Ethiopian in Saudi
Africa News

“ወረርሽኙ መፍትሔ እስከሚያገኝ ስደተኞቹ በያሉበት በትዕግስት ይጠባበቁ” በጂዳ የኢትዮጵያ ቆንስላ

ምንጭ፡ https://www.bbc.com/amharic

 

በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በሳኡዲ አረቢያ እስር ቤቶች ውስጥ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ይገኛሉ።

ስደተኞቹ ለቢቢሲ በላኩት ተንቀሳቃሽ ምስሎች፤ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ስደተኞች በጠባብ እና ሞቃታማ ቦታ ላይ በአንድ ላይ ታጭቀው በአስከፊ ሁኔታ ላይ ሆነው ይታያሉ።

ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ አንድ ወጣት ከሦስት ወራት ገደማ በፊት በየመንመመ በሁቲ አማፂያንና በሳኡዲ መካከል በነበረው ጦርነት ሕይወቱ አደጋ ላይ እንደነበር ያስታውሳል። በወቅቱ የሳኡዲ መንግሥት ወደ ግዛቱ እንዲገቡ ከፈቀደላቸው ስደተኞች መካለከል አንዱ የሆነው ይህ ወጣት፣ ከዚያ በኋላ አሁን ያሉበት ስፍራ መጣላቸውን ለቢቢሲ ተናግሯል።

በእስር ቤቱ ውስጥ ስላለበት ሁኔታም “በሽንት ቤት ውስጥ ነው ያለነው፣ እዚያው እንበላለን፣ ከሽንት ቤት ውሃ እንጠጣለን። ውሃም በሦስት ቀን አንዴ ነው የሚመጣው። እየኖርንበት ያለው ቦታ ልንተኛበት ይቅርና ለማየትም የሚያስጠላ ነው። እላያችን ላይ ሰገራ እየፈሰሰብን ነው” በማለት ያሉበትን ሁኔታ ገልጾታል።

በተለያዩ አሰቃቂ እስር ቤቶች ውስጥ ከሚገኙ ስደተኞች እስካሁን ሰባት ሰዎች የሞቱ ሲሆን፤ አንዱ በሳኡዲ የፀጥታ አካላት ነው የተገደለ” ሲል ከመካከላቸው የሞቱ ሰዎች ቢኖሩም እስከኣሁን የሚረዳቸው ሰው እንዳላገኙም ለቢቢሲ አስረድቷል።

ወጣቱ አክሎም “በአንድ ቀን ሦስት ሰዎች ሞተውብን ዝም ብለው እንደ ቆሻሻ ተጥለዋል። አሁን ራሱ ሊሞት የደረሰ ሰው አለ። እኛን የሚረዳ ሰው ማን እንደሆነ አናውቅም፤ መፍትሔ አጥተናል። ይህንን የምትሰሙም እባካችሁ እርዱን። ከዚህ ሞት አውጡን” በማለት የእርዳታ ጥሪውን አሰምቷል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸውና በዚያው በሳኡዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አስባባሪ የሆኑት አቶ መሀሪ በላይ ትናንት ረፋድ ላይ ስደተኞቹን ለመጎብኘት ባቀኑበት ወቅት፤ ስደተኞቹ አሁንም በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ መመልከታቸውን ተናግረዋል።

“በእስር ቤቱ ያለው ቆሻሻ፣ ረሃብና ሁሉም ችግር የታወቀ ነው” የሚሉት አቶ መሀሪ፤ የታመሙት ህክምና እንዲያገኙ እንዲሁም ወታደሮች ጉዳት እንዳያደርሱባቸው ተነጋግረው መምጣታቸውን ይገልጻሉ።

በእስር ላይ የሚገኙ ስደተኞች ለተለያዩ የጤና ችግር መጋለጣቸው እየተነገረ ነው

የምስሉ መግለጫ,በእስር ላይ የሚገኙ ስደተኞች ለተለያዩ የጤና ችግር መጋለጣቸው እየተነገረ ነው

“እኚህ ዜጎች ከየመን ሲመጡ፤ ልብስ የላቸው፣ ጫማ የላቸው፣ አንድ ቲሸርት ብቻ ለብሰው ነው የመጡት። አንድ ቲሸርት ለብሰው ለሦስት ወራት ያህል በአንድ እስር ቤት ቁጭ ሲሉ፤ በዚያ ላይ አሁን ባለው ከፍተኛ ሙቀት ተጨናንቀው እየደረሰባቸው ያለውን ጉዳት መገመት አያዳግትም” ይላሉ አቶ መሀሪ- ስለሁኔታው ሲገልጹ።

በእስር ቤት የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከዚህ በተጨማሪም በቂ ምግብ በማያገኙበትና ለመታጠቢያ እንኳን ውሃ በሌለበት አስከፊ ሁኔታ ላይ በስቃይ ውስጥ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

በሳኡዲ ያለው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብም እነርሱን ለመርዳት ጥረት እያደረገ እንደሆነም ነግረውናል።

አቶ መሀሪ በጥይት የተመቱ እና እግራቸው ላይ ብረት የገባባቸው እንዳሉ ገልፈው፤ ጂዛን በሚባል ከተማ ያሉት ዜጎች ደግሞ ተላላፊ ይሁን አይሁን ባይታወቅም ሰውነታቸው እና ፊታቸው ላይ እብጠት ስለወጣባቸው፤ ማኅበረሰቡ ለህክምና የሚሆን ብር እያዋጣ መሆኑን ጠቁመዋል።

“የእነዚህ ዜጎች ችግር የሚያበቃው ወደ አገራቸው መመለስ ሲችሉ ብቻ ነው” በማለት ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሱበት መንገድ እንዲፈለግ ጠይቀዋል።

ከቀናት በፊት የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር በእስር ላይ የሚገኙ ስደተኞችን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ወይም ወደተሻለ ማቆያ ሥፍራ ለማሸጋገር ጥረት እያደረኩ ነው ብሎ ነበር።

ይሁን እንጂ በጅዳ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ዜጎችን ወደ አገር ቤት የመመለሱ ጥረት እንደሚዘገይ ትናንት አስታውቋል።

ቆንስላው ረቡዕ ከሰዓት በፌስቡክ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ፤ ስደተኞቹን ወደ አገራቸው መመለስን በተመለከተም፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአፍሪካ ሕብረት ባወጧቸው ድንጋጌዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መፍትሄ እስኪያገኝ ድረስ ስደተኞች በያሉበት ይቆዩ ሲሉ መደንገጋቸውን በአስታውሷል።

ጨምሮም በኢትዮጵያም በቂ የለይቶ ማቆያ ስፍራዎች አለመኖራቸውን በመጥቀስ፤ ስደተኞችን ከሳኡዲ የማስወጣቱ እንቅስቃሴ መስተጓጎሉን ገልጾ በእስር ቤቶች የሚገኙ ዜጎችም በትዕግስት እንዲጠባበቁም ቆንስላው ጠይቋል።

በተያያዘም ቆንስላው በመግለጫው በጄዳ ሺሜሲ (የሴቶች እስር ቤት) በተፈጠረ ግርግር ምክንያት በርካታ ዜጎች ስለመጎዳታቸው መረጃ እንደደረሰው ገልጾ፤ ክስተቱ ለረዥም ጊዜ በእስር ቤት መቆየታቸውን በመቃወም ከእስር ቤት ለመውጣት ሲሞክሩ ከፖሊስ ጋር በመጋጨታቸው የተፈጠረ ነው ብሏል።

በዚህም በአንዲት ስደተኛ ላይ መጠነኛ ጉዳት መድረሱንና ህክምና እንደተደረገላት መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት ቆንስላ በመግለጫው አስፍሯል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *