abiy and WB
News

የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ለመስጠት አቅዶ የነበረውን 500 ሚሊዮን ዶላር አስቸኳይ የገንዘብ ድጋፍ አገደ

ምንጭ፡  https://ethiopiainsider.com

በተስፋለም ወልደየስ

የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ለመስጠት አቅዶ የነበረውን የ500 ሚሊዮን ዶላር አስቸኳይ የገንዘብ ድጋፍ ወደ ባንኩ ቦርድ ቀርቦ እንዳይጸድቅ መታገዱን የተቋሙ ታማኝ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። የእገዳው ውሳኔውን ያስተላለፉት “የዓለም ባንክ ከፍተኛ የስራ አስፈጻሚዎች ናቸው” ብለዋል።

በኢትዮጵያ መንግስት ጠያቂነት ለስምምነት ተዘጋጅቶ የነበረው ይህ የገንዘብ ድጋፍ ለዓለም ባንክ የስራ አስፈጻሚ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ሊቀርብ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው ለመጪው ሐሙስ ሰኔ 25፤ 2012 እንደነበር የተቋሙ ምንጮች አስታውቀዋል። ባንኩ የገንዘብ ድጋፉን ያገደው በሁለት ምክንያቶች መሆኑን ምንጮቹ ጠቁመዋል።

የመጀመሪያው ምክንያት “ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ተመንን ለማስተካከል እየሄደችበት ያለው አካሄድ የተንቀራፈፈ ነው” የሚል መሆኑን ምንጮቹ አስረድተዋል። ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ተመን ማስተካከያ እንድታደርግ ተደጋጋሚ ጉትጎታዎችን እና ግፊቶችን በማድረግ የሚታወቀው የዓለም የገንዝብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) መሆኑን የሚጠቅሱት ምንጮቹ የዓለም ባንክ ይህን በምክንያትነት ማንሳቱ “እንግዳ” ከመሆኑም ባሻገር ከተልዕኮው ጋር የማይሄድ መሆኑን አብራርተዋል።

የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት ዴቪድ ማልፓስ ኃላፊነታቸውን ከተረከቡ በኋላ ወር እንኳ ሳይሞላቸው በሚያዝያ 2011 ዓ.ም. ከጎበኟቸው ሶስት ሀገራት ኢትዮጵያ አንዷ ነበረች | ፎቶዎች፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

በዓለም ባንክ በሁለተኛ ምክንያትነት የተቀመጠው “በኢትዮጵያ የኢነርጂ ዘርፍ ላይ እየተካሄደ ያለው ማሻሻያ በእቅዱ መሰረት እየተከናወነ አይደለም” የሚል ይዘት ያለው እንደሆነ ምንጮቹ ገልጸዋል። ባንኩ ባለፈው ህዳር ወር ባወጣው ሰነድ ላይ ይህን ማሻሻያ የሚደግፈው በዘርፉ “ጾታዊ ተኮር ለውጦች እንዲካተቱ፣ ከዋናው የኃይል መስመር ውጭ ያሉ የኃይል አቅርቦቶች ገበያ እንዲጠናከሩ እና ሀገሪቱ ባላት ሰፊ የታዳሽ ኃይል ሀብት የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ” እንደሆነ ገልጾ ነበር።

የኢትዮጵያ መንግስት እየተገበረ ላለው የኢነርጂ ዘርፍ ማሻሻያ የዓለም ባንክ 200 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ ከስምንት ወር በፊት ለንባብ በበቃው ሰነድ ላይ ይፋ ተደርጓል። ጉዳዩን በቅርበት የተከተታሉ የተቋሙ ምንጭ “ማሻሻያው ተግባር ላይ ውሎ ሳለ ባንኩ የአስቸኳይ ጊዜ የገንዘብ ድጋፉን ለማገድ በምክንያትነት ማስቀመጡ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። እኚሁ ምንጭ የአሁኑ የባንኩ እርምጃ “ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ላይ በያዘችው አቋም ላይ ግፊት ለማሳደር ያለመ ሳይሆን አይቀርም” የሚል እምነት አላቸው።

የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት ዴቪድ ማልፓስ ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ባለፈው ሰኔ 11፤ 2012 ካካሄዱት ውይይት በኋላ በግል የትዊተር ገጻቸው ያሰፈሩት መልዕክት መሰል ጥርጣሬዎችን አጠናክረዋል። ማልፓስ በዚሁ መልዕክታቸው “ኢትዮጵያ እና ጎረቤቶቿ በውሃ ክፍፍል ላይ የሚያደርጉትን ገንቢ ውይይት እና ትብብር ዘላቂ ማድረግ እንደሚገባቸው” አሳስበው ነበር።

እርሳቸው የሚመሩት ተቋም ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በዋሽንግተን ዲሲ ሲያካሄዱት በቆዩት የሶስትዩሽ ድርድር ላይ ከአሜሪካ ጋር በታዛቢነት ሲሳተፍ መቆየቱን የሚያነሱ ወገኖች፤ ባንኩ በቅርቡ ለኢትዮጵያ ያጸደቀውን የገንዘብ ድጋፍ አስመልክቶ ባደረጉት ውይይት ላይ የድርድሩን ጉዳይ ማንሳታቸውን አልወደዱትም። የባንኩን ፕሬዝዳንት አካሄድም በሀገሪቱ ላይ ጫና ለማሳደር ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተርታ መድበውታል።

ማልፓስ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር ካደረጉት ውይይት አንድ ቀን ቀደም ብሎ፤ የአሜሪካ የብሔራዊ የጸጥታ ምክር ቤት “የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ከመጀመሩ በፊት ስምምነት ላይ መደረስ አለበት” ሲል በትዊተር ገጹ በተመሳሳይ መልኩ መልዕክት አስተላልፎ ነበር። ምክር ቤቱ “በምስራቅ አፍሪካ ያሉ 275 ሚሊዮን ህዝቦች ኢትዮጵያ ፍትሃዊ ስምምነት ላይ በመድረስ ጠንካራ አመራር ታሳይ ዘንድ እምነታቸውን ጥለዋል” ሲል አክሏል።

የአሜሪካንን ብሔራዊ ጸጥታ እና የውጭ ፖሊሲ ጉዳዮች በሚመለከተው ይህ ምክር ቤት በሊቀመንበርነት የሚመራው በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ነው። በህዳሴው ግድብ ላይ አሜሪካንን በመወከል በታዛቢነት ሲገኙ የቆዩት የትሬዥሪ ሴክሬተሪ ስቲቨን መኑሽንም የምክር ቤቱ አባል ናቸው።

አሜሪካ በዓለም ባንክ ላይ ያላትን ከፍ ያለ ተሰሚነትን ከግምት ውስጥ የሚያስገቡት የተቋሙ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች የባንኩን የገንዝብ ድጋፍ እገዳ ውሳኔ ከአሜሪካ አቋም ጋር ያገናኙታል። ባንኩ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስተዳደር ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ ከፍተኛ የገንዝብ ድጋፍ ሲያደርግ የቆየ መሆኑን የሚጠቅሱት ምንጮች የገንዘብ ድጋፉ እገዳ ከዚህ ጋር የሚቃረን መሆኑን ይጠቁማሉ። ከማልፓስ የትዊተር መልዕክት አንድ ቀን አስቀድሞ እንኳ ባንኩ ለኢትዮጵያ 250 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ማጽደቁን በማነጻጸሪያነት ያነሳሉ።

ይህ የገንዘብ ድጋፍ ኢትዮጵያ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የሚደርስባትን የኢኮኖሚ ተጽዕኖ መቋቋም ያስችላት ዘንድ የተመደበ ነው። ከአጠቃላይ ድጋፉ ውስጥ 125 ሚሊዮን ዶላር ያህሉ በብድር የተሰጠ ሲሆን ቀሪው እርዳታ ነው። የዓለም ባንክ አካል በሆነው አለም አቀፍ የልማት ማህበር (አይ ዲ ኤ) አማካኝነት ፈሰስ የሚደረገውን ብድር ስምምነት የኢትዮጵያ ፓርላማ ባለፈው ሐሙስ ሰኔ 18፤ 2012 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው አጽድቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

 

ከሁለት ሳምንታት በኋላ የግድቡ ውሃ ሙሌት ይጀመራል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *