የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ፕሮግራም
ህዳር 2012
መግቢያ
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በነፃና ርቱዓዊ ምርጫ በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ሊመሠረት እንዲችል፣ አባላቱ በኢትዮጵያ ሕዝብ የፖለቲካ ትግልና ሂደት ከፍተኛውን መስዋዕትነት የከፈሉት አባላቱ የወደቁለት ክቡር ዓላማ እውን እንዲሆን፣ ተጠያቂነትና ግልጽነትን የተላበሰ ዴሞክራሲያዊ አሠራር በድርጅቱና በሀገራችን ውስጥ እንዲሰፍን እራሱን እንደገና መርምሮና ሰላማዊና ሕጋዊ ትግልን የሚመጥን መዋቅራዊ መሻሻሎችን አድርጎ፣ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ሕዝብ የገባውን ቃል ኪዳን ዳግም አድሶ፣ በአዲስና በተሻለ አሠራር ትግሉን ለማስቀጠል የበለጠ ተዘጋጅቷል።
ኢሕአፓ ከተመሠረተበት ከሚያዝያ 1964 ዓ. ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚከበሩባት፣ እኩልነት የሰፈነባትና ዜጎች በመፈቃቀድ አብረው የሚኖሩባት ሉዓላዊነቷን የጠበቀች ሀገር በሁሉም መስክ ለመገንባት የሚያስችል ሁኔታ እንዲፈጠር ታግሏል፣ አታግሏል፣ አሁንም እየታገለ ይገኛል። ኢሕአፓ ከምሥረታው ማግሥት ጀምሮ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመሆን ሦስት አገዛዞችን አጥብቆ የታገለ ሲሆን ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱም አገዛዞቹ የኢትዮጵያን ሕዝብ መብት ረግጠውና አፍነው በአምባገነንነት የቀጠሉ መሆናቸውና ጨርሶም ሕዝብ የሚፈልገውን ለውጥ ለመቀበል ዝግጁ አለመሆናቸው ነው።