የትግራይ ቴሌቪዥን
News

የትግራይ ቴሌቪዥንና የድምጺ ወያነ ቴሌቪዥን ስርጭት ተቋረጠ

በትናንትናው ዕለት የትግራይ ቴሌቪዝንና ድምፂ ወያነ ቴሌቪዥን ጣብያዎች የሳተላይት ስርጭት መቋረጡ ታውቋል።

የሁለቱ መገናኛ ብዙሃን ጣብያዎች ሥራ አስኪያጆች ጉዳዩን ለቢቢሲ ያረጋገጡ ሲሆን የትግራይ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ተሻለ በቀለ የቴሌቪዥኑ ጣብያ የሳተላይት ስርጭት እንዲቋረጥ የተደረገው በኢትዮጵያ መንግሥት ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“መንግሥት የሳተላይት ስርጭቱ እንዲቋረጥ አድርጓል። ስለተፈጠረው ነገር ለማወቅ ሳተላይቱን ወደ አከራየን ድርጅት ስንደውል የኢትዮጵያ መንግሥትና የፈረንሳይ መንግሥት ተነጋግረው በሰጡት ትዕዛዝ መሰረት አቋርጠነዋል የሚል ምላሽ ነው የሰጡን፤ ምክንያቱን ስንጠይቅም የፈረንሳይ መንግሥት ያለውን መፈፀም አለብን ነው ያሉት።”

በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንድወሰን አንዷለም ለቢቢሲ በሰጡት ቃል “እስካሁን ባለኝ መረጃ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ሚዲያዎችን የመዝጋት እርምጃ አልወሰደም “ብለዋል።

የትግራይ ቴሌቪዥን ሥራ አስኪያጅ ስርጭታቸው እስከ መቼ ድረስ ተቋርጦ እንደሚቀጥል ያውቁ እንደሆን ተጠይቀው ይህንን ጥያቄ ስርጭቱን ላቋረጠው ድርጅት ማቅረባቸውን ይገልፃሉ።

እነርሱም እስከመቼ ድረስ እንደተቋረጠ እንደማያውቁ እና “ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ተነጋገሩ” ማለታቸውን ገልፀዋል።

ሥራ አስኪያጁ አቶ ተሻለ አክለውም ወደ ኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን መደወላቸውንና ስልካቸውን የሚመልስላቸው አለማግኘታቸውን ተናግረዋል።

አቶ ተሻለ ለቢቢሲ ጨምረው እንደተናገሩት መቋረጡን የሚገልጽ ደብዳቤ ከድርጅቱ አለመጻፉን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በትግራይ ክልል የሚገኘው የቢቢሲ ሪፖርተር የሁለቱ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ስርጭት እየተላለፈ አለመሆኑን አረጋግጧል።

አቶ አበበ አስገዶም፣ የድምፂ ወያነ ቴሌቪዥን ጣብያ ሥራ አስኪያጅ ለሪፖርተራችን እንዳረጋገጡት፣ በበኩላቸው ስርጭታቸው እንደተቋረጠ ፈረንሳይ አገር ወደ ሚገኘው የሳተላይት አገልግሎት አቅራቢ ድርጅት መደወላቸውንና የቴክኒክ ክፍል ኃላፊው የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲቋረጥ ማድረጉን እንደነገራቸው ገልፀዋል።

ባለፈው ሳምንት ድምፂ ወያነ በአዲስ አበባ የሚገኘው ቢሮው አቃቤ ሕግ በሚያደርግበት ምርመራ የተነሳ ፍተሻ እንደተደረገለት መዘገቡ ይታወሳል።

የብሮድካስት ባለስልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንድወሰን እነዚህ ሁለት ድርጅቶች የእርምት እርምጃ እንዲወስዱ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ መጻፋቸውን አስታውሰዋል።

ቢሆንም ግን የጣቢያዎቹ ስርጭት እንዲቋረጥ ባለስልጣኑ የወሰደው ምንም አይነት እርምጃ እንደሌለ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

Source: bbc.com

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *