን የማይመለከት ቢሆንም ጉዳዩ እናንተን የማይመለከት መሆኑን በግልጽ ባለማስቀመጤ እናንተን ይቅርታ ጠይቃለሁ” በለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *