addis ababa
Opinion

አዲስ አበባ ― ዳቦ፣ የመኖሪያ ቤት፣ መብራት እና ውሃ፣ የመሬት ቅርምት፣ ተረኝነተ፣ ሙስና፣ ግፍ፣ ወዘተ…

 

ያሬድ ኃይለማርያም

አዲስ አበባ ብዙ ስር የሰደዱ እና ውስብስብ ችግሮችን በጉያዋ የያዘች ጉደኛ ከተማ ነች። ልክ እንደ ከተማዋም አዲስ አበቤዎችም እንዲሁ ከዳቦ አንስቶ እጅግ ብዙ እና ውስብስብ የመብት እና የጥቅም ጥያቄዎች እንዳረገዙ ከዚህ ሁሉ ጭንቅ የሚገላግላቸው አስተዳደር ሲናፍቁ ዘመናት ተቆጥረዋል። ይህ ችግር በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ምን ያህል ሊከፋ እንደሚችል መገመት ይቻላል።

የኋላውን ትተን ባለፉት ሁለት ዓመታት [የአዲስ አበበባ ከተማ መስተዳድር] እና የፌደራል መንግሥቱ ከተማዋን ለማዘመን በሚል አዳዲስ ዕቅዶችን ይዘው እና አንዳንዱንም ጀምረው የከተሜውን ቀልብ ለመግዛት ጥረዋል። እነዚህ የተጀመሩ አንዳንድ የልማት ዕቅዶች በእርግጥም ከተማዋን ለማዘመን ይረዱ ይሆናል። ነገር ግን የከተማዋን ሕዝብ የቆዩ እና ውስብስብ ችግሮች የሚፈቱ ስለመሆናቸው በቂ ጥናት መደረጉን የሚያሳዩ ነገሮች አይታዩም።

ሀገሬን ምን ነካት? (አባይነህ ካሴ (ዲ/ን

አብዛኛዎቹ የመስተዳድሩ እንቅስቃሴዎች ገጽታ እና ምርጫ ተኮር ስለሆኑ የከተማዋን ገበና በእነዚህ ትላልቅ እና ከፍተኛ ገንዘብ በሚወስዱ ፕሮጀክቶች ለመሸፈን ጥድፊያም ላይ ያሉ ይመስላል። በሌላው ጎን ከንቲባው በአደባባይ የታሙባቸው እና ጠያቂ ቢኖር በሕግ በሚያስጠይቁ ተግባራት በማኅበረ ድኅረ ገጾች (social media) እና በሚዲያ ሲብጠለጠሉ ቆይተዋል። ከዚህ በሚከተሉት ጉዳዮች መስተዳድሩ አንድም ጊዜ አጥጋቢ ምላሽ ሲሰጥ አልተስተዋለም፤

• በሕገ-ወጥ መንገድ ዘር-ተኮር የነዋሪነት መታወቂያ ማደል፣
• በአንድ ሰው መኖሪያ ቤት ባለቤቱ ሳያውቅ ለበርካታ ሰዎች ዘር-ተኮር የመታወቂያ እና የቁጠባ ብድር መስጠት፣
• በከተማዋ ፕላን መሠረት በየአካባቢው ለልጆች መጫወቻ እና ለልማት የተተው ክፍት ስፍራዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ እና ዘር-ተኮር በሆነ መንገድ በግለሰቦች እጅ እንዲገቡ ማድረግ፣
• ሕገ-ወጥ መኖሪያዎች በሚል የሚደረጉ ዘር-ተኮር የቤት ማፍረስ እርምጃዎች፣
• የከተማዋ ነዋሪ ከዕለት ጉርሱ ቆጥቦ የሠራቸውን የመኖሪያ ቤቶች [የኮንዶሚኒየም ቤቶች] አሁንም ዘር-ተኮር በሆነ መንገድ ለሌሎች አሳልፎ መስጠት፣
• በከተማዋ መስተዳድር ውስጥ ዘር-ተኮር የሆነ የሠራተኞች ድልድልና ሽግሽግ ማድረግ እና በሌሎች ተመሳሳይ ጥፋቶች በአደባባይ መስተዳድሩ እየተወነጀለ ነው።

እነዚህ ክሶች እውነት ተደርገው ከሆነ ሁለት ዋና የጥፋት ዓይነቶችን የያዙ ናቸው። አንደኛው ድርጊቶቹ ለማንም ጥቅም ተብሎ ይፈጸሙ የሀገሪቱን እና የከተማዋን ሕግ የጣሱ ናቸው። ሁለተኛው ጥፋት እያንዳንዱ ድርጊት ዘር-ተኮር መሆኑ ነው። ሌሎቸን የሕብረተሰብ ክፍሎች ለመጉዳት ሆን ተብሎ የተፈጸሙ ነው ባይባልም እንኳ አንድን ዘር ባልተገባ መልኩ፣ ስልጣንን ከለላ በማድረግ እና ሕግን በተላለፈ መልኩ ለመጥቀም የተፈጸሙ ናቸው መባሉ ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ በግዙፍነቱ ቀዳሚ የሆነው ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ተመረቀ

በእነዚህ ክሶች ላይ መስተዳድሩ በድፍኑ አልፈጸምኩም ከማለት ባለፈ ወቀሳዎቹን በዝርዝር እና በማስረጃ ሲያስተባብል አይታይም። የእነዚህን ጉዳዮች ክብደት ከግምት በማስገባት የፌዴራል መንግሥቱ በጉዳዩ ውስጥ ጣልቃ መግባት እና ገለልተኛ አጣሪ አካል መድቦ ለእነዚህ የሕዝብ ብሶቶች በአፋጣኝ ምላሽ ቢሰጥ ጥሩ ነው። ይህን ቸል ማለት ድርጊቶቹ የፌደራል መንግሥቱን ድጋፍ የተቸሩ ያስመስላቸዋል። እነዚህን የሕዝብ ጥያቄዎች ወደ ጎን ለመግፋትም ሆነ በዳቦና በዘይት እደላ ለመሸፈን ከተሞከረ ግን ሌላ የፖለቲካ ቀውስ ማስከተሉ አይቀርም። አዲስ አበቤዎችም ያቄሙበትን ፖርቲ እንዴት መቅጣት እንደሚችሉ የሚያውቁበት መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ምርጫ 97ን ማስታወሱ በቂ ነው።

አቶ ያሬድ ኃይለማርያም መቀመጫውን ጄኔቭ ከተማ፥ ስዊዘርላንድ ያደረገ ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ (Association for Human Rights in Ethiopia) የተባለ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ናቸው።

 

Source: semonegna.com

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *